ኢትዮጵያ የአረብ ሊግ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታና ውሃ ሙሌት ላይ ያስተላለፈውን የ“ውሳኔ ሀሳብ” እንደማትቀበል አስታወቀች።
ኢትዮጵያ የአረብ ሊግ ትናንት በሕዳሴ ግድብ ግንባታ እና ውሃ ሙሌት ላይ ያወጣውን መግለጫ የማትቀበለው መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እና ውሃ ሙሌትን ጨምሮ የአባይ ወንዝ አስተዳደርና አጠቀቃም ጉዳይ በአፍሪካ የሚገኙ ባለድርሻ አካላትን ብቻ እንደሚመለከትም ገልጿል።
“ለአረብ ሊግ የናይል ወንዝ እና ሁሉም የተፋፈሱ አገራት የሚገኙት በአፍሪካ እንደሆነ ማስታወስ አያስፈልገንም ያለው መግለጫው ሊጉ የዓለም አቀፍ ሕግ መሰረታዊ መርሆዎችን ወደ ጎን በመተው የአንድ አገር ቃል አቀባይ ሆኗል” ሲል አስታውቋል።
የአፍሪካ ሕብረት “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ” መርህ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ በግድቡ የሶስትዮሽ ድርድር በሚያነሷቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ እንዲስማሙ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሷል።
ይሁንና አረብ ሊግ “የሶስትዮሽ ድርድሩን ያስቀመጠበት መንገድ ስህተት ነው” ሲል ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።
“ግብጽ በቅኝ ግዛት ዘመን በራሷ የወሰነችው የውሃ ሀብት ክፍፍል መቀጠል አለበት የሚለው ግትር አቋምና ጉዳዩን ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው እያደረገች ያለችው ማብቂያ የሌለው ጥረት የድርድሩ ሂደት እንዲዘገይ አድርጎታል” ሲል አመልክቷል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት ለሚመራው የሶስትዮሽ ድርድር ቁርጠኛ መሆኗን አስገንዝቧል።
የአረብ ሊግ የ”ውሳኔ ሀሳብ” እና የግብጽ መግለጫዎች በአፍሪካ ሕብረት ስር በሚካሄደው ድርድር “በጎ በሆነ መልኩ” ተሳትፎ እያደረገች መሆኑን ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይከታዋል ብሏል።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ 2015 በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መካከል በተፈረመው የመርዎች ስምምነት አማካኝነት የሕዳሴ ግድቡን ግንባታ እና ውሃ ሙሌት እንደምትቀጥል ነው ቃል አቀባይ ጸህፈት ቤቱ በመግለጫው ያስታወቀው።
ኢትዮጵያ የድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብቶችን ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የመጠቀም መርህ እንደምታከብር እና ተገዢ እንደሆነችም ገልጿል።