የደቡብ ወሎ አስተዳዳሪ የትህነግ ሃይል በሃራ መስመር ጥቃት ለመሰንዘር የመጣበትን ምክንያት ሲጠየቁ ” ምን ይዤ ልመለስ” እንደማለት መሆኑንን አመልክተዋል። አስተዳዳሪው ይህን ያሉት ሃይሉ እየተመታ መሆኑና ያሰበው እንደማይሳካ ለማስታወቅ ነው። በሌላ በኩል ሕዝብን እያስገረመ ያለው የትህነግ ሰራዊት እየተመታ ከያዛቸው ቦታዎች መልቀቁ ሳይሆን፣ “ይህን ሁሉ አካባቢ እንዴት ወረረ?” የሚለው ሆኗል።

ደቡብና ሰሜን ጎንደርን፣ ደቡብና ሰሜን ወሎን፣ አፋርን በከፊል የወረረው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር የሰው ማዕበል በማጉረፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰፊ ወረራ ፈጽሟል። ይህ ሃይል በመከላከል ተመክቶ ዛሬ ላይ በመልሶ ማጥቃት አብዛኛዎቹን አካባቢዎች እንዲለቅ መደረጉን አርሶ አደሮች የደረሰባቸውን በደል እያወጉ ምስክር ሆነዋል። የመንግስትና የመከላከያ፣ እንዲሁም የክልሉ መንግስት ይፋ እያደረጉ ነው።

ትህነግ የወረራቸውን አካባቢዎች መልቀቅ ብቻ ሳይሆን የደረሰበት ኪሳራና የገበረው የሰው ሕይወትም እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ከየግንባሩ የሚወጣው መረጃ እያሳየ ነው። ደጋፊዎቹና አመራሮቹም ቢሆኑ ሲወሩ ያሰሙት እንደነበረው አይነት ድምጽና ፉከራ እያሰሙ አይደለም። ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸውም ቢሆኑ እንደወትሮው አዲስ አበባ ለመግባት ቀጠሮ፣ ባህር ዳር፣ ጎንደርና፣ ደብረብርሃን ለመድረስ መንገድ ሲያማርጡ አይታዩም።

“ያሻንን ከማድረግ የሚያቆመን ምድራዊ ሃይል የለም” ሲሉ የነበሩት አቶ ጌታቸው ሰራዊታቸው በወረራ በቆየባቸው ቦታዎች ያሳይ የነበረው ባህሪ ተራ፣ የቆሸሸ፣ አሳፋሪ፣ አሳዛኝ፣ የተልከሰከሰ፣ ወራዳ፣ምጣድና ቡሃቃ ስር የሚነደባለል፣ ጠኔ የፈጀው፣ ቸነፈር ያጠቃው፣ በደም ያበደ… መሆኑ የታየበት ነው። ይህን እውነት ያረጋገጡት ካድሬዎች፣ ባለስልጣናት ወይም አፈ ጮሌዎች ሳይሆኑ ምስኪኑ አርሶ አደር፣ የአርሶ አደር ቤተሰቦችና የምስል ማስረጃዎች ናቸው። ገና ብዙ መረጃ ይወጣል።

“ጦርነቱን ሕዝባዊ አድርገነዋል” ያለው ትህነግ አብሮት አድጎ ባደቀቀው የአስተሳሰብ ልምሻ ሌሎች ሕዝባዊ ሃይል እንደሚያደራጁ ሊገምት አቅም አልነበረውም። እሱ ከገነባው በላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ በተቆጡ ልጆቿ ወዶ ዘማችነት ተጥለቀለቀች። ትህነግ ያወደመው ህብረት፣ በትህነግ ጎትጓችነት ኢትዮጵያን ከዳር እስከዳር አያያዘ። ደጀኑ፣ ግንባር ያለውና ወደ ግንባር ሊሄድ የሚዘጋጀው፣ ከዛም አልፎ “ልዝመት” የሚለው ሃይል አንድ ላይ የትህነግ ሃይልን ፊኛ ይዘው። አሁን ትህነግ ፊኛው ተያዞ እየተንፈራገጠ ነው።

ሰሞኑንን እንደተሰማው ከያዛቸው አካባቢዎችና ገዢ መሬቶች የተጠረገው የትህነግ ጭፍራ፣ እድሜ ለትግራይ እናት ማህጸን ከፊት ያለው ሲረግፍ ከሁዋላ እየተካ ዘልቋል። በከሃዲነቱ ወደር የሌለው ይህ ደም ግብሩ የሆነ የሽፍታ ቡድን መልኩን ቀይሮ አቅጣጫ እየቀያየር ጥቃት መፈጸምን ተያይዞታል። ደብረ ዘቢጥ ላይ ተደቁሶ የተረፈው ሃይል ቁልቁል ከሸሸ በሁዋላ በዚህች ሶስት ቀናት ከሱዳን በሰረጉ ሃይሎቹ፣ በደቡብ ጎነደርና ደቡብ ወሎ፣ እንዲሁም አፋር በርሃሌ አካባቢ ጥቃት እየሰነዘረ ይገኛል።

