የተገዙ ኦሮሞዎች – የኦሮሞን ምስኪን ገበሬ በትህነግ አዘረፉ፣ እያዩና ተባባሪ ሆነው ንብረቱ አወደሙ

“ለኦሮሞ ሕዝብ ስል ነፍጥ አንስቼ ጫካ ገባሁ” የሚለው ኦነግ ሸኔ በጉርብትናም ሆነ በስትራቴጂ ትግል ሊጣመር ከማይችለው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ጋር ገጥሞ በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙትን የኦሮሞ ብሄረሰብ በተባባሪነት ማዘረፉ ተገለጸ። ዘርፎ አብሮ ያዘረፈው ሸኔ አካባቢው ነጻ ሲወጣ የትህነግ አንጋቾች እንዳባረሩትም ተመልክቷል።

አሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ ማኀበረሰቡ የሚገለገልባቸው በርካታ የመንግሥትና የግል ተቋማትን መዝረፋቸውን፤ ዘርፈው ማጋዝ ያልቻሉትን ማውደማቸውን ያስታወቁት በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ሀሰን ናቸው። እሳቸውም ብቻ ሳይሆን ነዋሪዎች ” በራሳችን ሰዎች ተዘረፍን፣ አስዘረፉን፣ አስገደሉን …” ሲሉ ተደምጠዋል። ይህን የሰሙ ” መንጋው በሸኔ መሪነት ኦሮሚያን ቢወራ ምን ሊያደርግ ነው?” የሚል ጥያቄ በድፍን ኦሮሚያ መነሳቱን ይጠቁማሉ። ልክ አማራ ክልል እንደሆነው ስለመፈጸሙ በግልጽ በማህበራዊና በገሃድ ሚዲያዎች እየተገለጸም ነው። በምሁራን ስብሰባም እይተጠቆመ ነው። ለዚህ ይመስላል ኦሮሚያ ሕዝቡ ሸኔን አምርሮ ፊት የነሳው።

አቶ አህመድ ሀሰን በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአካባቢው በቆየባቸው ቀናት ከተላላኪው የሸኔ ቡድን ጋር በመሆን በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በርካታ የመንግሥትና የግል ተቋማት ላይ ጉዳት አድርሷል። በተለይም በግል ዘርፉ ተሰማርተው ሀብት ያካበቱ ባለሀብቶችን ንብረት በመዝረፍና በማውደም ኅብረተሰቡን ጥሪት አልባ አድርገዋል።

አሸባሪው ሕወሓት ማኀበረሰቡ የሚጠቀምባቸውን በርካታ የንግድና የአገልግሎት ዘርፎችን አበላሽቷል። በዚህ ወንጀሉም መገልገያዎቹን ሕዝብ ወደፊት እንዳይጠቀምባቸው በማድረግ አስነዋሪ ተግባር ቢፈጽምም ከአካባቢው ተሸንፎ ተባሯል ብለዋል።

ቡድኑ ከፍተኛ ሀብት የፈሰሰባቸው የቱሪዝም ዘርፉን የሚደግፉ ተቋማትን በመዝረፍ፣ ለማጓጓዝ አመቺ ያልሆኑ ንብረቶችን ደግሞ ማውደሙ በአደባባይ የታየ ሐቅ ነው ያሉት አስተዳዳሪው፣ ከዚህ ባለፈ ሕወሓት በቃላት ለመግለጽ አዳጋች የሆኑ በርካታ አስነዋሪ ተግባራትንም ፈጽሟል ሲሉ ገልጸዋል።

አሸባሪ ቡድኖቹ በከሚሴ ከተማ የሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ መድሃኒቶችን ሙሉ በሙሉ ዘርፏል፤ ሌሎች የሆስፒታሉችን ንብረቶች በመዝረፍ አውደሟል። በዞኑ የሚገኙ ጤና ጣቢያዎች ተመሳሳይ ተግባር ፈጽሟል። በመንግሥት መስሪያ ቤቶችም በተመሳሳይ አስነዋሪ ተግባሩን የፈጸመ ሲሆን፤ በተለይ የዞኑ አዲስ የአስተዳደር ሕንፃ ከ15 ሚሊዬን በላይ ወጪ ተደርጎ የተገዙ ኮምፒውተሮችና ፈርኒቸሮች ተዘርፈዋል። በተለያዩ ስፍራዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶችንም እንደ ካምፕ በመጠቀም የተማሪ መቀመጫዎች ሳይቀር ለማገዶነት በመጠቀም ከጥቅም ውጪ ማድረጉን ገልጸዋል።

ከነዳጅ ማደያዎች ውስጥም ነዳጆችን በመቅዳት ወደ ትግራይ ጭኖ ማጓጓዙን ጠቅሰዋል። በአሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ የጥፋት ቡድኖች የተነሳ ማኅበረሰቡ በተለያየ የሥራ ዘርፍ ተሰማርቶ እራሱን የሚደጉምባቸው ከጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሾች እስከ ከፍተኛ የንግድ ድርጅቶች ወድመዋል። ይህም ሕዝቡ በኢኮኖሚ እንዲላሽቅ ታቅዶ የተሠራ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ የማኀበረሰቡን አብሮ የመኖር እሴት ለመሸርሸር እንዲሁም ስነ-ልቦናውን ለመጉዳት ያለመ ሴራ የሽብር ቡድኑ ፈጽሟል ያሉት አቶ አህመድ፤ ግጭቶችን የብሔር መልክ እንዲይዙ አሸባሪ ኃይሉ በዕቅድ የተመራ ተንኮል አራምዷል ብለዋል።

የኦሮሞና የአማራ ማኅበረሰቦች ለበርካታ ዘመናት አብረው የኖሩበትን እሴት ለማጠልሸት በሁለቱ ሕዝቦች መካከል መጠራጠሮችና ጥላቻዎች እንዲፈጠሩ የሽር ቡድኑ በአካባቢው በቆየባቸው ጊዜያት ጥረት አድርጓል ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ ጥረቱ ከንቱ ሆኖ አሸባሪውና ወራሪው የሕወሓት ቡድንና ተላላኪው ሸኔ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርን በወረራ በያዙበት ወቅት በርካታ የዞኑ ማኅበረሰብ አባላት ኢትዮጵያን አላስደፍርም በሚል ስሜት ፊት ለፊት እንደተፋለሙትም አመልክተዋል።

በተለይም የጂሌ፣ የባቲ ዙርያ ወረዳና የደዌ ሀረዋ ማኀበረሰብ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጉን አንስተዋል። በባቲ ወረ ገርፋ፣ ከሸነን ጂሌ አካባቢ ደግሞ የሰደን ጂሌ አርሶ አደሮች በመደራጀት የአሸባሪዎችን ሕወሓትና ሸኔ ኃይሎችን በመመከትና አካባቢያቸውን ሳያስደፍሩ ቆይተዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ማኅበረሰብ አባላት በአጠቃላይ አሸባሪ ኃይሎቹን በማዳከም ረገድ ታሪክ የሚያስታውሰው ጀግንነት ፈጽመዋል ያሉት አቶ አህመድ፤ ቡድኖቹ የዘረፉትን ንብረት ይዘው እንዳይወጡ የዞኑ ማኅበረሰብ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጉን አንስተዋል።

ፍቃዱ ዴሬሳ

Leave a Reply