Site icon ETHIO12.COM

በላልይበላ የሽብር ቡድኑን ጭካኔ ተጋፍጦ አገልግሎት!

በሰሜን ወሎ ዞን ላልይበላ ከተማ የሚገኘው የቅዱስ ላልይበላ ጠቅላላ ሆስፒታል በከተማዋ ለአራት ወራት ያህል ከርሞ የነበረውን የሽብር ቡድኑን የጭካኔ በትር ተጋፍጦ አገልግሎቱ ሲሰጥ መቆየቱን የሆስፒታሉ ተወካይ ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ።

ግፈኛውና አሸባሪው ቡድን የሆስፒታሉን ባለሙያዎች ከመደብደብ አልፎ የሆስፒታሉን ቁሳቁስ በመዝረፍ እና በመሰባበር የክፋቱን ጥግ አሳይቷል ብለዋል።

ሆስፒታሉን በተወካይ ሥራ አስኪያጅነት እየመሩ የሚገኙት ባዮ ሜዲካል ኢንጂነር ሲሳይ ታመነ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ ሆስፒታሉ በአካባቢው ላሉ 300 ሺ የኅብረተሰብ ክፍል አገልግሎት የሚሰጥ ነው። ወራሪው ኃይል ወደ ላልይበላ ከተማ ከገባ ጀምሮ ለአንድ ሁለት ቀን ያህል ሥራ አቋርጦ የነበረ ቢሆንም ወዲያው ኮሚቴ ተዋቅሮ የሽብር ቡድኑን የግፍ በትር በመቋቋም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ወደሥራ ገብቷል።

በሆስፒታሉ የተቋቋመው ኮሚቴ፣ ለጊዜው የተወሰኑ ዲፓርትመንቶችን በማጠፍ በተለይ ወላጆችንና ስር የሰደደ (ክሮኒክ) ችግር ያለባቸውን ህሙማን አሸባሪው ኃይል የሚያደርሰውን ፈተና በመጋፈጥ ሲያገለግሉ መቆየታውን ተወካይ ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል።

እርሳቸው እንዳሉት፤ የሆስፒታሉ ባለሙያዎች መንገድ ላይ እየተደበደቡም ቢሆን ወራሪው ኃይል ከተማውን ተቆጣጥሮት በቆየባቸው በአራት ወር ውስጥ ወደ 34 እናቶች በኦፕራሲዮን እንዲወልዱ ማድረግ ችለዋል። ከአምስት ሺ በላይ የሆኑ ስር የሰደደ በሽታ ያለባቸው ታማሚዎች ወደ ሆስፒታሉ መጥተው ተስተናግደዋል። በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ስራውን ሳያቋርጥ ቆይቷል።

በወራሪው ኃይል ተደፍረው ከመጡ ሴቶች መካከል ሁለት ታካሚዎች ሲሆኑ፣ አንዷ እመጫት መሆኗን የተናገሩት ተወካዩ፣ በኑሮ ደረጃዋም ዝቅተኛ ከሚባሉት መካከል የምትመደብ መሆኗ ተናግረዋል። ተደፍረው የመጡ ሴቶች በተገቢው መንገድ አገልግሎት እንደተሰጣቸውም አመላክተዋል።

በሆስፒታሉ የተቋቋመው ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አቤኔዘር ፈንቴ በበኩላቸው፤ ሆስፒታሉ በከባድ ፈተና ውስጥ ሆኖ ሲሰራ የቆየ ነው ብለዋል። በተለይ የሆስፒታሉ የፋርማሲ ባለሙያዎች ይደበደቡ እንደነበርም ተናግረዋል። በዚህ ሁሉ ውስጥ የሆስፒታሉ ባለሙያዎች የወራሪውን ዱላ ሳይፈሩ ተቋቁመው አገልግሎት ሲሰጡ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

እንደ ኮሚቴ ሰብሳቢው ገለጻ፤ አንዲት እናት ልትወልድ ወደሆስፒታሉ መጥታ እርሷን ለማዋለድ በሚደረገው ሂደት ለጄኔሬተር ናፍጣ መጠቀም እየተፈለገ ወራሪው ኃይል ግን ናፍጣውን በጉልበት ይወስድ ነበር። ከሆስፒታሉ አውቶቡሶች ውስጥ ሁሉ ናፍጣውን በቱቦ እየሳበ ይጠቀም ነበር።

ሆስፒታሉ ከዚህ በኋላ በርካታ ወረዳዎችን የሚያገለግል እንደመሆኑ የክልል ጤና ቢሮ የተለየ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉ አቶ አቤኔዘር ጥሪ አስተላልፈዋል። ሆስፒታሉ በመከራ ውስጥ ሆኖ አገልግሎት ሲሰራ በተመቻቸ ሁኔታ አለመሆኑም መታወቅ አለበት ብለዋል።

በሆስፒታሉ የሐብት አፈላላጊ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ መለሰ አሰፋ በበኩላቸው፤ ወራሪው ኃይል ሆስፒታሉን ካምፕ አድርጎ መክረሙን ተናግረዋል። በዚህም የተነሳ ሆስፒታሉ ለአንድ ሁለት ቀን አገልግሎት መስጠት ያቆመ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኮሚቴ ተዋቅሮ ከሁለት ቀን በኋላ ወደ ሆስፒታሉ ሲገባ ምንም አይነት መድኃኒት እንዳልነበር ገልጸዋል። በዚህም የተነሳ የላስታ ላልይበላ ተወላጆች አስቸኳይ እርዳታ በማቋቋም መድኃኒት ተገዝቶ ከዞኑ መቄት ከሚባል ወረዳ ከፍላቂት ከተማ መድኃኒት ተገዝቶ በአህያ ተጭኖ መምጣቱን አስታውሰዋል።

በዚህ መሃል ግን ስር የሰደደ በሽታ ያለባቸው ታማሚዎች ይሞቱ እንደነበር አስታውሰዋል። የቅዱስ ላልይበላ ሆስፒታል ክፍት ነው በሚልም ከወልዲያ፣ ከቆቦና ላስታ ድረስ ሰዎች መጥተው ይታከሙ እንደነበር አመልክተዋል። 

አቶ መለስ፣ እንዳሉት፣ በወቅቱ ወደ13 የስራ ክፍሎች በወራሪው ኃይል ተሰባብረዋል። ማህበረሰቡን ሲያገለግሉ የነበረው የጥገና ስራ በማካሄድ ነው። በርካታ የሆስፒታሉ እቃዎች በሽብር ቡድኑ አባላት ተሰርቀዋል። በተለይ የህክምና አላቂና ቋሚ እቃዎች ተወስደዋል።

አስቴር ኤልያስ አዲስ ዘመን ታህሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም

Exit mobile version