የአፍሪካ ሕብረት መፈንቅለ መንግሥት መንግሥታዊ ለውጥን እንደማይቀበል አስታወቀ

የአፍሪካ ሕብረት ሕጋዊ ያልሆነ መንግሥታዊ ለውጥ በማድረግ ሥልጣን ለመያዝ የሚሞክሩ ቡድኖችን እንደማይቀበልና በእነሱም ላይ ማዕቀብ እንደሚጥል አስታወቀ። ሕብረቱ መፈንቅለ መንግሥት፣ ግጭት እና የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ በተለያዩ ተግዳሮቶች ላይ ምክክር ካደረገ በኋላ ለሁለት ቀናት በቆየው የመሪዎች ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት እንደተናገሩት፤ በአፍሪካ ሕብረት ሕጋዊ ያልሆኑ መንግሥታዊ ለውጦች ተቀባይነት እንደሌላቸው ገልጸው፤

 ይህንን በሚያደርጉ ቡድኖች ላይ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ማዕቀቦችን ይጥላል ብለዋል።

በዚህም መፈንቅለ መንግሥት በማድረግ በወታደራዊ መሪዎች ሲመሩ የነበሩትን አራት ሀገራት ማለትም ቡርኪናፋሶ፣ ጊኒ፣ ማሊ እና ሱዳንን ከአፍሪካ ሕብረት አባልነት ማገዱን የገለጹት ሊቀመንበሩ፤ ሕብረቱ እነዚህ አባል ሀገራት ወደ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲመለሱ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል።

ይህም ሕገ መንግሥታዊ ያልሆኑ የመንግሥት ለውጦች እንዳይስፋፋ እና እንዲቆም እንደሚያደርግም ገልጸው፤ በአህጉሪቷ ያለውን መልከ ብዙ የፀጥታ ችግር በአፍሪካውያን አቅም ለመቅረፍ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም ዴሞክራቲክ ኮንጎ የሰላም ማስከበር ጥረቶች በቀጠናው የፀጥታ ኃይሎች ጥምረት ወደ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጡ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም አፍሪካውያን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በትብብርና በአንድነት ለጋራ ብልጽግና መስራት አለብን፤ በዚህም በቂ የገንዘብ ድጋፍ ሊቀርብ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ሊቀመንበሩ ገለፃ፤ የአፍሪካ ፀጥታ ችግሮች በተለይም ሽብርተኝነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስጋት ቢሆንም በፀጥታው ምክር ቤት የሚሰጠው ድጋፍ አነስተኛና ኢ-ፍትሐዊ ነው። የአፍሪካ ሕብረት ለፖለቲካዊ ሥልጣን ኢ-ዴሞክራሲያዊ መንገድ ለሚከተሉ ቡድኖች ትዕግስት እንደሌለውም አሳስበዋል።

አዲሱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር እና የኮሞሮሱ ፕሬዚዳንት አዛሊ አሱማኒ በበኩላቸው፤ የአፍሪካ ሕብረት የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት ሕጋዊ ያልሆነ መንግሥታዊ ለውጥን በተመለከተ ሰፊ ውይይት አድርጓል ብለዋል።

ሕብረቱ እገዳውን ሲያስቀምጥ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በማሰብ እና ዴሞክራሲያዊ ያልሆኑ መንግሥታዊ ለውጦች በአፍሪካ እንዳይኖር በማሰብ ነው ብለዋል።

የአፍሪካ ሕብረት በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ በተመለከተ የተጠየቁት ፕሬዚዳንት አዛሊ አሱማኒ፤ መሪዎቹ በ2020 የተጀመረውን እያሽቆለቆለ ያለውን የንግድ ስምምነት ትግበራ ለማፋጠን ተስማምተዋል ብለዋል።

See also  ኢትዮጵያ ለዘላቂ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የትኛውንም መሥዋዕትነት ትከፍላለች - መንግስት

“በ2023 አፍሪካ ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ እና የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራን ቀዳሚ አጀንዳዎች ወስጄ እሰራለሁ” ያሉት አዲሱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር አዛሊ፤ ሰላም፣ ፀጥታ እና የልማት አጀንዳዎችን ማሳካት ትልቅ ፈተና እንደሚሆኑ ጠቅሰው፤ የአፍሪካን ሕዝብ ወደ አንድነት በማምጣት ስኬታማ ስራዎችን እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል።

የአፍሪካ የተፈጥሮ ሀብት በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ በኩራት የሚያቆም ነው። አፍሪካን ማልማትና የንግድ ትስስርን ማጠናከር ለሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ ነው ያሉት ፕሬዚዳንት አዛሊ፤” አህጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጠናውን ትግበራ ማሳለጥ ካለምንም ማቅማማት ተቀዳሚ ቁልፍ ጉዳዮቼ ናቸው” ብለዋል።

በሌላ በኩል የአፍሪካ ድምፅ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይሰማ ዘንድ በፀጥታው ምክር ቤት አባል እንድትሆን መስራት ሌላው ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ለመንግሥታት ኢ-ዴሞክራሲያዊ ለውጦች ያለውን ጽኑ አቋም እና የአፍሪካን የነጻ ንግድ ስምምነት ወደፊት ለማራመድ 2023 የተለየ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ሲሉም ተናግረዋል።

36ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ “የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራ ማፋጠን” በሚል መሪ ሃሳብ የካቲት 11 አና 12 መካሄዱ የሚታወስ ነው።

ሳሙኤል ወንደሰን እና ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን የካቲት 14 ቀን 2015 ኣ.ም

Leave a Reply