በመንግሥትና በኦነግ ሸኔ ወይም ኦነግ መካከል ሲካሄድ የከረመው የመጀመሪያ ምዕራፍ የተባለ ንግግር መጠናቀቁን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሑሴን ቅድሚያ ወስደው ይፋ አድርገዋል። የጎልጉል ታማኝ የመረጃ አቀባዮች እንደሰሙት መንግሥት “አልቀበልም” ያለውና ያላስማማው ጉዳይ ኦነግ በኦሮሚያ ሪፈረንደም እንዲካሄድ ያቀረበው ጥያቄ ዋናው ነው።
ከመንግሥት ተደራዳሪዎች በኩል ቃል በቃል ምን ምላሽ እንደተሰጠ ባይገልጹም ዜናውን ያቀበሉን እንዳሉት ከሆነ መንግሥትም ሆነ አቀራራቢዎቹ አካላት በዚህ ጉዳይ ላይ የያዙት አቋም ተመሳሳይ ሆኗል። ጥያቄው ሚዛን የሚደፋና አሁን ላይ ሊነሳ የማይችል እንደሆነ ቀደም ሲል የኦነግ ከፍተኛ አመራር የነበሩ ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።
የኦፌኮው ሊቀመንበር መረራ ጉዲና ገና ከጅምሩ ኦነግን በሚቃወሙት አፍላ ጊዜያቸው “ኦሮሞ ከማን ነው የሚገነጠለው? ኦሮሞ ግንድ ነው። ቅርንጫፎቹ ከፈለጉ ይገንጠሉ እንጂ” በሚል አቋም ድርጅቱን ሲያጣጥሉ፤ ተከታታይ ጽሁፍ በማቅረብ ሲሞግቱ መቆየታቸውን በጥናታዊ ጽሁፋቸው ላይ የተገኙ ያስታውሳሉ። መረራ በለዘብተኛ አቋም በሚታወቁበት ዘመን የኦነግን አመለካከት በማክሰምና ማስተካከያ አድርጎ በገሃድ የመገንጠል አጀንዳ እንደሌለው ሲያስታውቅ እንደነበርም እንግዳ አይደለም።
በኦሮሚያ የፖለቲካ ጥያቄዎች መመለሳቸውና አሁን ላይ በክልሉ ያለው አመለካከት የረጋ በመሆኑ ብሄርተኝነትን ዳግም ለማሟሟቅ ታስቦ እንደቀረበ የተነገረለት የሪፈረንደም አጀንዳ በአመክንዮ ተቀባይነት እንዳጣ በይፋ ባይገለጽም የመጀመሪያው ዙር የሰላም ንግግር መዘጋቱ ይፋ ሆኗል።
“ዛሬ ላይ ኦሮሞ ያልተመለሰ ምድራዊ አጀንዳም ሆነ ጥያቄ የለውም። ጉዳዩ የፖለቲካ ውድድር ብቻ ነው” በማለት የቀድሞ የኦነግ ከፍተኛ አባሎችና መሥራቾች በሚያመሳስላቸው ከመንግሥት ጋር አብሮ ለመሥራት፣ በሚያለያያቸው ጉዳይ በሰለጠነ አግባብ ለመንቀሳቀስ ወስነው ድርጅቱን መለየታቸው ይታወሳል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ “ኢትዮጵያ ከኦሮሚያ ትውጣ (Ethiopia out of Oromia)” በሚለው የአደባባይ ንግግሩ የሚታወቀው ጃዋር ሲራጅ መሐመድ እንኳን በአሁኑ ጊዜ የሪፈረንደምም ሆነ የመገንጠል ጥያቄ ለኦሮሞ ሕዝብ እንደማይጠቅመው የሚናገር ሆኗል። በአባልነት የተቀላቀለውም ፓርቲ የመገንጠል አቋ ያለውን ኦነግን ሳይን ኦፌኮ እንደሆነ ይታወቃል።
ኦነግ የዛንዚባሩን የሰላም ንግግር ይፋ ሲያደርግ ባወጣው መግለጫ “ውይይቱ በአብዛኛው በአዎንታዊ መልኩ የተከናወነ ቢሆንም በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ግን በዚህኛው የውይይት ምዕራፍ ስምምነት ላይ ለመድረስ አልተቻለም” በሚል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ካወጣው መረጃ ጋር ብዙም ልዩነት የሌለው አቋም ይፋ አድርጓል። ይሁን እንጂ ቢቢሲ በንግግሩ ላይ የተገኙ እንደነገሩት ጠቅሶ “ኦነግ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ባቀረበው ጥያቄ ምክንያት ስምምነት አልተደረሰም” ብሏል።
