«በአገሩ መከላከያ ላይ አፉን የሚከፍት ሕዝብ የለም፤ መንግስትም አይታገስም» ክብር ለመከላከያ ሰራዊት!!

በየትኛውስ አገር ነው የአገሩን ሉዓላዊነትና ነፃነት ለማስጠበቅ የሕዝቡን ዘላቂ ሰላምና ጥቅም ለማስከበር ያለ እረፍት በሐሩርና በቁሩ እያለፈ ዳገቱን እየወጣ ቆልቁለቱን እየወረደ ጋራ ሸንተረሩን እያቋረጠ የሚጠብቀውን ጋሻ ሰራዊት መንግስት ባለበት ሁኔታ ማንም አካል እየተነሳ በነፃነት ደረቱን ነፍቶ በአደባባይ ስሙን የሚያጠፋበት እድል ማግኘት የሚችለው?

Opinion by Thomas Jejaw Mola

ያለግጭት ሕልውና የሌለው ወያኔ ዳግም ወደወረራ ሊገባ የሚችለው መንግስት በሚመራው ክልል የሚኖረው ሕዝብ ተከፍቶ ሕዝባዊ አመፅ ውስጥ መግባት ሲችል እንዲሁም የኢትዮጵያ ዋናው ምሽግና አለኝታ መከላከያ ሰራዊት ሲዳከም መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም።

ወያኔ አሁን ባለው ሁኔታ የኢትዮጵያ ሰራዊትን በግንባር ጦርነት ለማሸነፍ የሚያስችል ቀርቶ ለቀናት መመከት የሚያስችል የሰው ሃይልም ሆነ የትጥቅ ብልጫ የለውም። የኢትዮጵያን ሰራዊት ቁመና ሊለካካ አይችልም። ወደፊትም። ነገር ግን ጠላት ወያኔ አሁን እያደረገ የሚገኘው የወገንን አቅም በመለየት ቀድሞ በዘረጋው መዋቅራዊ ድጋፍ በሐገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች አደራጅቶ ተልዕኮ ሰጥቶ ባሰማራቸው አካላት በኩል በስመ ተቆርቋሪነት እንዲያዳክሙ ማድረግና አገር የማፍረስ እንቅስቃሴው ተስፋ ሰጭ ሆኖ ሲያገኘው ዳግም ወረራ መጀመር ይሆናል። ይህን ለማሳካት መሬት ላይ ካደራጃቸው ሳተላይት ድርጅቶቹ በተጨማሪ ትልቁ ጦርነት የሚካሄደው ሚዲያ ላይ በመሆኑ የሚዲያ hegemony በመውሰድ ሕዝቡን በሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት በተዛባ መረጃ በማደናገርና በማሳሳት የእርስ በርስ ግጭት እንዲፈጠር ኢትዮጵያዊያን አንድ ሆነው እንዳይቆሙ የሚያደርጉ ስራዎችን ትኩረት ሰጥቶ መስራት ነው። የድካሙን ልክ ላሰበው ጊዜ ሆኖለታል ካልሆነ በስተቀር በዚህ በኩል ቀላል የማይባል ስኬቶችን እያየ ይገኛል።

እንደጠላት በሚቆጥሩ አካላት ጭምር ሁሉ አላማው ተሽጦ የዕለት ተዕለት አጀንዳ ሁሉ መሆን ችሏል።

ከሰሞኑ ደግሞ አገር ለማፍረስ እንቅፋት የሆነበትንና ለራሱ ስጋት የፈጠረበትን ጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን በተለመደው ነጥሎ ጀኔራሎችን ስም የማጥፋት ዘመቻ እያደረገ የሰነበት ሲሆን አሁን ደግሞ መከላከያ ሰራዊቱን በጅምላ ስሙን ወደማጥፋት ተሸጋግሯል። ኢትዮጵያን ማፍረስ የሚቻለው መከላከያ ሰራዊቱን ማዳከምና ማፍረስ ከተቻለ ብቻ ነው። የወያኔ ጀኔራሎች ሌሎችም የወያኔ ሰዎች ከዓመት በፊት አንዱ አላማቸው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን ማደከም ስለመሆኑ ደጋግመው ተናግረውታል። የኢትዮጵያ ዋልታና ማገር የሆነው መከላከያ ሰራዊት አሁን ባለበት ቁመና ሆኖ ጠላት ወያኔ አገር ማፍረስ ቀርቶ ባለፈው የደገመውን የመድገም ቁመናና ዕድል ማግኘት አይችልም።

