ፌስቡክ ላይ በመጻፍ፣ በመዋጋትና በማዋጋት ነጻነታችንን መጠበቅ አንችልም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ


“ፌስቡክ ላይ በመጻፍ፣ በመዋጋትና በማዋጋት ነጻነታችንን መጠበቅ አንችልም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰላም ሚኒስቴር የመጀመሪያ ዙር የበጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት ስልጠና የወሰዱ ከ10 ሺህ በላይ ወጣቶችን በወዳጅነት ፓርክ በይፋ መርቀዋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፤ በአባቶች ደምና አጥንት በነጻነት በቆመች አገር ላይ መሆናችንን መገንዘብና የትናንትን ጠቃሚ ነገር ማስቀጠልን ማስታወስ ያስፈልጋል።

ወጣቱ የተቀበለውን ነገር እንዳለ ማቆየት ሳይሆን ማሻሻል እንዳለበት ገልጸዋል።

ለአብነትም የወዳጅነት ፓርክ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች አንስተው፤ ኢትዮጵያን ያቆዩ አባቶች ስራዎች ሳይዘነጉ ይበልጥ ማሻሻል፣ ማላቅና ማበልጸግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ማረም፣ ማበልጸግና ማላቅን ወጣቱ በልቦናው ማቆየት እንዳለበት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከግራ፣ ከቀኝ፣ ከኋላና ከፊት ለመገመት በሚያዳግት ደረጃ ትልቁም ትንሹም ተረባርቦ የተናሳባት ጊዜ ላይ ትገኛለች” ብለዋል።

የዚህ የውሸት ፕሮፓጋንዳና ጥላቻ ንግግር ዋና ዓላማ ከምዕተ ዓመት በፊት አልገዛም በማለት ለጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተምሳሌት መሆኗን ዛሬም በድህነት ላይ ለመድገም መነሳሳቷ እንደሆነ ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያ ድህነት አያስፈልገኝም ብልጽግናን እሻለሁ፤ መለመን አልፈልግም መስጠትን እመኛለሁ እያለች ነውና ይህችን አገር ካላቆምናትና ካልቀጨናት በስተቀር አሁንም ለጥቁር ህዝቦች አረአያ ትሆናለች የሚል ስጋት በሰፊው ይናፈሳል” ብለዋል።

ትልቅ ትንሹ ቢጮህና ብዙ ውሸት ቢነገር ለጥቁር ህዝቦች ነጻነቷን ጠብቃ አረአያ የሆነችው ኢትዮጵያ ዛሬም በልጆቿ ጥረትና ትብብር ታግዛ የብልጽግና ምሳሌ እንደምትሆን ተናግረዋል።

“ጆሯችሁን፣ ልባችሁን፣ አዕምሯችሁን ጠብቃችሁ ኢትዮጵያን ማላቅ፣ ማበልጸግ፣ መውደድና በክብር መስዋዕት መሆን የኩራት ሁሉ ምንጭ እንደሆነ አውቃችሁ እንድታገለግሉ፣ እንድትጠብቋት፣ እንድታሻግሯት፣ ለሚመጡ ወጣቶች ተስፋ ለአዛውንቶች ደግሞ እንድትሆኑ አደራ” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአገር መከላከያ ሰራዊትና የፌዴራል ፖሊስ ብዙ ወጣቶች እንዲቀላቀሏቸው እንደሚፈልጉ ገልጸው፤ ከቅርብና ከሩቅ ብዙ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚፈልጉ ሃይሎች ስላሉ መጠናከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ብዙ ወጣቶች በሰራዊት ውስጥ ተቀላቅለው ከማገልገል ይልቅ በፌስቡክ እንደሚዋጉና እንደሚያዋጉ ገልጸው፤ “በፌስቡክ ነጻነታችንን መጠበቅ አንችልም፤ ዋጋ ከፍለን ራሳችንን ካልሰጠን በስተቀር በያላችሁበት በምትናገሩትና በምትጽፉት የኢትዮጵያን ህልውና ማስጠበቅ ስለማይቻል በመከላከያና በፖሊስ ሰራዊት ውስጥ ተሳትፈን አገራችንን መጠበቅና ህልውናዋን የሚገዳደሩ ሃይሎች የማይችሉ መሆኑን ማሳየት ያስፈልጋል” ብለዋል።

See also  «ዝግጁ ነኝ» መላኩ ፈንታ

Source/ EBC

Leave a Reply