“ግጭቱን በዘላቂነትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማስቆም እንዲቻል ሁለቱም አካላት የሰላም ውይይቱን መቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ላይ ተግባብተዋል” የሚለው የሁለቱም ወገኖች አሳብ ቢሆንም ጎልጉል ባለው መረጃ ኦነግ በኦሮሚያ ሪፈረንደም እንዲካሄድ በይፋ ጥያቄ አቅርቧል። ጥያቄው ከመገንጠልና አብሮ ከመኖር (ነጻነት ወይም ባርነት) እንደሚለው የኤርትራ ሪፈረንደም ቅጂ እንደሆነ ተመልክቷል።
ኦነግ “የክልል ፓርቲ በመሆኑ የሽግግር መንግሥት በመላው አገሪቱ እንዲቋቋም የመጠየቅ መብት፣ ማንዴቱና ተፈጥሮው አይፈቅድም” ሲሉ የገለጹት ወገኖች፣ የቢቢሲ ዘገባ ቀደም ሲል ከድርጅቱ የጦር አዝማቾች ጋር ካለ ግንኙነት አንጻር የሌሎች ድርጅቶችን ቀልብ ለመሳብና የወቅቱን መጠነኛ ግርግር ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ቅስቀሳ ለማድረግ የታሰበ እንደሆነ አመልክተዋል።
ሸኔ በወለጋ ንጹሐንን ሲገድልና ሲያሰቃይ ፈጣን መረጃዎችን በማቅረብና ጃል መሮን በተደጋጋሚ ቃለ መጠይቅ በማድረግ የሚታወቀው ቢቢሲ በዚህ መልኩ የዜናውን ዕይታ ማንሸዋረሩ የዓላማ ጉዳይ እንደሆነ ተመልክቷል። ኦነግ ወደ ታንዛኒያ ሲሄድ ለመንግሥት ዕውቅና ሰጥቶ እና በሕዝብ የተመረጠ መሆኑን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ አምኖ መሆኑ እየታወቀ ይህንኑ መንግሥት አንተም አብረህ ከእኛ ጋር ተሸጋገር ብሎ ኦነግ ሊጠይቅ እንደማይችል የቢቢሲን የተንሻፈፈ ዘገባ ውድቅ የሚያደርጉና የስብሰባውን ሒደት የሚከታተሉ ይጠቁማሉ። ኦነግ በንግግሩ ላይ ያነሳውን የሬፈረንደም ጥያቄ መዘገብ የፖለቲካ ኪሣራ የሚያስከትል በመሆኑ ቢቢሲ ይህንን መንገድ መከተሉ ግልጽ ነው።
በቀጣይ መነጋገርና ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ላይ እንደሚሠራ ልክ እንደ መንግሥት ያስታወቀው ኦነግ፣ “የሽግግር መንግሥት ከጠየቀ በቀጣይ ምን ሊነጋገር ነው ቀጠሮ የያዘው” ሲሉ የሚጠይቁም አሉ። የኦሮሞን ሕዝብ ቀልብ የሚስብለትና ድጋፍ የሚያስገኝለት ቢሆን ኖሮ ኦነግ የሽግግር መንግሥት ጥያቄውን የቢቢሲን ድጋፍ ሳይጠይቅ ራሱ በመግለጫው ይፋ ያደርገው ነበር ወገኖች የሽግግር መንግሥት የጠየቀ ድጋሚ ወደ ስብሰባ አይመጣም፣ ቀጣይ ስብሰባም እንደሚኖር በመግለጫው አይጠቁምም በማለት ሒሳቸውን ይሰነዝራሉ።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