ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ አስር የዓለማችን ቱጃሮች ሃብታቸው እጥፍ ማደጉ ተሰማ

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቱጃሮችን የበለጥ ባለጸጋ፤ በድህነት አረንቋ ውስጥ የነበሩትን ደግሞ የበለጠ ደሃ እንዳደረጋቸው ኦክስፋም የተሰኘው የእርዳታ ድርጅት አስታወቀ።

ድርጅቱ እንዳለው የዓለማችን ደሃ ሃገራት የገቢ ምንጫቸው በመድረቁ ምክንያት በቀን 21 ሺህ ሰው እየሞተባቸው ነው። ነገር ግን የምድራችን 10 ባለሃብቶች በፈረንጆቹ ከመጋቢት 2020 ጀምሮ ሃብታቸው እጥፍ ማደጉን ኦክስፋም ገልጧል። ድርጅቱ ለወትሮው ዳቮስ ከሚከናወነው የዓለም ምጣኔ ሃብት ስብሰባ በፊት ነበር የምድራችን የሃብት ክፍፍልን የሚያሳይ መረጃ የሚለቀው።

ዳቮስ፤ በየዓመቱ ፖለቲከኞች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የመብት ተሟጋቾች፣ የምጣኔ ሃብት ሰዎች እንዲሁም ጋዜጠኞች በስዊዝ ስኪ ሪዞርት ተሰባስበው ውይይት የሚያደርጉበት፣ የሚከራከሩበት እንዲሁም ዘና የሚሉበት ስፍራ ነው። ነገር ግን ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ የዳቮስ ምጣኔ ሃብት ጉባዔ በኦሚክሮን ምክንያት በበይነ መረብ የሚከናወን ይሆናል።

በዚህ ሳምንት የሚከናወነው ጉባዔ የወረርሽኙ ጉዳይ፣ የክትባት ክፍፍልና ኃይል ማመንጨት ሐሳብ ይነሳበታል ተብሎ ይገመታል። የኦክስፋም የታላቋ ብሪታኒያ ቅርንጫፍ ኃላፊ ዳኒ ስሪስካንዳራጃህ እንዳሉት ድርጅታቸው ሪፖርቱን የስብሰባው ሰሞን የሚለቀው የምጣኔ ሃብት፣ የንግድና ፖለቲካ ሰዎችን ቀልብ ለመግዛት ነው።

“በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ቢያንስ በየቀኑ አንድ ሰው ቢሊየነር ይሆናል። በሌላ በኩል 99 በመቶ የሚሆነው የዓለማችን ሕዝብ በእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት ታፍኖ ነበር። የዓለም አቀፍ ንግድና ቱሪዝም ተቀዛቅዞም ነበር። በዚህ ምክንያት 160 ሚሊየን የዓለማችን ሰዎች ወደ ድህነት ዓለም ተገፍትረዋል።” “አንዳች ነገር የዓለማችንን ምጣኔ ሃብት ሸንቁሮ ይዞታል” ሲሉ አክለዋል ኃላፊው።

ኦክስፋም የፎርብስ መፅሔት መረጃን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው የዓለማችን አስር ሃብታሞች እኚህ ናቸው፤ ኢላን መስክ፣ ጄፍ ቤዞስ፣ በርናርድ አርኖልት፣ ቢል ጌትስ፣ ላሪ ኤሊሰን፣ ላሪ ፔጅ፣ ሰርጌ ብሪን፣ ማርክ ዛከርበርግ፣ ስቲቭ ባልመር እና ዋረን ባፌት።

አስሩ ስማቸው የከበደ ቱጃሮች ጠቅላላ ሃብታቸው ከ700 ቢሊየን ወደ 1.5 ትሪሊየን ሲያድግ በግል ደግሞ የኢላን መስክ ገቢ በአንድ ሺህ እጥፍ ሲወንጨፍ ቢል ጌትስ በበኩሉ 30 በመቶ ጭማሪ አምጥቷል።

ፎርብስ መፅሔት የዓለማችን ቱጃሮችን የሚለካው ባለቸው ተቀማጭ ሃብት ለምሳሌ መሬትና ሌሎች ሲቀነስ ዕዳ በማድረግ ነው። ኦክስፋም ከዓለም ባንክ ወስዶ በሪፖርቱ ባካተተው መረጃ መሠረት በጤና አገልግሎት እጦት፣ በረሃብ፣ ፆታዊ ጥቃት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በየአራት ሰከንዱ አንድ ሰው ይሞታል።

ድርጅቱ እንዳለው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት 160 ሚሊየን የዓለማችን ሰዎች በቀን ከ5.50 ዶላር በታች ገቢ ነበራቸው። የዓለም ባንክ መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሃገራት በቀን 5.50 ዶላር የደህነት መለኪያ ነው ይላል። የኦክስፋም ዘገባ አክሎ ደሃ ሃገራት ዕዳቸው እየበዛ ስለመጣ ከማሕበረሰባዊ ወጪያቸው ላይ እየቀነሱ ለሌላ እያዋሉት ነው ብሏል።

የፆታ እኩልነትን በተለመከተ ደግሞ በፈንጆቹ 2019 ጋር ሲነፃፀር 13 ሚሊዮን ሴቶች ከሥራ ገበታቸው ተፈናቅለዋል። በተለይ ደግሞ በዩናይትድ ኪንግደም፣ ባንግላዴሽና ዩናይትድ ስቴትስ ጥቁሮች በኮቪድ ምክንያት እጅግ ተጎድተዋል። ዳኒ ስሪስካንዳራጃህ የዓለም መንግሥታት አሁን እየሄድንበት ያለውን የከፋ መንገድ ለመቀልበስ አንድ መላ መምታት አለባቸው ይላሉ።

ይህ ቱጃሮችን መቅረጥን ሊያካትት ይገባል፤ ከፍተኛ ገቢ ካላቸው የሚገኘው ቀረጥ ጥራት ላለው የጤና አገልግሎትና ለማሕበረሰባዊ ግልጋሎቶች ሊውል ይጋል ይላሉ ኃላፊው።

ከቢቢሲ አማርኛ የተወሰደ

Leave a Reply