መከላከያን አለማመን የአገር ክህደት ነው! በአጥንት ካባ ህዝብ አታጋድሉ!

የፈረደበት ምስኪኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዴትና መቼ ሰላም ያገኛል? ቢባል መልሱ ግራ ነው። አንዱ ሴራ፣ መከራ፣ ችግር፣ ቀውስ፣ በሽታ፣ ትርምስ፣ ጦርነት ወዘተ ሲታለፍ ሌላ ይጥነሰሳል።ይጸነሳል። ይወለዳል። ያድግና ይረጫል። ቀውስ በልዩ ትዕዛዝ የታተመብን ይመስል ሰላም የሚያጥወለውላቸው ሳያሰልሱ ክፋትን እየቆፈሩ ህዝብን በቁጣ ስሜት ይከቱታል። ” ጊዜው አሁን ነው” በማለት ህዝብን በአጥንቱ እየለዩ በደም ባህር ከተው ወደ ሚፈልጉት ስልጣን ይዋኙበታል። ይሳዝናል። ያማል። አንዳንዴም መፈጠርን ያስጠላል።

አንድ ግልጽ ያልሆነ ጉዳይ አለ። ለምን ወደ አንድ ዕዝ መግባት፣ ለምን በአንድ የዕዝ ተዋረድ መመራት፣ ለምን ከአንድ ዕዝ መዋቅር ውስጥ መካተት ያስፈራል? በተቃራኒው በአንድ ዕዝ ስር ሲኮን ትዕዛዝ ሰጪ ይኖራል። እንደልብ ሜዳ ላይ ጥይት መርጨትና እንደፈልጉ መሰማራት አይኖርም። እንግዲህ በህገመንግስቱ በተቀመጠውና ህዝብ ሲጠይቅ፣ መንግስትም ሲወቀስበት የቆየውን ጉዳይ ጊዜው ደርሶ ሊያስተካክል ሲል ተቃውሞው የተነሳው ለምን ይሆን? እርግጥ ካሁን በሁዋላ ትህነግ የአማራ ህዝብ ስጋት ይሆናል? ዳግም ዱቄት ወዳደረገው ጦርነት ይመለሳል?

ይህን የምንለው አሁን በተነሳው ትርምስ መነሻ ቢሆንም ፋይሉ የተቀዳው ካሳለፍነው ውስብስብ ፈተና ነው። መንግስት፣ ተቃዋሚ የሚባሉ አካላት፣ ራሳቸውን “ተንታኝ” ያሉ አንቂዎች፣ ለትርምስ የተፈለፈሉ ሚዲያዎች፣ የማህበራዊ ገጽ … ሳንል በደፈናው “ምን እየሆነ ነው?” ብንል መልሱ ግራ ነው።

ከቅርብ ጊዜው የሃይማኖት ሽፋን የነበረው ትርምስና ለሃይማኖቱ “እኔ ብቻ ዋና ባለቤት ነኝ” የሚለው ትርክት ሲቋጭ የታዘብነው ሁሉ አሳፋሪ እንድነበር መካካድ አይቻልም። ህዝብን ” ቀኖና ቤተመቅደስህ ተደፈረ” ብለው ወደ እሳት ሲመሩት የነበሩ ሁሉ፣ የችግሩን ምንጭ ከራሳቸው ሲሰሙ ከስረዋል። ምክንያቱም ጸቡ ስልጣን፣ ትልቅ ገቢ ያለበት ደብር የመመደብ ሙስና፣ የበጀት ጥያቄ፣ የማዕረግና የጠቅላይነት ግብግብ እንደነበር ነገሩን። መስቀል ተሸክመው የሚያገለግሉ ካድሬዎች እንደሆኑ አየን። ቤተ እምነት የትኛው የውድቀት አረንቋ ውስጥ እደገባች ተረዳን። ለምደባ አንድ ሚሊዮን ጉቦ የሚቀበሉ ካህናት በምድር አስረው በሰማይ የሚፈቱ … እጅግ ልብ የሚሰብር …

የአንዱን ሰፈር አነሳን እንጂ ራሳቸውን ” ነብይ ” እያሉ በቡድን በመደራጀት ህዝብን በአደባባይ ኪስ የሚያወልቁ ማጅራት መቺዎች፣ የመስጂድ መሪዎች ኢትዮጵያን ሞልተዋታል። እዛም እዚህም ምዕመኑ እንጂ መሪዎቹ መንፈሳዊነት አይታይባቸውም። አብዛኞቹ በቁማቸው የሰቡ ሙቶች ናቸው።

