የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ኢኮኖሚ ከማድቀቅና ህዝቡን ከማሰቃየት ውጭ የሚፈታው ጥያቄ የለም

የአማራ ክልልን በኢንቨስትመንትና በኢኮኖሚ ተመራጭ ለማድረግ አመራሩ ጽንፈኝነትና ስርዓት አልበኝነትን በጽናት ሊታገል ይገባል–ዶክተር ይልቃል ከፋለ

የአማራ ክልልን በኢኮኖሚና በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ተመራጭ ለማድረግ በየደረጃው ያለው አመራር ጽንፈኝነትና ስርዓት አልበኝነትን በጽናት መታገል እንዳለበት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አሳሰቡ።

በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታዎችና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የሚመክር የከፍተኛና መካከለኛ አመራር ኮንፍረንስ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት በክልሉም ሆነ እንደአገር ያለው የሥራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ወቅታዊ ተግዳሮቶች እንዲባባሱ መነሻ ሆነዋል።

በክልሉ ለተስተዋለው አለመረጋጋት አባባሽ የሆኑ ችግሮችን ፈጥኖ በማረም የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአመራር አንድነትና ቁርጠኝነትን ማሳደግ እንደሚገባ ገልፀዋል።

አመራሩ የብልጽግና መርሆዎችንና አስተሳሰብን በማስተግበር ክልሉን በኢኮኖሚም ሆነ በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ተመራጭ ለማድረግ ጽንፈኝነትንና ስርዓት አልበኝነትን ታግሎ ማሽነፍ እንዳለበትም አሳስበዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን በክልሉ ያለውን እምቅ የቱሪዝም ሃብት በአግባቡ በማልማትና በማስተዋወቅ አሁን የተከሰተውን የኑሮ ውድነት የሚያረግብ ውጤታማ ስራ መስራት ይገባል ብለዋል።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በህገ-ወጥ መንገድ የሚጠራ አድማና አመጽ ከጉዳት ውጭ እንደማይጠቅም ከህዝቡ ጋር መክሮና ተግባብቶ ማስቆም የአመራሩ ሚና መሆን እንዳለበትም ዶክተር ይልቃል አስገንዝበዋል።

“መንገድ መዝጋት ዜጎች በሕክምና እጦት እንዲሞቱ እንዲሁም ነዳጅ፣ ማዳበሪያና ሸቀጦች ወደ ክልሉ እንዳይገቡ ያደርጋል” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ይህም የክልሉን ኢኮኖሚ ከማድቀቅና ህዝቡን ከማሰቃየት ውጭ የሚያመጣው ውጤትና የሚፈታው ጥያቄ የለም ብለዋል።

“የአማራ ህዝብ ጥያቄዎችን በተለያዩ የፖለቲካ መድረኮችና ጉባኤዎች ላይ በማንሳት እንዲፈቱ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፣ የኮንፍረንሱ ታዳሚዎችም ይሄን በአግባቡ ሊገነዘቡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

“ጽንፈኝነትና ስርአት አልበኝነት መስፋፋት ከሚያስከትለው ዘርፈ ብዙ ጉዳት ውጭ ምንም ጥቅም ስለሌለው ድርጊቱን በቁርጠኝነትና በጋራ መታገል አለብን” ብለዋል።

“የጽንፈኞች ፍላጎት በበሬ ወለደ ፕሮፓጋንዳ የክልሉን ህዝብ ትኩረት ይዘው ከልማት ሥራው ማደናቀፍ ነው” ያሉት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ ዶክተር ጋሻው አወቀ ናቸው።

See also  ባልደራስ "መንግስት ሕዝብን ንቋል" አለ፤ "ራስህ ትህነግን ግጠም "

በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት የተጠናከረ የህዝብ ግንኙነት ሥራ በመስራት የክልሉ ህዝብ ተረጋግቶና ደህንነቱ ተጠብቆ እንዲኖር ማስቻል እንደሚገባ ገልጸዋል።

“ችግሮችን በአግባቡ ተረድቶ ወደ እድል በመቀየር የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ፓርቲ እና መንግስት አለ” ያሉት ዶክተር ጋሻው፣ ለዚህም የሚታገል ቁርጠኛ አመራርና አባል መፍጠር ይገባል ብለዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለአምስት ቀናት እየተካሄደ ባለው ኮንፍረንስ ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በመሳተፍ ላይ መሆናቸው ተመልክቷል።

በኮንፍረንሱ መጀመሪያም በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ለነበሩት አቶ ግርማ የሺጥላና የሥራ ባልደረቦቻቸው የህሊና ጸሎትና የሻማ ማብራት ሥነስርአት ተካሂዷል።

(ኢዜአ)

Leave a Reply