በኦሮሞ ስም በጅምላ ጭፍጨፋ ለማካሄድ የሚያበቃ ምድራዊ ምክንያት የለም!!

አቋማችን

በቁጥር አንጣላም። መቶ ….. ሶስት መቶ …. አራት መቶ …. ሰባት መቶ …. እስካሁን ያለው ሲደመር ቤት ትክክለኛውን ቁጥር ይቁጠረውና ንጹሃን የአማራ ተወላጆች አልቀዋል። እልቂታቸው ዘግናኝ ነው። አማራ ያልሞተው ዓይነት ሞት የለም። ላለፉት ሰላሳ ዓመታት አማራ በተጠና ፍረጃ ” ነፍጠኛ” ተብሎ ተዘርዝሮ የማያውቅ በደል ደርሶበታል። የህዝቡ ቁጥር ሳይቀር በፖሊሲ ደረጃ እንዲወርድ ተደርጓል። እንዳይወልድ ሆኗል። ይህ ሁሉ መከራ ለአማራ ህዝብ ለምን?

ኦሮሞ በቋንቋው የመስራትና የመማር፣ ብሎም የመዳኘት፣ ራስን በራስ የማስተዳደር፣ በፌደራል ደረጃ አብዛኛ ቁጥር ስላለው ተመጣጣኝ ስልታን ሲጠይቅ ነበር። ይህን ጥያቄውን ማንሳቱ ሃጢአት ሆኖ መከራ ሲበላ፣ ሲታሰር፣ ሲገደለና “ጠባብ” ተብሎ ተፈርጆ ሲነገላታ ነበር። ዛሬ ያ ታሪክ የለም። በዚህም መነሻ በኦሮሞ ሕዝብ ስም ጠብመንጃ ይዞ ሰላማዊ ዜጎችን በጅምላ ለመጨፍጨፍ አንዳችም ምድራዊ ምክንያት የውም። የስልጣን ጥያቄ እንዳለ ይታወቃል። የስልጣን ጥያቄን ለማሳካት ግን በኦሮሞ ሰላማዊ ህዝብ ስም ሌሎችን በዘራቸው መርጦ ማረድ ፍጹም አውሬነት ነው። ለስልጣንም አያበቃም። ነገ ሌላ ዋጋ ያስከፍላል። ወደማይቆመው ደም መቃባት ያሸጋግርና ሌሎች ምስኪኖች እንዲያልቁ ምክንያት ይሆናል። ይህን አያምጣው!!

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ሰኔ 1/2014 ዓ.ም ጊምቢ ወረዳ ባሉ ቀበሌዎች የኦነግ ሸኔ ሃይሎች የጅምላ ጭፍጨፋ ማካሄዳቸውን የተረፉ ምስክሮች ተናግረዋል። ከጭፍጨፋው ከተረፉት በላይ ምስክር የለምና ማንም ምንም ቢል ማመን ቀርቶ ለአፍታም ጆሮ የሚያውስ አካል የለም። ይህ አሳዛኝ፣ መኖርን የሚፈታተን ዜና ከተሰማ ጀምሮ ተቆርቋሪዎች ነን ፣ ልዩ አሳቢ ነን የምትሉ፣ ሰው የሆናችሁ መላው ኢትዮጵያዊያን … የደም ፖለቲካ ከሚቆምሩ ለምድ ለባሾች በስተቀር ሃዘን ላይ ነን። ከሃዘኑ በሁዋላ ምን ይሁን?

ከ450 ያላነሱ የአኝዋክ ወገኖቻችን በአንድ ቀን መታረዳቸውን አንርሳ። በበደኖ ኡንቁፍቱ ገደል የሰው ልጆች ከነነብሳቸው መገደላቸውን አንርሳ፤ በደደር ሰዎች መታረዳቸውን አንዘንጋ። ሌሎች አካባቢዎችም በተመሳሳይ የሰው ልጆች ተሰይፈዋል። ይህ ሁሉ የሆነው ደግሞ ዘርን መሰረት በማድረግ ነበር። ዛሬም ያው ድራማ እንደቀጠለ ነው።

ኢትዮጵያ ከዚህ አዙሪት እንዴት ትውጣ? ምን ቢደረግ ይሻላል? አማራው እስከመቼ እየታረደ ይቀጥላል? የፖለቲከኞች የደም ቁማርና የንጹሃንን ነብስ ለመብላት የሚማማሉት እስከ መቼ ነው? ህዝብስ ስለም “በስሜ አትግደሉ፣ ለልጅ ልጆቼ ቂምና ጥቁር ጠባሳ አታስቀምጡ” ሲል አይሟገትም። ሆ ብሎ አይነሳም?

ከተራ መንተክተክ፣ ከማይረባ የፖለቲካ ንግድና ዝናና ሽቀላ ይልቅ ረጋ ብሎ ከላይ የተነሱትን ጉዳዮች ማሰቡ የውቅቱ ብልሃት ይመስለናል። ሁሉም አልቃሽ ከሆነ የመፍትሄ ድምጾች ይዋጣሉ። ለቅሶን በማቆም ይህን መረን የለቀቀ ወንጀል እንዴት ማስቆም እንደሚገባ ህግን ጠብቆ መንደፍ ግድ ይላል።

የኦሮሚያ ክልል መንግስት የተለያዩ ሃላፊዎች እንደ መንግስት ሃላፊነታቸው ዛሬ ለደረሰው ግፍ በጥፋታቸው ልክ ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል። ከመንግስት አልፎ ዞን፣ ከዞን አልፎ ወረዳ፣ ከወረዳ ዝቅ ሲል ቀበሌዎቹ በተዋረድ በህግ ወረንጦ መዳነት አለባቸው። ይህ ውሎ ሳያድር ለህዝብ በግልጽ ሊነገር ይገባል።

ከዚህ ጎን ለጎን በአካባቢው በቋሚነት የአገር መከላከያ ሃይላችን ሊሰፍርና እንደለመደው ክንዱን በክፉዋች ላይ እያነሳ ዜጎችን ከተመሳሳይ ጥቃት ሊጠብቅ፣ ከዛው ጎን ለጎን ህዝቡ ራሱን አደራጅቶና ታጥቆ በራሱ አደረጃጀት ማናቸውንም በትር እንዲመከት ሊደረግ ይገባል። የእሳካሁን ይበቃል። ከዚህ በላይ ህዝብ መታገስ በቃ ሊል ይችላልና!!

እናንት በጋምቤላና በወለጋ የተጨፍቸፋችሁ ምስኪን ዜጎች አምላክ ምህረቱን ያብዛላችሁ። ለስልጣንና ስልጣን ይዞ ለመዝረፍ በንጹሃን ደም አመጽ ለማቀጣጠል የምትተጉ የደም ነጋዴዎች በይትኛውም መመዘኛ ሃጢያታችሁን ማቅለል እንደማትችሉ ተረዱ። ዛሬ በኦሮሞ ስም ንጹሃንን ለመቸፍጨፍ የሚያበቃ አንዳችም ምድራዊ ምክንያት የለምና አቁሙ!! ነብስ ይማር

You may also like...

Leave a Reply