ካድሬዎችም ቢሆን እከሌ ከእከሌ ሳይባል አብዣኞቹ ሆዳሞች፣ ህሊናቸው የተሰወረባቸው፣ የሴራ አራጋቢዎች፣ ከድሃ አጥንት ላይ የሚግጡት ሳያንሳቸው፣ በአጥንት እየመደቡ ደሙን የሚጠጡ ናቸው። ጥቂት መልካሞች ከሆኑት በቀር የሚታየው ሁሉ አንገት የሚያስደፋ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ የሚሳዝነው ሌቦቹ ጥቂት የሚባሉትን መልካሞች በማሸማቀቁ ስራ ተባባሪ ሆነው አገር የማንፈሩን ስራ ማገዛቸው ነው። ለምን ቢባል፣ አገር ሲረጋ እነሱ ይናጣሉና!!ይህን የምንለው በድፍረት ነው። ብዙ የምናውቀው ጉዳይ ስላለ ነው። ህዝብም አይስተውም።

See also  አማራ " የሰውነት ውሃ ልክ" ሲመሳሰል " ወርቅ ሕዝብ"

በ1997 ምርጫ አቅላቸውን የሳቱን “ፓርላማ ከገባችሁ ዋ” በሚል ዘመቻ ያንን ታሪካዊ ምርጫ በዜሮ ያባዙ ሚዲያዎች በአብዛኛው እዛው የድንዛዜና የቀውስ ደውላቸው ስር መገኘታቸው ደግሞ ችግሩን ሁሉ ያጎላዋል። ምንም ሳንደባበቅ ካየነው በወቅቱ አንዱ ሌላውን የሚበላበት ሚዲያ ላይ አለቃና ታማኝ ሆነው ሲሰሩ የነበሩ አሁን ድረስ ከዚያ ችካላቸው አልተነቃነቁም።

ልብ እንበል። ዛሬ መንግስት ጥፋት ቢኖርበትም ቅንጣት ታክል በጎ ነገር እንደሌለው እየተቀባበሉ ሃያ አራት ሰዓት ሳያሰልሱ ክፋትና ህዝብን ቁጣው ውስጥ የሚከት ዜና የሚያሰሙት ለውጡ ላይ አበባ የተበረከተላቸው። ከለውጡም በሁዋላ እስከ ቅርብ ጊዜ በታላላቅ የአገሪቱ ተቋማት ውስጥ እንዳሻቸው ሲወጡና ሲገቡ በፊልም ሲያሳዩን የነበሩ መሆናቸው ” ምን ሆነው ነው? በምን ጉዳይ አኩርፈው ነው?” ቀኝ ኋላ ያሉት የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ይገባል። ይህን ስልንል አቋማቸውን በሚዛናቸው ያደረጉ የሉም ለማለት አይደለም። አሉ!!

የሚዲያው ብቻ ሳይሆን አፈድፋጆቹም እንደዚሁ። “ሌጋባው በየነ” የሚል መመሪያ ሲሰጡ የነበሩትን ጨምሮ ይህ መንግስት ከሞት መንጋጋ ያወጣቸው ዛሬ የአደባባይ ተሳዳቢ ሆነው አቅላቸውን የሳቱት ምን ሆነው ነው? እንዴትስ በዚህ ደረጃ ወርደው እንደ መንደር ኮማሪ ሚዲያ ሳይመርጡ ተራ ስድብ ውስጥ ይገባሉ? ምንድን ፈልገው ተጠግተው፣ ምንድን ስለተከለከሉ ነው? ማለቂያ ስለሌለው እናቁመው።

የፖለቲካ ፓርቲዎችና ውስን መሪዎቻቸው ምንድን ነው እያራገቡ ያሉት? “በአንድ እጅህ ..” እያሉ “አራት ኪሎ ግባ” የሚል ጥሪ የሚያሰሙ አንቱዎች ዓላማቸው ምንድን ነው? የሚሉት ወይም የሚመኙት እንዴት ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ጭራሽ ያሰሉት አይመስልም። እውነት እናንገር ካልን ኢትዮጵያ ውስጥ የውሳኔና የባለቤትነት ድርሻቸው እኩል የሆነ ዜጎች፣ ክልሎች፣ አስተዳደሮችና የህሊና መብት ባለቤቶች መኖራቸው የተካደ ሁሉ ይመስላል።

መንግስትን አፍንጫውን ይዞ ማረቅ፣ መታገል አግባብ ነው። ሚዛናዊ ሆኖኖና ከጅምላ ስድብ በመራቅ ታግሎ ማታገል የሚደነቅ ነው። መልካሙን በማድነቅ አገርን በሚጠቅም መልኩ መንግስትን መፈተን ህዝብን ተጠቃሚ ስለሚያደርግ ይደገፋል። “ስልጣን ለመያዝ ይጠቅመኛል” በሚል እሳቤ ተቃውሞን ትርምስ ለመፍጠር በሚያመች ቅኝት አጥንት እየቆጠሩ ማቀጣጠል ግን ምስኪን ዜጎችን ከመጉዳቱ ውጭ ጥቅም አያስገኝም።

See also  ፖለቲከኞችና መሸተኞች ከዕምነት ሰፈር ውጡ፤ ሕዝብም ፖለቲካና ዕምነትህን ለይ!

