የውጭ ጫናዎችን ለመቋቋም ዳያስፖራው ገንዘቡን በህጋዊ መንገድ በመላክ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተጠቆመ

ግንቦት 23 ቀን 2013 (ኢዜአ) ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መ/ቤት ውሳኔ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ጫናዎችን መቋቋም እንዲቻል ዳያስፖራው ገንዘቡን በህጋዊ መንገድ በመላክ፣ መጠኑን በመጨመርና የተጠናከረ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራ በማከናወን ሃገራዊ አለኝታነቱን በድጋሚ ሊያረጋግጥ እንደሚገባ ተጠቆመ።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መ/ቤት ውሳኔን ተከትሎ በኢትዮጵያ ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ጫናዎችን መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የኢፌዴሪ ሚሲዮኖችና ልዩ ልዩ የዳያስፖራ አደረጃጀቶች የተሳተፉበት በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲና በካናዳ የኢፌዴሪ ኤምባሲ ቅንጅት የተዘጋጀ የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል፡፡

መድሩኩን በንግግር የከፈቱት ም/ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ባስተላለፉት መልዕክት ዳያስፖራው እያከናወነ ያለው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ተግባር አበረታች መሆኑን አንስተዋል፡፡

እንዲሁም ከኢትዮጵያ ጥቅም በተጻራሪ የቆሙ ሃይላት የሚያራምዱትን የተደራጀና የተቀናጀ ጫና ለመቋቋም ከመንግስትም ሆነ ከዳያስፖራው ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ከኢትዮጵያ ጥቅም በተጻራሪ የቆሙ ሃይላት ውስጣዊ ተጋላጭነታችንን መንጠላጠያ በማደግና በመልማት ጉዟችን ላይ እንቅፋት በማበጀት ደካማ ሃገር ሆነን እንድንቀር ስትራቴጂ ነድፈውና ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የተጋረጠብንን ችግር የሚመጥን እርምጃ ለመውሰድ በዳያስፖራውም ሆነ በመንግስት በኩል በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

የዕለቱ ተጋባዥ እንግዳና የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር ይናገር ደሴ በበኩላቸው መንግስት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መ/ቤት ውሳኔን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን ችግር ማቃለል እንዲቻል ልዩ ልዩ ስልቶችን ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከነዚህም መካከል የውጪ ንግድን ለማስፋፋትና ከዳያስፖራው የሚላከውን የውጭ ምንዛሪ መጠን ለማሳደግ የፖሊሲ አማራጮችን ማየት እንደሚገኝበት አብራርተዋል፡፡
አያይዘውም ጫናውን መቋቋምና ይህን ከባድ ጊዜ በጋራ ማለፍ እንዲቻል ዳያስፖራው ገንዘቡን በህጋዊ የመላኪያ መንገዶች ብቻ ተጠቅሞ እንዲልክ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው ዳያስፖራው ለሃገራዊ ፕሮጀክቶችና ወቅታዊ ጥሪዎች እያደረገ ስላለው ድጋፍ አመስግነው፣ ይኸው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡

አክለውም ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መ/ቤት ውሳኔ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ጫናዎችን መቋቋም እንዲቻልም ዳያስፖራው ገንዘቡን በህጋዊ መንገድ በመላክ፣ መጠኑን በመጨመርና የተጠናከረ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራ በማከናወን ሃገራዊ አለኝታነቱን በድጋሚ ሊያረጋግጥ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

See also  ሸኔ ጉቦ ወስዶ ያፈናቸውን ሰላማዊ ሰዎች ፈታ፤ "የኦሮሞ ጥያቄ ይህ ነው?"

በመድረኩ ላይ በፓናሊስትነት የቀረቡ የኢፌዴሪ አምባሳደሮች አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ፣ አምባሳደር ፍጹም አረጋ፣ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ እንዲሁም አምባሳደር ዘነበ ከበደ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መ/ቤት ውሳኔ ሊያስከትላቸው ስለሚችላቸው ጫናዎች፣ ጫናዎቹን ለመቋቋም በየተመደቡባቸው ሃገራት እያከናወኗቸው ስላሉት ተግባራት እንዲሁም በሃገር ቤትና በዳያስፖራው መካከል ቅንጅት በመፍጠር መሰራት ስላለባቸው ስራዎች ዝርዝር ሃሳቦችን አቅርበዋል፡፡

የዳያስፖራ አደረጃጀት ተወካዮችም በበኩላቸው ባከናወኗቸው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራዎች ውጤቶች ቢመዘገቡም በቂ አለመሆናቸውን፣ የተናበበና የተቀናጀ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚያስፈልግ፣ በተለይም ኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ካላቸው ቁጥር አንጻር በአሜሪካ ም/ቤቶች ተመራጮች ላይ ተጽዕኗቸውን ለማሳደግ መስራት እንዳለባቸው ተጠቅሷል፡፡

እንዲሁም በመንግስት በኩል መረጃዎችን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ፣ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ስራዎችን ለማጠናከር ብሎም በዘርፉ አቅም ያላቸው ተቋማትን በመቅጠር የሃይል ሚዛኑን ለማስተካከል ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በመጨሻም ም/ጠ/ሚ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት መድረኩ ገንቢና ጠቃሚ ሃሳቦች የተንሸራሸሩበት እንደነበር አንስተው፣ የተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን በዕቅድ ውስጥ በማከተት ለመመለስ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

አክለውም ዋናው ችግራችን ውስጣዊ መሆኑን ተረድተን ከዚህ አንጻር ሁላችንም ያለንን አቅም አሟጠን በመስራት ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት መንቀሳቀስ ይጠበቃል ብለዋል።

Ena

Leave a Reply