አሸባሪው የህወሓት ቡድን ከሱዳን ድንበር ጋር ትስስር በመፍጠርና ከሌሎች ፅንፈኛ ኃይሎች ጋር ቅንጅት በመፍጠር ያደረገውን እንቅስቃሴ ማምከን መቻሉን የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ጄነራል ጌታቸው ጉዲና ገለፁ።
የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥና የአድዋ ድል ጀግና ሜዳይ ተሸላሚው ጄነራል ጌታቸው ጉዲና፣ የሽብር ቡድኑ በግንባር እያደረገ ያለውን ጥቃት ለማፋጠን ከሱዳን ድንበርና ከሌሎች ፅንፈኛ ኃይሎች ጋር ያደረገው ትስስር የምእራብና የማእከላዊ ጎንደር ብሎም የወልቃይት አካባቢ መስተዳድርና የፀጥታ ኃይሎች ከሰራዊታችን ጋር ጥምረት በመፍጠር ባደረጉት ወደር የሌለው ተጋድሎ ማምከን መቻሉን ገልፀዋል።
ለአካባቢው አመራርና ህዝብም ጄነራል ጌታቸው ምስጋና አቅርበዋል።
የሽብር ቡድኑ እንኳን ለሌላ ህዝብ፣ ወጥቼበታለሁ ለሚለው ማህበረሰብ የማይበጅ እንደሆነ የገለፁት ጄነራል ጌታቸው ጉዲና፣ ቡድኑ በህይወት እስካለ ድረስ ከጥፋት የማይመለስና ለእኩይ ዓላማ የተፈጠረ በመሆኑ ይህን የጥፋት ሰደድ ላይመለስ እስከወዲያኛው ማሰናበት ተገቢ እንደሆነም አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
እስካሁን የተሰሩ ስራዎች በውጤታማነት የተቋጩት ጠንካራ የትብብርና የመደጋገፍ ባህል በመስፈኑ እንደሆነ የገለፁት ጄነራል መኮንኑ፣ ከድል ማግስት ያሉ የትንሽነት አባዜዎችን በማኮስመን ትብብራችንን በደነደነ መሰረት ላይ ማስቀመጥ ይጠበቅብናል ብለዋል።
እንደ ሀገር ትልቆች በመሆናችን እይታችንና ተግባራችንን በትልላቅ አጀንዳዎች ላይ ማድረግ ይገባል ማለታቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የፌስቡክ ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
Via EBC