‹‹ በምርጫው ሂደት በጥላቻ ንግግር ላይ የሚሰማሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ አመራርና አባላትን በህግ የመጠየቅ ስራ ይሰራል›› አቶ አወል ሱልጣን በጠ.አ. ህግ የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ

በምርጫው ሂደት በጥላቻ ንግግር ላይ የሚሰማሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ አመራርና አባላትን በህግ የመጠየቅ ስራ እንደሚሰራ በጠቅላይ አቃቤ ህግ የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ አወል ሱልጣን አስታወቁ።

አቶ አወል ሱልጣን በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ህግን የሚያስከብር ተቋም እንደመሆኑ የፍትህ ሥርዓቱን የመጠበቅና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የማድረግ ኃላፊነት አለበት።

ይህን ኃላፊነቱን ከሌሎች የፍትህ አካላት ጋር በቅንጅት ለመወጣት እየሰራ ነው ያሉት አቶ አወል፣ በጥላቻ ንግግር ላይ የሚሰማሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ አመራርና አባላትን በህግ ይጠይቃል ብለዋል። ከምርጫ ቅስቀሳ ጋር በተገናኘ የትኛውንም የወንጀል ድንጋጌ የሚጥሱ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም ጠቁመዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ሂደት ውስጥ ለህዝቡ የሚያስተላልፏቸው መረጃዎች ህጉንና ህገ መንግስቱን ተከትለው የወጡ አዋጆችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን ያከበሩ መሆን አለበት ያሉት ኃላፊው፤ የትኛውንም የሰው ልጆችን መብት የሚጥሱ መሆን የለባቸውም ብለዋል።

በምረጡኝ ቅስቀሳ ሂደት ውስጥ እንዲመርጡ የሚያስችላቸውን ሃሳብ በነጻነት የመግለጽ ህገመንግስታዊ መብት አላቸው ያሉት አቶ አወል ፣ በዛው ልክ ደግሞ ሊያከብሯቸው የሚገቡ ኃላፊነቶችም እንዳሏቸው አመልክተዋል። ይህ ካልሆነ ግን ህግንና ስርዓትን ተከትሎ ተጠያቂ እንደሚሆኑ አሳስበዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ በምርጫ ቅስቀሳ የሚሳተፍ ማንኛውም ሰው ህግ ማክበር መቻል አለበት። ህግን ሳያከብር በህግ የተከለከሉ ተግባራትን ፈጽሞ የሚገኝ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲና ግለሰብ ካለ የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ ንግግርን ለመከላከል የወጣው አዋጅ ተግባራዊ በማድረግ በህግ እንዲጠየቅ ይደረጋል።

በወንጀል ህግ 240 ላይ አንድን ቡድን በሌላ ቡድን ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ማነሳሳት እንደሚያስቀጣ በግልጽ የተቀመጠ በመሆኑ ከምርጫ ጋር ተያይዞ ሁከት፣ ብጥብጥና ረብሻን ሊቀሰቅሱ የሚችሉ መረጃዎችን የሚያስተላልፉ ወይንም ቅስቀሳ የሚያደርጉ አካላትን ለመከላከልና በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።

ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በአስሩም ክፍለ ከተማዎች በአማካኝ ከ30 ያላነሱ አቃቢያን ህጎች ያሉት ሲሆን እነዚህ ዐቃቢያን ህጎች ከምርጫ ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ብቻ በመመርመር ክስ መስርተው ለምርጫ ብቻ ተብሎ ለተቋቋመው ችሎት እንደሚያቀርቡ ጠቁመዋል።

እንደ አቶ አወል ማብራሪያ፤ የወንጀሉ መጠን ከፍተኛ ከሆነና የፀረ ሽብር አዋጁን በመተላለፍ የጥላቻ ንግግርን የሚመለከቱ ትላልቅ ወንጀሎች ሲፈጸሙ ደግሞ የተደራጁና የድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች መርምሮ ተጠያቂ የሚያደርግበት ሂደት ይኖራል ብለዋል።

ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ለ100 አቃቢያን ህጎችን በምርጫ አዋጁ ዙሪያ የማብቃት ስራ ሲሰራ መቆየቱ አስታውቀዋል። የፌዴራል አቃቢያን ህጎችን ከክልል አቃቢያን ህጎች ጋር የፌዴራል ፖሊስን ከክልል አቃቢ ህግ ጋር በማጣመር ስልጠናዎች ሲሰጡ መቆየታቸውን ጠቁመዋል።

ሞገስ ፀጋዬ – አዲስ ዘመን መጋቢት 28 ቀን 2013 ዓ.ም


Leave a Reply