በቅርቡ በተካሄደው የህግና የሉዓላዊንት ማስከበር ዘመቻ ከየክልሉ ወደ ሰሜን የአገሪቱ ክፍል የዘመቱ ወገኖች፣ የዘመቱት ለአማራ ክልል ድጋፍ ለመስጠት ሳይሆን ለመላዋ አገራቸው ሲሉ ነው። ድጀኑም ሆነ መለዮ ለባሹ ሁሉም የአገሪቱ ክልል አገሩ ስለሆነ ነው። የአናት አገሩም ግዴታና ውዴታ ስላለበት ነው። የትግራይ ህዝብንም የማዳን ተልዕኮም ስላላቸው ነው። አድርገውታል። ይህ ሲባል የአማራ ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻ፣ ህዝብ ልዩ ሚና የለውም ለማለት ሳይሆን መከላከያ ማለት ከአመራር ጀምሮ አማራም ያለበት፣ ትግሬ፣ሲዳማ፣ ቤኒሻንጉል፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሞ፣ አፋር… ያሉበት በመሆኑ ነው።

ይህን ያልነው ሁሉም ክልሎች በአገሪቱ ህገመንግስታዊ የጸጥታ መዋቅር ለመደራጀት ሲስማሙ አማራ ክልልም ተቀብሎ ሳለ አማራ ክልል ያደራጀው ሃይል ከማን መመሪያ ወስዶ ነው ውሳኔውን አልቀበልም በሚል እዚህ ውጥንቅጥ ውስጥና “ይህ ይደረግ፣ ይህ ካልተደረገ” የሚል አዛዥና ናዛሽ ሊበዛ የቻለው? የሚለው ግራ የሚያጋባ ጉዳይ መልስ ስለሚያስፈልገው ነው።

ይህ አሁን እየታየ ያለው አደገኛ አዝማሚያ ባስቸኳይ ሊቆም ይገባል። የክልል ፌደራል ሃይሎች መፍረስ የቆየ የህዝብና የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄ ነው። ዛሬ ኮንትሮባንድ፣ በየጫካው ተመሽጎ ህዝብ መዝረፍ፣ መግደልና ክልል አቋርጦ በመሄድ የማይጮህላቸውን ዜጎች ማውደም ገደቡን አልፏል። በኮንትሮባንድ ያበዱ፣ አደባባይ ብቅ እያሉ ፈራንካ በመርጨት ሚዲያ የሚያጯጩሁ ከዚህ ድርጊት ጀርባ ስለመኖራቸው ጥርጥር የለምና ህዝብ ንቃ!!

አፈሳጸም ላይ ችግር ካለ መወያየት፣ የማስተካከያ እርምት መውሰድ እንጂ እንደ ትህነግ ልብ አሳብጦ ወደ ለየለት ግጭት መግባት ሲጀመር አሸናፊ አይደርግም። ሲቀጥል አውዳሚ ነው። ከዚያም ሲያልፍ ከሌሎች ጋር ያለ ግንኙነትን ያበላሻል። በውጤቱም በርካታ ሰላማዊ ዜጎች ይጎዳሉ። ይህ ሳይሆን ህግን በማክበር፣ የጎድለን በማስተካከል፣ በመመካከር ወደ ቀናው መንገድ መመለስ ” ጊዜው አሁን ነው” ከሚል ስሜት መታቀብ ያዋጣል።

ሰፊው የአማራ ህዝብ በሄደበት ሁሉ ታትሮ የሚሰራ፣ ከሚኖርበት ህዝብ ጋር የተዋሃደ፣ ሁሉም አገሩ የሆነ፣ በተለየ አምኖ፣ በተለየ የሚጠረጥረው ወገን የሌለው ነውና አትበርዙት። በስሙ እየማላችሁ በሰላም ከሚኖርበት ሰፈር ድረስ ችግር አታዋልዱለት። “መከላከያን አላምንም፣ ልዩ ሃይልን ነው የምፈልገው” ማለት ለዛሬ ፉከራ ቢሆንም አድሮ ጣጣው ብዙ፣ የአገርም ክህደት ነውና እናስብ። መከላከያ ክህደት ሲፈጸምበት ያነባነው “መከላከያችን ነው” ብለን እምነት የምንጥልበት የመንፈስ አብራካችን ስለሆነ ነው። ልዩ ሃይል ከክልል አልፎ የሁላችንም አብራክ ወደሆነው ተቋም ቢገባ ማዕረጉም፣ ክብሩም ይሰፋል እንጂ ጉዳት የለውም። ምኑ ቅሬታ እንዳስነሳ የማይገባንም ለዚህ ነው።

See also  በኦሮሚያ ለሚገደሉ ዜጎች የፖለቲካ ቁማርና የሴራ ትንተና ፋይዳ የለውም!!

