“ከኢትዮጵያዊነት ከፍታ እወርዳለሁ የሚለውን ማዕረጉን ገፈን …”

የመጀመሪያው ውጊያ ሲካሄድ የአገር መከላከያ ሰራዊት ከነበረው ሃይል ጋር ሲነጻጸር የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባርን ከስድስት እጥፍ በላይ ተዋጊ ሃይል ማሰለፉንና፣ በከፍተኛ ደረጃ በትጥቅና ስንቅ የበላይነት እንደነበረው ጀነራል አበባው ታደሰ አስታወቁ። ጀነራሉ ከትህነግ የተጀመረው ጦርነት እንዳልተጠናቀቀና ሰራዊቱ ለቀጣይ ግዳጅ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አመለከቱ። አሁን ሰራዊቱ ከተገነባበት ከኢትዮጵያዊነት ከፍታ በመውረድ ሌላ ነገር የሚያቡትን ማዕረጋቸውን በመቁረጥ እርምጃ እንደሚወሰወሰድ አስታውቀዋል።

የትህጋይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር / ትህነግ መንግስት በነበረበት ወቅት በጎን የራሱን ሃይል ያደራጅ እንደነበር በማስታወስ፣ በዝርፊያና በክህደት ከሰበሰበው በላይ ቀድሞውኑ የአገሪቱን የመከላከያ መሳሪያ ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠር ስለነበር ውጊያ የከፈተው ይህንኑ ተማኖና ከ240 ሺህ በላይ ሃይል አስለልፎ እንደነበር የኢትዮጵያ ጦር ሃይሎች ምክትል ኤታማዦር ሹም ጀነራል አበባው ከመንግስት ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስታውቀዋል።

“ጦርነቱ ሲጀመር ከነተጨማሪ ጀሌዎቹ ውጪ ከሁለት መቶ አርባ ሺህ በላይ የታጠቀ የአሸባሪው የትህነግ ኃይልን ከ44 ሺህ ባልበለጠ ሃይል ገጥመነዋል” ያሉት ጀነራሉ፣ የድሉ ሚስጢር ኢትዮጵያዊ እንድነትና የወቅቱ የእልህ ስሜት እንደሆነ አስገንዝበዋል። አያይዘውም ከሰሞኑ እድገትና ሽልማት ጋር በተያያዘ ምላሽ ሰጥተዋል።

የመከላከያ ሰራዊት ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ የኢትዮጵያ ሠራዊት የሚለካው በስራው ስኬት እና በግዳጅ አፈፃፀሙ እንጂ በብሄሩ እንዳልሆነ ጉዳዩን አስመልክቶ ለተተየቁት ምላሽ ሰጥተዋል። “ከዚህ በፊት በነበረው የብሄር ተኮር የሠራዊት ግንባታ ዋጋ የከፈለው እራሱ ሠራዊቱ ነው” ሲሉ አደረጃጀቱ ለመመታት እንዳጋለጠው ያስረዱት ጀነራል አበባው በአሁኑ ሰዓት “ትዮጵያዊነትን የተላበሰና በሞያው ብቁ የሆነ ሠራዊት እየተገነባ ነው” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በታላቁ ቤተመንግስት ለዴያስፖራ ባደረጉት የእራት ግብዣ ላይ የሰራዊቱ አመራሮች በየደረጃው የተሸለሙትና እድገት የተሰጣቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀድሞ ከነበረው ሃይል አምስትና ስድስት እጥፍ የላቀ፣ ዘመናዊና በአፍሪካ የሚፈራ ሃይል በመግንባታቸው ጭምር እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል። ጀነራል አበባውም ይህንኑ በመድገም አሁን ላይ በከፍተኛ ደረጃ ሙያዊ ብቃት ያለው ሰራዊት እየተገነባ እንደሆነ አረጋግጠዋል።