በሁሉም ስፍራዎች መመታቱን የየአካባቢው አስተዳዳሪዎች አስታውቀዋል። በሰሜን ጎንደር ደባርቅ ግንባር ሰርዶ የሚባለውና የተሻለ እንደሆነ የሚነገርለት የትህነግ ሰራዊት ከላይ በድሮን፣ ከታች በመከላከያ፣በፋኖና ልዩ ሃይል፣ እንዲሁም በሕዝብ ቁጣ መድቀቁ ተገልጿል። የደባርቅ ነዋሪ ቤተሰቦች እንደነገሩኝ ሕዝብ ተቆጥቷል። ይህን ሃሳብ ለማንሳት ያነሳሳኝም ይኸው ነው። በደቡብ ወሎም ሆነ በአፋር የሆነው ተመሳሳይ ነው። የህዝብ ቁጣ!! ሕዝብ ላይመልስ ተቆጥቷል!!

ቁጣ – ” ምን ይዤ ልመለስ”

አሁን ላይ ትህነግ የተነሳበትን ቁጣ እንዴት ሊያበርደው እንደሚችል ለማንም ግልጽ አይደለም። ግልጽ የሆነለት ካለ የሚለውን ይበል። እኔ እንደገባኝና እንደተረዳሁት፣ በየአቅጣጫው እንደሚነገረው፣ ተወደደም ተጠላም በመሬት ላይ ያለው እውነት የሚያረጋግጠው ትህነግ በኢትዮጵያ ሕዝብ የተተፋ ነው። አሜሪካ በምስራቅ አፍሪቃ የሾመቻቸው ባለማዕረግ ፌልትስ፤ ” ትህነግ ከኢትዮጵያ ህዝብ ልብና ጭንቅላት ውስጥ መውጣቱን እናውቃለን” ሲሉ በዲፕሎማቲክ ቋንቋ መናገራቸው ሃሳቤን የሚያጸናው ይመስለኛል። ምክንያቱም ትህነግ እንዲያንሰራራር የተሾሙ ማሽንክ ከተመደቡበት ልዩ ተልዕኮ አፈንግጠው እንዲህ ያሉት መሬት ላይ ያለው ሃቅ ስለገፋቸው እንጂ በሌላ በምንም ሊሆን አይችልምና።

ከላይ እንዳልኩት ሕዝብ ተቆጥቷል። ቁጣውንም ” ለአገሬ እዘምታለሁ” በሚል እየገለጸ ነው። የኑሮ ውድነቱን፣ ችግሩን፣ አበሳውን … ተቋቁሞ “ትህነግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንንቀል” እያለ እየተመመ ነው። ደጀኑም፣ ሚሊሻውም፣ ልዩ ሃይሉም፣ መክለላከያን እየደገፈ ትህነግን ስለማጥፋት እንጂ ሌላ ወሬ የለውም። አልፎ አልፎ ከሚልከሰከሱ በስተቀር የተያዘው ዓላማ አንድና አንድ ነው። ትህነግን መደምሰስ።

ትህነግ ሲወለድ ጀምሮ ለትግራይ ህዝብ ጠላት እየፈጠረ፣ ሕዝቡ ጠላት አለኝ ብሎ እንዲያምን አይደረገ የኖረ ድርጅት ነው። ትህነግ ለትግራይ ሕዝብ ኤርትራና ከአማራን ቁሚ ጠላት አድርጎለታል። አሁን ደግሞ አፋርን አክሎለታል። ትህነግ የሶማሌ ክልል ሕዝብን በየትኛውም ዘመን ሊረሳ በማይችል ደረጃ አሰቃይቷል። የኦሮሞን ህዝብ ለንግግር በሚከብድ ደረጃ አዋርድ፣ እንዲሰደዱ አድርጎ፣ ቶርቸር አድርጎ፣ ገሎ፣ አፍኖ… ተጫውቶበታል። ትህነግ ሶማሌን ሲገልና በበረሃ እስር ቤት ሲያሰቃይ፣ ኦሮሞን ደብዛውን ሲያጠፋና ሲረሽን፣ አማራን ተላት አድርጎ ሲቀጠቅጥ፣ የኤርትራዊያንን ሃብት ሲቀማና ሲከድ ” ተው በስሜ አታድርግ” ያለ አልነበረም። ይልቁኑም በሌሎች ለቅሶ የሚጨፍሩ ነበሩ። አርሶ አደሩን አይመለከትም።

