ሕንድ ስንዴ ወደ ውጪ መላክ አቆመች

ሕንድ በዩክሬን ጦርነት እና ከፍተኛ የሙቀት መጠን ባሳደረው ጫና ሳቢያ ስንዴ ለዓለም ገበያ ማቅረብ አቆመች። ውሳኔውን የቡድን ሰባት አባል አገራት የግብርና ሚኒስትሮች አጥብቀው ኮንነዋል።የሕንድ የውጭ ንግድ መሥሪያ ቤት ትላንት አርብ መንግሥት በሚያስተዳድረው ጋዜጣ ባወጣው መግለጫ ዓለም አቀፍ የዋጋ ግሽበት የሕንድ፣ የጎረቤቶቿን እና ተጋላጭ አገራትን የምግብ ዋስትና ደሕንነት እየተፈታተነ እንደሚገኝ አትቷል። መሥሪያ ቤቱ የሕንድ ፈቃድ ያልተሰጠው የስንዴ ምርት ለሌሎች አገራት እንዳይሸጥ የከለከለው በአገሪቱ የታየውን የዋጋ ጭማሪ ለመቆጣጠር መሆኑን አስታውቋል። በዩክሬን ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በዓለም ገበያ የስንዴ ዋጋ በ40 በመቶ ጨምሯል። ከጦርነቱ በፊት ሩሲያ እና ዩክሬን በዓለም ገበያ ከሚሸጠው ስንዴ እና ገብስ አንድ ሶስተኛውን ያቀርቡ ነበር። ይሁንና በጦርነቱ ምክንያት የዩክሬን ወደቦች ሲዘጉ የእህል ጉተራዎች ወድመዋል። የሕንድ አመታዊ የስንዴ ምርትም በሙቀት መጨመር ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል። በዓለም ሁለተኛዋ የስንዴ አምራች የሆነችው ሕንድ ያሳለፈችው ውሳኔ ግን በቡድን ሰባት አባል አገራት ተቃውሞ ገጥሞታል። በኢንዱስትሪ የበለጸጉት የቡድን ሰባት አባል አገራት ዛሬ ቅዳሜ ባወጡት መግለጫ ሕንድ ፈቃድ ያላገኘ የስንዴ ምርት ለተቀረው ዓለም እንዳይሸጥ ያሳለፈችውን ውሳኔ አውግዘዋል። የጀርመን የግብርና ሚኒስትር ቼም ኦዝደሚር “ሁሉም የወጪ ንግድ ላይ ገደብ ከጣለ ወይም ገበያውን ከዘጋ ቀውሱን ያባብሰዋል” ሲሉ በሽቱትጋርት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስጠንቅቀዋል። ትላንት የተላለፈው ውሳኔ ከመውጣቱ በፊት የተፈጸሙ የግብይት ውሎችን ሕንድ እንደምታከብር የገለጸች ቢሆንም ከዚህ በኋላ ግን የመንግሥት ፈቃድ ማግኘት ግዴታ ሆኗል። ሌሎች መንግሥታት የምግብ ዋስትና ፍላጎታቸውን ለማሟላት ጥያቄ ካቀረቡ እና የሕንድ መንግሥት ፈቃድ ከሰጠ ግብይቱ ሊካሔድ እንደሚችል አሶሼትድ ፕሬስን ጠቅሶ የጀርመን ድምጽ ዘግቧል።

Leave a Reply