መንግስት ሲወቀስበት የነበረውን የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ለውይይት አቀረበ

“ፍትህ የሌለበት ዕርቅ ሰላምን አያመጣም” በሚል በተደጋጋሚ የህግና በዘርፉ ልምድ ያላቸው ሲናገሩ ነበር። ዛሬ የፍትህ ሚኒስቴር የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ አዘጋጅቶ ለውይይት ይፋ ማድረጉን ተከትሎ፤ ከትችት በመላቀቅ ሰነዱን በሙያ የማዳበርና የማጎልበት ተሳትፎ ከዜጎች እንደሚጠበቅ ተመለከተ።

በሽግግር ውስጥ ያለ ማህበረሰብ ከነበረበት ሁኔታ ሲወጣ ወይም ለመውጣት በሚደረግ ሂደት ውስጥ የሚያጋጥመው ፈተና በግጭት፡ በጦርነት ወይም ጨቋኝ ሥርዓት በነበረበት ወቅት ለተፈፀመ ጥቃት፣ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትና በደል የተሟላ መፍትሄ መስጠት አለመቻል አንዱ ችግር እንደሆነ ሰነዱ በመግቢያው አመልክቷል።

“በዋናነት ሙሉ ፍትህ የሚሰጥበትን መንገድ መዘርጋት እና ማህበረሰቡ ተመልሶ ወደ ቀደመ ሁኔታው እንዳይመለስ ለማድረግ የሚያስችል ዘላቂ ሰላም፡ እርቅ፡ መረጋጋት እና የህግ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት መገንባት የሚቻልበትን ሁኔታ …” በሚል ያነሳው ሰነዱ በኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች በተካሄዱ ለውጦች ሳናካ እንደነበራቸው ተሞክሮዎቻቸውን በማንሳት አሳይቷል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በሽግግር ሁኔታ ውስጥ ብታልፍም በተሟላ መልኩ የሽግግር ፍትህ አላማዎች ተተግብረው አያውቁም፡፡ በነዚህ የሽግግር ሂደቶች ያለፉ ጉልህ የሰብአዊ መብቶች ጥስቶች፣ በደሎች እና ጭቆናዎችን መንስኤ ምንነት፣ አይነት እና የጉዳት መጠን በበቂ መንገድ በማጣራት፣ እውነትን በማውጣት እና እውቅና በመስጠት ሂደት ችግር በመኖሩ የተሳካ የሽግግር ጊዜ አላጋጠማትም።

በኢትዮጵያ አሸናፊዎች ፍርድን በድል አድራጊነት ከማስፈጸማቸው የዘለል በተጠያቂነት፡ በይቅርታ እና በእርቅ ላይ የተመሰረተ የተሟላ ሂደት ሙከራ ቢኖርም በወጉ አልተከናወነም።

“ከእርስ በእርስ ጦርነት፡ ግጭት እና ጭቆና በመውጣት ፣ በፖለቲካና በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትርጉም ያለው ሽግግር ለማድረግ በሞከሩ ሀገራት የሽግግር ፍትህ ሂደቶች ተግባራዊ ተደርገዋል። የሽግግር ፍትህ ስርአት መዘርጋቱ ዘላቂ ሰላም፣ እርቅ እና ፍትህ በማስገኘት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዎ አበርክቷል” ያለው ሰነዱ ኢትዮጵያም ይህን ታደርግ ዘንድ ግድ መሆኑን አትቷል።

በሀገራችን ኢትዮጵያም በተለያዩ ጊዜያት የሽግግር ፍትህ ሂደት አላባዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ሙከራ ተደርጓል። የሽግግር ፍትህ ስልቶችን አላማ፡ ግብና የሚኖራቸውን መስተጋብር የሚቃኝ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ሰላልነበር – አማራጮቹ በተንጠባጠበ እና በማይመጋገብ መልኩ እንዲተገበሩ ሆኗል። ይህም የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ እንዳይሆኑ አስተዋፅኦ አደርጓል። ከዚህ አንፃር – በሀገራችን ከተተገበሩ ሙከራዎች በመማር፡ የተገኘውን ውጤት እና ልምድ በመቀመር፡ ዓለምአቀፍ ተመክሮዎችን እና ምክረ ሀሳቦችን ባካተተ መልኩ – የሀገራችንን ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ሁኔታ መሰረት በማድረግ – በሀገራችን የሽግግር ፍትህ በምን አግባብ ሊመራ እና ሊተገበር ይገባል የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ማዘጋጀት አስፈላጊ እንደሆነ አመልክቷል።

See also  ከሱዳን የተነሳ የትህነግ ሃይል (ሳምሪ) ሳይዋጋ ሙሉ በሙሉ ተማረከ

ፍትህ ሚኒስቴር በፌስ ቡክ ገጹ

ለውይይት የቀረበ የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ ማዕቀፍ አማራጮች ሰነድ

ይህ አረንጓዴ የጥናት ወረቀት (የፖሊሲ ማዕቀፍ አማራጮች ሰነድ) በሽግግር ፍትህ ዙርያ ያሉ የፖሊሲ አማራጮችን ለውይይት መነሻ እንዲሆኑ የቀረቡበት ሰነድ ነው።

ሰነዱን መነሻ በማድረግ በሽግግር ፍትህ ዙርያ በሀገር-አቀፍ ደረጃ ውይይት እና ክርክሮችን በስፋት በማካሄድ – በሃገራችን ነባራዊ ሁኔታ የተሻሉ አማራጮችን በመለየት እና የፖሊሲ መነሻ ሃሳቦቹን በማዳበር በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ማዕቀፍ እንዲኖር ለማድረግ ታስቧል።

ከዚህ አንፃር በቀጣይ በሃገር-አቀፍ ደረጃ ተከታታይ የፖሊሲ ውይይት መድረኮች የሚዘጋጁ ሲሆን በቅድሚያ ለዚህ መነሻ ይሆን ዘንድ ይህን ሰነድ ለህዝብ ይፋ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል።

ሰነዱን ተመልክታችሁ ለሚኖራችሁ ማንኛውም አስተያየት የምናመቻቻቸው የውይይት መድረኮች እንደተጠበቁ ሆነው በኢሜይል አድራሻ ethio.transitionaljustice@moj.gov.et ወይም በፖስታ ሳጥን ቁጥር 1370 ለፍትሕ ሚኒስቴር መላክ የሚቻል መሆኑን በማክበር እንገልጻለን፡፡

በዚህም መሰረት ከዚህ በታች የተቀመጠውን ማስፈንጠሪያ/ ሊንክ/ በመጫን ሙሉ ሰነዱን ማግኘት የሚችሉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ ብሏል።

ሰነዱን ያንብቡ

Leave a Reply