ለዛም ነው ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከ ጀኔራሎች መካከል ነጥሎ ስማቸውን በመጥቀስ አሁን ደግሞ ሰራዊቱን እንዳለ የስም ማጥፋት ዘመቻ በመክፈት በደም መስዋዕትነት በሕዝቡ ያገኙትን ክብርና ፍቅር ለመሸርሸርና ሕዝቡ ጀጀን እንዳይሆን ብቻ ሳይሆን በጠላትነት እንዲነሳ ለማድረግ አልሞና ቀምሮ አጀንዳ ቀርፆ እያሰራጨ የሚገኘው። ወታደሩ በአንድነት እንዳይቆም እንዳይተማመን አንድያ ሕይወቱን እየገበረ ጠላትን እያሸበረ በሴራ አለ ሴራ መስዋዕትነቱን ለማርከስ እየተሞከረ ያለው ሙከራ የሚናቅና በቀላሉ ሊታለፍ የሚገባው ነው ብዬ አላስብም። ከዚህ በላይ ጠላትነት የለም።

የኢትዮጵያ የሕልውናዋ የመጨረሻ ምሽግና አለኝታ የሆነን ጀግና መከላከያ ሰራዊታችንን ማንም ያለ ስሙ ስም እየሰጠ የወደፊት የሰራዊቱን የመዋጋት ሞራል ለመስበር፣ አንድነቱን ለማላላትና ለማዳከም የሚያደርገውን የተጠና የጠላት ፕሮፖጋንዳ የሚያራግቡ አካላትን መንግስት አደብ የማሲያዝና አገር የመጠበቅ ግዴታ አለበት። ማንም እየተነሳ መከላከያ ላይ የጠላትን አላማ በሚያሰራጭ አካል ላይ እርምጃ መውሰድ የማይችል ከሆነ የሰራዊቱ ጠላት ማንም ሳይሆን ራሱ መንግስት ይሆናል።

በመከላከያ ሰራዊታችን ላይ ምላሱን የሚያሾል ባንዳና የባንዳ ባንዳ ላይ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ግድ ነው። መከላከያም እነዚህ አካላት ላይ ዝምታውን ያቁም። መከላከያን መንካት አደገኛ ወንጀል ነውና

በጦር ግንባር በዋና ጠላት ፊት ለፊት ያልተንበረከከን የኢትዮጵያን አለኝታ ሰራዊትን የባንዳ ባንዳዎች በስመ የሕዝብ ተቆርቋሪት ከጀርባ በኩል እንዲወጉትና እንዲያጠቁት ሊመቻች አይገባም።

የሰራዊቱን በደም የገኘ ጀግንነት ሕዝባዊ ክብርና ፍቅር ማንም ሐሳብን በነፃነት በመግለፅ ስም ወይም በስመ የሕዝብ ተቆርቋሪነት ሊያራክሰውና ሊያጎድፈው ሊፈቀድለት አይገባም።

በየትኛውስ አገር ነው የአገሩን ሉዓላዊነትና ነፃነት ለማስጠበቅ የሕዝቡን ዘላቂ ሰላምና ጥቅም ለማስከበር ያለ እረፍት በሐሩርና በቁሩ እያለፈ ዳገቱን እየወጣ ቆልቁለቱን እየወረደ ጋራ ሸንተረሩን እያቋረጠ የሚጠብቀውን ጋሻ ሰራዊት መንግስት ባለበት ሁኔታ ማንም አካል እየተነሳ በነፃነት ደረቱን ነፍቶ በአደባባይ ስሙን የሚያጠፋበት እድል ማግኘት የሚችለው?

ባለፈው ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ጦርነቱን ስትጀምር የመከላከያ ሰራዊቷ ላይ ስም ለማጥፋት በሚሞክር የትኛውም አካል ላይ እስከ 15 ዓመት በሚያስቀጣ እስር እንደሚጠብቀው ያወጀችው። የማንም አገር መንግስትም ሰራዊቱን አያስፈቅድም።

አበው “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው!” ይላሉና በጀግናው ሰራዊታችን ላይ የሚነዛውን አሉባልታ ከወዲሁ መንግስት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ በባንዳ ባንዳዎች ላይ እርምጃ ሊወስድ ይገባዋል‼️

መከላከያ ሰራዊትም ራሱን ለማስከበር በጠላት-ተላላኪዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ ሊወስድ ይገባዋል‼️

Leave a Reply