ኢትዮጵያ ስንዴ ወደ ውጭ መላክ ጀመረች “ለኢትዮጵያ ማድረግ ከሚገባን ትንሹ ስኬት ነው” ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያን የስንዴ ምርት ወደ ውጭ የመላክ መርሃግብር በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን አስጀመሩ።

የኢትዮጵያ ህዝብ ትኩረቱን በሰላም፣ ልማትና ብልፅግና ላይ በማድረግ የበለፀገችና ለሌሎች የምትተርፍ ሀገር ለማየት እንዲተጋም ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመርሃግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ባሌ ላይ ያየነው ስንዴን ኤክስፖርት የማድረግ ሂደት ለኢትዮጵያ ማድረግ ከሚገባን ትንሹ ስኬት ነው ብለዋል።

የምናደርገውንና የምናቅደውን በተግባር በአረንጓዴ አሻራና በህዳሴ ግድብ እያሳየን መጥተናል፤ አሁን ደግሞ ስንዴን ከውጭ ከማስገባት ከማቆም ባለፈ ወደ ውጭ በመላክ ያሰብነውን በተግባር ፈፅመን ለኢትዮጵያዊያንና ለዓለም አሳይተናል ነው ያሉት።

በዚህም ኢትዮጵያ ከስንዴ እርዳታ መላቀቅና ወደ ውጭ መላክ አትችሉም ያሉንን ችለን በማሳየታችን ኩራት ተሰምቶናል ብለዋል።

ለዚህ ስኬት የኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ ሌሎች ክልሎችም በክረምት፣ በበልግና የበጋ መስኖ ልማት ጉልህ አበርክቶ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይም የኦሮሚያ፣ የሶማሌ እና የአማራ ክልሎች ሰፊ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ላይ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ250 ሚሊዮን በላይ እርዳታ ፈላጊዎች መኖራቸውን በመጥቀስ “ኢትዮጵያን ኤይድ” በሚል ስንዴ ለመለገስ ተግተን እንሰራለን ነው ያሉት።

በዓለም ላይ የተፈጠረውን የስንዴ ገበያ ችግር ለማቃለልም ኢትዮጵያ የበኩሏን እንደምትወጣ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ትኩረቱን በሰላም፣ ልማትና ብልፅግና ላይ በማድረግ የበለፀገችና ለሌሎች የምትተርፍ ሀገርን ለማየት እንዲተጋም ጥሪ አቅርበዋል።

የሚያጋጥሙ ችግሮችን በስሜት ሳይሆን በምክክርና በማስተዋል እየፈታን ለሀገር መስራት አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግስት ህዝቡን ከድህነት ለማላቀቅ ከሚሰራው ስራ ባሻገር ለዘመናት ተከማችቶ የቆየውን የእዳ ጫና የማቃለል ትልቅ ህልም ይዞ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን የስንዴና ሌሎች የኤክስፖርት ምርቶች በማሳለጥ ልማቷን በማፋጠን ጠንካራና የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን እናደርጋለን ብለዋል።

“ኢትዮጵያ ያሰበችውን ከማሳካት ሊያቆማት የሚችል እንደሌለ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በወንድማማችነት፣ እየተመካከርን፣ እየተደማመጥን በጋራ የሀገራችንን ህልም ማሳካት አለብን ነው ያሉት።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሺመልስ አብዲሳ፤ ባለፉት አራት ዓመታት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሰነቁት ሀሳብ መሠረት በስንዴ ምርት እራስን ከመቻል እስከ ኤክስፖርት ማድረግ ታቅዶ በመሰራቱ ሰፊ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

See also  “ነጭ ቀለም ያላቸው የአረብ ወታደሮች በኢትዮ ሱዳን ድንበር እየሰፈሩ፣ አዳዲስ ከምፕ እየገነቡ ነው”

በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው ዓመት 10 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ ዝግጁ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በክረምት ይለማ ከነበረው 800 ሺህ ሄክታር መሬት በአሁኑ ወቅት 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር መድረሱን በመጥቀስ።

በ7 ሺህ ሄክታር መሬት የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በዘንድሮው በጀት ዓመት 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር ለማልማት ወደ ሥራ መገባቱን ገልፀዋል።

የክልሉ ህዝብ ስንዴን ኤክስፖርት በማድረግ ታሪክ መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ፤ የኢትዮጵያ ስንዴ ኤክስፖርት የማድረግ ህልም በህይወት እያሉ በመሳካቱ ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

ሀገራዊ ለወጡን ተከትሎ መንግስት ስንዴን በስፋት በማምረት በአጭር ጊዜ ከውጭ የሚገባ ስንዴን በሀገር ውስጥ ምርት መተካቱን ጥቀሰዋል።

የስንዴ ምርት እና የምግብ ፍጆታ ሚዛን ታይቶ ከሀገሪቱ ፍጆታ የሚተርፍ 32 ሚሊዮን ኩንታል ትርፍ እንደሚኖር በመረጋገጡ በዚህ ዓመት ስንዴን ወደ ውጭ የመላክ ስራ በይፋ ተጀምሯል ብለዋል።

ለዚህም ዘንድሮ ሱዳንና ኬንያን ጨምሮ ስንዴ የመግዛት ፍላጎት ያላቸው ስድስት አገራት ጋር የ3 ሚሊዮን ኩንታል የውል ስምምነት ተፈርሟል ነው ያሉት።

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 5/2015

Leave a Reply