በቅርቡ የተካሄደው ወታደራዊ የማዕረግና የሜዳልያ ሽልማት በግዳጅ አፈፃፀም ላይ የተመሰረተ፣ በየደረጃው ላሉ ዕዞች ማዕረግ የተሰጠበት፣ የሠራዊቱ አመራሮችን የሚመጥንና የሠራዊቱን ሞራል የገነባ እንደነበር በማብራራት አካሄዱን የብሄርና የዘር ልዩነት እንዳለበት አድርገው ሲያቀርቡ ለነበሩ ግልጽ ምላሽ ሰጥተዋል። መስፈርቱ ብሄርና ዘር እንዳልሆነ መናገራቸው ብቻ ሳይሆን ” የሚገባም ነው” ሲሉ ነው አስረግጠው የተናገሩት። “በመጀመሪያው ምዕራፍ ከአሸባሪው ህወሓት ጋር የገጠመው የኢትዮጵያ ሠራዊት፤ ከጠላት የሰው ኃይል ቁጥር እና ትጥቅ ያነሰ ነገር ግን ኢትዮጵያዊነትን ስንቁ ያደረገ ነበር” ሲሉም እድገቱና ሽልማቱ በዚሁ እይታ ጀመሮ ሊቃኝ እንደሚገባው አመልክተዋል።

ኤታማዦር ሹም የሚሆኑት እሳቸው ስለነበሩ ይህንኑ ለመከላከል በሚሰሩበት ዕድሜያቸው በጡረታ እንዲገለሉ የተደረጉት ጀነራል አበባው በሰሜን ዕዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ተሰንዝሮ ወደ ኤርትራ ሽሽቶ የሄደውን ሃይል ለመመልከት ከሄዱ በሁዋላ ” አልመለስም” ብለው የተበተነውን ሰራዊት በመምራት ስራቸውን እንደጀመሩ ይታወሳል። ጀነራሉ አሸባሪው የህወሓት ቡድን አሁንም ትንኮሳውን እንዳላቋረጠም በቃለ ምልልሳቸው አስታውቀዋል። አሸባሪው ህወሓት ተቆጣጥሯቸው ከነበሩ አካባቢዎች በማስወጣት የተገኘውን ድል “ህዝባዊ ድል” ሲሉ ለሁሉም ኤትዮጵያዊ የሰጡት ጀነራሉ፣ ድሉ የጠላትን የማድረግ አቅም ያዳከመ፣ ከፍተኛ የሰው ኃይልና የንብረት ኪሳራ ያደረሰ መሆኑንም ተናግረዋል።

በጋሸና፣ ሚሌ እና በመሀል ግንባሮች ፈታኝ ውጊያዎች ተደርጎ እንደነበር ጀነራሉ አመልክተዋል። የጠቀሷቸው ግንባሮች ሠራዊቱ ከፍተኛ ጀብዱ የፈጸመባቸው እንደሆነ አመክተዋል። ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሩ የወሰደው ቁርጠኝነት የሠራዊቱን ዝግጁነት አቅም ያሳደገ እንደነበር ከቃለ ምልልሳቸው ለመረዳት ተችሏል።

ጀነራል አበባው የሰጡት ማብራሪያ ከሹመት አሰጣጡ ጋር በተያያዘ ጉዳዩን ከብሄርና ከጎጥ ጋር በማያያዝ ልዩነት ለመፍጠር፣ በተለይም አማራው እንደተበደለና እንደተካደ ተደርጎ ለሚቀርበው ቅስቀሳ በቂ ምላሽ ይሆናል ተብሎ ተገምቷል። ጀነራል አበባው ቁጥብ፣ ብዙ ሚዲያ ላይ የማይበዙና በሕዝብ የተወደዱ በመሆናቸው ማብራሪያቸው ምን አልባትም በእነዚሁ ክፍሎች ላይወደላቸው እንደሚችል ከወዲሁ የገለጹ አሉ።

Leave a Reply