በየከተማው መንገድ ዘግቶ ” መከላከያ ተቆርጦ እዚህ ቦታ ላይ ብቻውን ነው” የሚባለው ዜና ዛሬ ለጊዚያዊ ትርምስ ካልሆነ በቀር በፍጹም አሸናፊ እንደማያደርግ እንረዳ። ትናንት “መከላከያን በክህደት አረዱ” በሚል ህዝብ የተነሳባቸው የትህነግ አመራሮችና ወራሪዎችም በድል አድራጊነት ሲጨፍሩ እንደነበር አንዘንጋ። የቅርብ ወዳጆቻችን ሳይቀሩ የዛሬን ሳያስቡ ሲዛበቱብን ነበር። ይህ ታሪክ እንዲደገም አያስፈልግም።

ለትርምሱ ግብዓት እንዲሆን በሚል የመሬት ወረራን ማሞካሸት፣ ህገወጥነትን በጅምላው የበደል ስር አድርጎ ማቅረብ አይጠቅምም። ህጋዊ የሆኑ አካላት በህገወጦች ላይ እርምጃ ሲወሰድ ተነክተው ከሆነ በወጎ መረጃ አቅርቦ ማጋለጥ፣ መሟገትና ፍትህን መጠይቅ እጅግ ድንቅ የሚባል ወገናዊነት መሆኑ አያጠራጥርም። ነገር ግን ለፖለቲካ ገበያ ሲባል ህዝብን ቁጣ ውስጥ የሚከት ዘመቻ ማካሄድ ያከማቹት ቁጣ የገነፈለ እለት “አቁሙ” የሚል ያሳጣል እንጂ የሚፈለገውን ለውጥ አያስገኝም።

በጥቅሉ አሁን በተጀመረው የልዩ ሃይሎችን መልሶ በህግ አግባብ በተቀመጠ አደረጃጀት የማካተት ስራ ሲጀመር ሁሉም ክልሎች እንዳሉት ” ትጥቅ ማስፈታት” አይደለም። ትጥቅ ማስፈታት የሚለው አባባል ለምን አማራ ክልል እንደተፈበረከ ግልጽ ማብራሪያ የሚሰጥ አካል የለም። ስለዚህ ትጥቅ ማስፈታት የሚለው ገለጻ በትክክለኛ ስሙ በመጥራት የተጓድለ ነገር ካለና ስጋት የሚያስነሳ ጉዳይን ዘርዝሮ ሌሎችን ባማያስቀይምና ትግራይን ጨምሮ ” እኛም ትጥቅ አንፈታም” የሚል ጥያቄ እንዳይስነሳ ጥንቃቄ ተወስዶ መፍትሄ ይበጅለት ለማለት እንወዳለን። ከዚህ ውጭ “ሌሎች ይፍቱ፣ እኛ ትጥቅ አንፈታም። የአማራ ልዩ ሃይል እንጂ መከላከያን አናምንም” የሚለው ጨዋታ በኢትዮጵያ ጥላ ስር የሚያስኬድ አይመስለንም። አለያ የሚድበሰበስ ጉዳይ ሊኖር አይገባምና ምን እንደተፈለገ ግልጽ ይሁን።

ጉዳዩ የክልል ልዩ ሃይል የሚባለውን መዋቅር ማክሰም ሆኖ ሳለ ” ለምን ሸገር ዙሪያ ከተማ ተቋቋም” በሚል ሌሎችን መነካካት ደግመን እንላለን አክሳሪ ነው። መንገድ ዘግቶ አገልግሎት ማስተጓጎል ቅድሚያ የሚጎዳው የአማራን ህዝብና የክልሉን ኢኮኖሚ ነው። ነዳጁም፣ መድሃኒቱም፣ ማዳበሪያውም፣ የውጭ ንግዱም በጅቡቲ ይቀጥላል። ይህ ያልተጠና አድማ ዜና ካምጯጯህ ውጪ አማራን ይጎዳው ካልሆነ በቀር አይተቅመውምና ይታሰበበት። የጎደለና የተዛባ ነገርን ህዝብ ሳይጎዳና ሌሎችም ሳያኮርፉ መጠየቅ ሲገባ በዚህ መልኩ ወደ ቀውስ ማምራቱ የነገ ሃዘን ነው። የነገ አብሮነትንም ይንዳል። እንደወትሮው ሁሉ መከላከያችንን ማመን ግድ ነው!!

Leave a Reply