የጠላት ሃይል አሰፍስፎ ክልሉን ለማተራመስ እየሰራ መሆኑን አውቆ የክልሉ ህዝብ ከመንግስት ጎን ሊሰለፍ ይገባል – አቶ ግዛቸው ሙሉነህ


በሰሜን ሸዋና አካባቢው መሽጎ የሚገኘውን ኃይል ለመደምሰሰስ እየሰራ መሆኑን ክልሉ አስታወቀ

በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋና አካባቢው ሰሞኑን ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር ዛሬ መለስተኛ መሻሻሎች እንደታዩበት፣ የተኩስ ድምጽ መቆሙን፣ ነገር ግን የጠላት ሃይል በአካባቢው መሽጎ እንደሚገኝ የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ገለጹ፡፡
አቶ ግዛቸው በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዛሬ እንደገለጹት፤ በአጣዬና አካባቢው ሰሞኑን ተከስቶ የነበረውን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝና የጠላትን ሃይልን ከአካባቢው ለማጽዳት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
‹‹ዛሬ በአካባቢዎቹ መለስተኛ መሻሻሎች አሉ፣ የተኩስ ድምጽ ቆሟል፣ ነገር ግን ከአካባቢው አሁንም የጠላት ሃይል አልጸዳም፣ መሽጎ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የጠላትን ሃይል ማጽዳት ያስፈልጋል›› ብለዋል አቶ ግዛቸው፡፡
አካባቢውን ከጠላት ሃይል ለማጽዳት የክልሉ የጸጥታ መዋቅር፣ የፌዴራል መከላከያ ሰራዊትና የመረጃ ደህንነትን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ተጨማሪ ሃይል ወደ ቦታው እንዲገባና አካባቢው ነጻ እንዲሆን የማድረግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
ግጭቱ የተከሰተባቸውና ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች በፌዴራል ደረጃም በኮማንድ ፖስት እየተመሩ መሆኑን ገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ጉዳት አድራሾች፣ ከባድ ወንጀል እየፈጸሙ ያሉ የታጠቁ አጥፊ ቡድኖችና ሃይሎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማደረግ አልያም መደምሰስ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ ይህንን ለመስራት የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ይደረጋሉ ሲሉም አመልክተዋል፡፡
የጠላት ሃይል አሰፍስፎ ክልሉን ለማተራመስ እየሰራ መሆኑን አውቆ የክልሉ ህዝብ ከመንግስት ጎን ሊሰለፍ ይገባል ብለዋል፡፡ አጋጣሚውን በመጠቀም መነገድ የሚፈልጉ አንዳንድ የፖለቲካ ሃይሎች ከድርጊታቸው ርቀው በሰከነ ሁኔታ መንግስትን ሊያዳምጡና ሊተባበሩ እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል፡፡
የክልሉ ህዝብ በተለይ ወጣቶች ጉዳዩ ዕልባት እንዲያገኝና ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለስ ትብብር ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
በስጋት አካባቢ ያሉትም በየአካባቢያቸው ተደራጅተው ራሳቸውን እንዲከላከሉ፣ ወደ አካባቢያቸው የጠላት ሃይል ሲመጣ ከመንግስት ጎን ተሰልፈው መረጃ በመስጠት እንዲተባበሩም አቶ ግዛቸወ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ዘገባው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ነው፡፡


See also  "ቀድሞ ጠላት አማራ ክልልን የወረረው በውስጥ ተላላኪዎች ሴራ ስለሆነ ያ አይደገምም"

Leave a Reply