የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ አሁን ባለው የኤምባሲዎች ስርጭት መቀጠል እንደማይቻልና ሰላሳ የሚሆኑት እንደሚዘጉ ከወዲሁ ፍንጭ ሰጡ። አዳዲስ ዲፕሎማቶች ሰልጥነው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን መቀላቀላቸውን ሲናገሩ ኤምባሲዎቹ የሚዘጉት ብክነትን ለማስወገድ በሚል ሲሆን ስራዎች በማዕከል ሊሰሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ከተወካዮች ምክር ቤት ለቀረበላቸው ዲፕሎማሲ ተኮር ጥያቄ ሲመልሱ “ኤምባሲዎች የግል ጉዳይ ማስፈጸሚያ መሆን የለባቸውም” ብለዋል። በመጪው መስከረም የሚመሰረተው መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳያሻሽል እንደቀድሞው አድርጎ ቢያመጣ ተቀባይነት እንደማይኖረው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአውሮፓና አሜሪካ በቂ የሚባል ፈቃደኛ ዲፕሎማቶች ስላላት እዛ ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ” እኔ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሆን የኒውዮርክ ቆንስላ አያስፈልገኝም” ሲሉ እዛ ያሉ አገር ወዳድ፣ ከማባሳደሮች በላይ ብቃት ያላቸውን እንደሚተቆሙ በመግለጽ ቀጣዩን አሰራር አመላክተዋል።
ዲፖሎማሲውን አስመልክቶ አንዳንዶች ጽሁፍ አንብበው ምክር ለመለገስ እንደሚሞክሩ አውስተዋል። ይሁን እንጂ በአብዛኛው በምናውቀው እውነት ሲቀጥፉ በተደጋጋሚ በመታየቱ በማይታወቅና ማሰላሰል በሚያስፈልጉዋቸው ጉዳዮች ለማመን አስቸጋሪ መሆኑንን አንስተዋል።
የውጭ አገር ሚዲያዎችና ዲፕሎማቶ ፊትለፊት በተቀመጡበት ሚድያው አይን ያወጣ ቅጥፈት ማራገቡ እንጂ ብዙም የዲፕሎማሲ ችግር ኖሮ እንዳልሆነ ያወሱት አብይ አሕመድ ” ተመድና አፍሪካ ህብረትን የመሰረትን ዲፕሎማሲውን የምናውቅ ነን። ዲፖሎማሲ ብርቃችን አይደለም” ብለዋል። ልማትና ብልጽግና ብቻ ለኢትዮጵያዊያን ብርቅ በመሆኑ በዚህ መልኩ መርዳት ቢችሉ አግባባ መሆኑንን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ሰላምና ዴሞክራሲ የሚረጋገጠው በሕዝቦቿ ብቻ በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን ሌሎች በሚከፍቱት ቦይ ከመፍሰስ ጥንቃቄ እንዲወሰድ አሳስበዋል። አንዳንድ አገሮች መንግስት እንዲቀየር እንደጠየቁ ጠቁመው ” መንግስት መቀየር የግለሰብ ጉዳይ አይድለም። ተላላኪ መንግስት ማቋቋም አይቻልም” ብለዋል። ለመጨረሻ ጊዜ ማብራሪያቸውን ለሰማቸው ፓርላማ ” እናንተ እድለኞች ናችሁ፤ ቀጣዩ ፓርላማ እዳው ብዙ ነው። ሕዝብ ለሊቱን ሁሉ ቆሞ መርጦታል” ብለዋል። እስካሁን ላበረከቱት ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበው ቀጣዩ ፓርላማ ” እንደዚህ ለሊቱን ወጥቶ ከመረጠ ህዝብ የሚሰርቁ ከሆነ ሞት ይሻላል” ሲሉ በሚያፈስ ቤት እየኖረ፣ መደብ ላይ እየተኛ የመረጣቸውን ሕዝብ በቀናነት ለማገልገል ከወዲሁ እንዲዘጋጁ ጥሪ አቅርበዋል።