ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ የተሰጠ መግለጫ

ከብሔራዊ መግባባት መሸሽ ያገራችንን ችግሮች እያባባሰና እያወሳሰበ ነው፡፡

ዛሬ ሀገራችን በቀውስ እየተናጠች ነወ፤ ሠላም የለም፡፡ የአገራችን አንዳንድ ክፍሎች ኮማንድ ፖስት ሥር ይተዳደራሉ፡፡ የሕግ የበላይነት እየተከበረ አይደለም፡፡ ፍርድ ቤት በነፃ ወይም በዋስ የለቀቀውን ፖሊስ ያስራል፡፡ የበለጠ በጣም አሳሳቢው ደግሞ በሕግ ቁጥጥር ሥር የሚገኙ ዜጎች በማን አለብኝነት ከእስር ቤት እያወጡ ያለፍርድ መግደል የተለመደ ሆኗል፡፡ የሆሮ ጉዱሩ ዞን ጂማ ራሬ ወረዳ ነዋሪዎች፤ ባኔ ነገሪ፣ ብርሃኑ ቶለሳ፣ በላይ ጢቂ፣ ጉታ ጫራና፣ ጭምዴሳ ሶቾሳ በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በሌሎች የኦሮምያ አከባቢዎችም ተመሳሳይ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው፡፡

የአገሪቱ ዋና ከተማና አንዳንድ ትልልቅ ከተሞች ውስጥ ዜጎች የሚያስፈልጋቸውን መሠረታዊ አገልግሎችን አንድም ጨርሶ አያገኙም፤ ወይም በበቂ ሁኔታ አያገኙም ወይም ሊከፍሉት ከሚችሉት ዋጋ በላይ ይጠየቃሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ሕወሓት/ኢህአዴግ በመቀጠልም የብልፅግና ፓርቲ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ሲያደርሱ ከቆዩት የመልካም አስተዳደር ጉደለት የተነሳ መሆኑ በማንም የማይታበል ሐቅ ነው፡፡

ፓርቲያችን ኦፌኮ የአገሪቱ ውስብስብ ችግሮች በብሔራዊ መግባባት ይፈቱ ዘንድ ያደረጋቸው እጅግ ብዛት ያላቸው ጥሪዎች እየተደብሰብሰ በመታለፉቸው፤ አገራችን ሊትወጣ ከማትችልበት ሁለንትናዊ መመሰቃቀል ውስጥ ገብታ ትገኛለች፡፡ በአማራ ክልል በኦሮሞ ልዩ ዞን ውስጥ በሕዝብና በመንግስት ልዩ ኃይል መሀከል ሕይወት የጠፋበትና ንብረት የወደመበት እጅግ በጣም ዘግናኝ ግጭት ተከስቷል፡፡ እንዲያውም የኦሮሞ ብሔር ሕዝብን ከኢትዮጵያ በመነጠል ለማንም በማይጠቅም መልኩ “ኦሮሙማ ይውደም! ኢትዮጵያ ትቅድም!” የሚል መፈክር በአማራ ከተሞች በአደባባይ ተስተጋብቷል፡፡ በበኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕዝብን ያፈናቀለ፣ ሕይወትን ያጠፋና ንብረትን ያወደመ ግጭት ተፈጥሯል፡፡ በኦሮምያ ክልል በወለጋና ጉጂ ዞኖች እንዲሁም በሌሎች አከባቢዎች ግጭት በመስፋፋቱ ብዙ ሕይወት እየጠፋ ነው፡፡ ትግራይ ውስጥ ያለው አጠቃላይ ቀውስ ከኛ አልፎ የዓለም መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ እነዚህና ሌሎች ችግሮች እያሉ መንግስት በብሔራዊ መግባባት ያልታጀበና በኛ እምነት ችግሮችን ያባብስ እንደሆነ እንጂ፤ ችግሮችን የማይፈታ ምርጫ እንዲካሄድ እየገፋ ነው፡፡ ኦፌኮ በገዥው ፓርቲ ጫና ከምርጫ ውድድሩ የወጣ ቢሆንም በኃይል ምርጫን ለማስፈጸም ከመሯሯጥ አስቀድሞ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር እንደሚመረጥ አሁን አጥብቀን እንመክራለን፡፡

See also  ኢትዮጵያ "ቁማሩ ይቁም" ስትል አሳሰበች፤ "የትህነግ ጉዳይ ሰለቸን"ዜጎች

አንፃራዊ ሰላም ይታይባታል ከምትባለው ርዕሰ ከተማ ፊንፊኔ/አዲስ አበባን ጨምሮ የመራጮች ምዝገባ ከሚጠበቀው በታች መሆኑ ምርጫው የሕዝቡን ስሜት አለመሳቡን በግልፅ ያመለክታል፡፡ ይህ የምርጫ ትያቲር ዘመን እንዳለፈም የሚያሳይ ምልክትም ነው ብለን እናምናለን፡፡ ሚሊዮኖች የተፈናቀሉበት ዘመን ነው፡፡ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለን ግንኙነት እየሻከረ መጥቷል፡፡ ከዕርዳታ ሰጪና አበዳሪ አገሮች ጋር አገራችን እየገባችበት ያለው አለመግባባት ኋላ ላይ ውድ ዋጋ ሊያስከፍላት የሚችል ይመስለናል፡፡ ዜጎች ቢያንስ የትራንስፖርትና የመሠረታዊ አቅርቦት አገልግሎት ከማያገኙበት ደረጃ ላይ ደርሰው የከተማ ውስጥ ዘራፊዎች መጫዋቻ እስከመሆን ደርሰዋል፡፡ ከነዚህ አስከፊ ችግሮች ለመላቀቅ መፍትኼ መሻት ይኼን ያህል ቀላል ይሆናል ተብሎ ባይገመትም መንግስት ከብሔራዊ መግባባት መሸሹ ሕዝባችንን ለበጠ አደጋ ከማጋለጥ የበለጠ ፋይዳ ያለው አይመስለንም፡፡

ስለሆነም፤ መንግስትና ገዥው ፓርቲ ሁሉንም አቀፍ ያልሆነ ምርጫ ከማካሄድ መጣደፉን አቁመው የዕርቅና ብሔራዊ መግባባት መድረክ እንዲያመቻቹና አገራችን ከተጋረጠባት መመሰቃቀል እንዲትወጣ እንዲያደርጉ አበክረን እየጠየቅን፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሀገሪቱ ዴሞክራሲ ኃይሎችና የዓለም ማህበረሰብ ከገባንበት የፖለቲካ አጣብቂኝ እንድወጣ የየበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንዲታደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)
ፊንፊኔ፤ ሚያዚያ 2013 ዓም

Leave a Reply