የጎረቤቴ ‘ ገራገር ‘ ፖለቲካ !

አንድ አካባቢ የምንኖር አፍቃሪ ህወሃት ጎረቤት አለኝ። ከድሮም ጀምሮ ከእርሱ ጋር ስንገናኝ ሆነ ብዬ ‘ ገብስ ገብሱን ‘ እጫወታለሁ። ህጻናት ልጆቻችንን ቅዳሜ ጠዋት ዋና ስንወስድና Home work group ስናደርሳቸው በሳምንት ሁለቴ እንገናኛለን።

ጎረቤቴ በዚህ ሰሞን ቤቱን ቀለም መቀባት ይዟል። ስራ ፈትተህ ከምትቀባ ለምን ቀለም ቀቢ ቀጥረህ በአንድ ቀን ሽው አያደርግልህም ? ስል ጠየቅኩት። ከስራ እርፈትም ይሆነኛል ደግሞስ የራሴን ቤት ከፍዬ ላስቀባ ? ሲል መለሰለኝ። ሳምንት አልፎታል እስካለፈው ረቡዕ ድረስ ቀለም ቅቢው ቀጥሎ ሰንብቷል።

ቀለም ቅባቱ ግን እንዲሁ ተራ ቤት ማሳመር እንዳልሆነ እኔም ጎረቤቴም እናውቃለን። ህወሃት ለአዲስአመት አዲስአበባ ስትገባ እርሱ እርሱ ደግሞ ወዳጆቹን ደግሶ ሊያበላ ስለት ተስሎ ነው ደፋ ቀና የሚለው። ህወሃት አዲስአበባ ለአዲስ አመት መግባቷን ሚስቱ ጾታዋ ሴት መሆኗን ያህል የሚተማመንበት ሀቅ ነው። ሸገር ተወልዶ ያደገ ወየንቲ ስልሆነ ሁሌም ይህን ጅልነት ከየት አመጣው ? ስል እጠይቃለሁ። ስንገናኝ ግን እኔም አብሬው ጅል ጅል እጫወታለሁ። ያለፈው ቅዳሜ ” እረ ይሄ ሰውዬ ሰዎቹ ሳይዙት እንደ መንግሥቱ ሀገር ጥሎ ቢሄድ ጥሩ ነው ” አለኝ። ከህወሃት ደጋፊዎች ጋር ያለመከራከር የጸና አቋም አለኝ። አቢይ ኤምሬትስ ውስጥ አረቦቹ ትልቅ ሆቴል እንደገዙለት እንደሰማሁ ሹክ አልኩት። ወዳጄ ቱግ አለ። ” አረብ ሀገር ተሰዶ ቢዝነስ ሊሰራ ? ” ሲል ጠየቀኝ። ” ይመስለኛል plan B ሳይሆን አይቀርም ” አልኩት። ብስጭቱን መደበቅ አልቻለም ። ህወሃቶች የአቢይን መልካም መስማት እንደማይፈልጉ ስለማውቅ ነው ዋሽቼ ደሙን ያሞቅኩት።

ዛሬ አዲስ አመት ነው ህወሃት ጎረቤቴ እንደተመኘው እንቁጣጣሽን አራት ኪሎ አላከበረም። የወየንቲ ደጋፊ እንደሆነ ነገም ሳገኘው ” ጆሮህ ተሳስቶ እንጂ ለመስቀል ነው ሸገር እንገባለን ያልነው ” ብሎ እንደሚከራከረኝ አስቀድሜ አውቃለሁ። እኔም የራሴን ጆሮ በግምገማ ስህተቱ የራሱ እንደሆነ ለማሳመን ብዙ አይከብደኝም። ለአዲስ አመት አራት ኪሎ እንገባለን ተብሎ ስንቱ ቤት ቀለም ተቀባ ? ስንት ሳጥን ውስኪ ተገዛ ? ስንቱ ሆቴል በድብቅ ሲደግስ ከረመ ?

See also  የጣልቃ ገብነት አባዜ፣ የኢትዮጵያዊነትና የምዕራባዊነት ፍጥጫ

እንኳን አደረሳችሁ በድጋሚ ! Samson Michailovich

Leave a Reply