ይህ ተመዝግቦ ያለ የቅርብ ጊዜ የትህነግ ገድል ማስተባበያ የሚቀርብለት አይደለም። ከለውጡ በሁዋላም ቢሆን ወደ ትግራይ በማፈግፈግ “እንደ አንድ ክልል መኖር ይከብደኛል፣ እኔ ልዩ ነኝ፤ ከቤተመንግስት ውጭ መኖር አልችልም” በማለት የዘረፈውን እየረጨ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሽብር ሲግት ቆየ። በትህነግ ስፖንሰር አድራጊነት አሰቃቂ ግድያ ተፈጸም። ሕዝብ ተፈናቀለ። ዩኒቨርስቲዎች የመጫረሻ አምባ ሆኑ። ትህነግ ቀውሱን በፊል እየቀረጸ አገሪቱ በእንባና በሃዘን ማቅ ቀረቀረ። መንግስት ለማቋቋም ከፍተኛ ሃብት አውድሞ አልሆን አለው። መንግስት እንደሌለ ቀን ቆጥሮ አውጀ። አብረው በጓዳ አመድ ላይ ሲንደባለሉ የነበሩትን ይዞ መንግስት ለመግለበጥ ምስኪኑንን አቀንቃኝ አሳረደ። አሁንም አልሆነም። በመጨረሻ በመከላከያ ሃይል ላይ የክደት ቢላ አነሳ። አረዳቸው። እርቃናቸውን አሰቃያቸው። ሴቶቹን ጡታቸውን ቆረጠ። የተርፉትን በመኪና ሄደባቸው። ጫማ አስወልቆ በከተማ ማካከል እንደ ባዕድ ሃይል አስተፋባቸው። አሰደባቸው። ከስምንት ወር በሁዋላ – መርዝ እንዲጠጡ መደረጉን ጨምሮ ክህደት ተፈጸመ።

ያ ሁሉ አልበቃ ብሎ፣ መከላከያ ከወጣ በሁዋላ የወደመውን፣ የፈረሰውን እየተገኑ ችግሩ በሰላም እንዲፈታ ከመሞከር ይልቅ ” ከአማራ ጋር የምናወራርደው ሂሳብ አለ” በሚል ትህነግ ወረራ ውስጥ ገባ። በወረራቸው አካባቢዎች ሁሉ ሊጥ፣ ዱቂትና የሽንት ጨርቅ ሳይቀር ዘረፈ። ቅርስ አወደመ። ሆስፒታልና ክሊኒክ፣ ትምህርት ቤቶችንና ተቋማትን ዘርፎ የተረፈውን አመድ አደረገ።

ወረራውንም ሆነ ዘርፊያውን ሲያደረግ በተመሳሳይ ሰዓት “ሞትን፣ አለቅን…” እያሉ ሲነከባለሉ የነበሩ ጨፈሩ። ለሊጥና ዱቄት ዘፊያ፣ ለእንስሳት ግድያና የሃይማኖት ተቁማት ዝርፊያ ዘለሉ። ትምህርት ቤት ሲቃጠልና የጤና መስጫ ኬላና ሆስፒታሎች ሲወድሙ ” እሰይ ጀጋኑ” ብለው ከበሮ ደለቁ። ምንም የማያውቅ አርሶ አደር ሲታረድና ሲያልቅ አሽካኩ። በዚህ ሁሉ ስካር ውስጥ ሆነው በሁለት ሳምንት ውስጥ ሸኔን እየጋለቡ አዲስ አበባ እንደሚገቡ በናገር ሳይሆን መትፋት ጀመሩ።

ልክ እንደ እነሱ ሁሉ መንግስት ሃይሉን አስነሳ። አማራ ክተት አለ። ክልሎች ለድጋፍ ሃይል አሰማሩ። ኢትዮጵያ ከዳር እሰከዳር ተነሱላት። ዛሬ የጦር ሜዳ ውሎና ” እሰይ ጀጋኑ” መሆኑ ቀርቶ ሌላ ሆነ።

ከወረራቸው ስፋራዎች በመከላከያ፣ በህዝብ ማዕበል፣ በልዩ ሃይል፣ ሚሊሻና ፋኖ እየተቀጠቀጠ ተባረረ። ከጥቂት የወሎ አካባቢዎች በቀር ትህነግ አለመኖሩ፣ አልፎ አልፎ እንደ ሽምቅ ተዋጊ እዛም እዚህም ከሚያሰማው ተኩስ ውጭ አቅም አልባ እየሆነ እንደሆነ በመረጃ በሚነገርበት በአሁን ሰዓት የደጋፊዎቹን ሞራል ለማነሳሳት እየጣረ እንደሆነ ለመረዳት አያዳግተም። ሞራል ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ግራ ቢያጋባም፣ ራሱ ትህነግ ዙሪያ ሞራል አለ ወይ የሚለው ጥያቄ አነጋጋሪ ቢሆንም።

ይህን እያጻፍኩ ባለሁበት ቅጽበት የትህጋይ ሚዲያ ሃውስ ትህነግ ነፋስ መውጪያን አሁን ድረስ እንደያዘ እየሰበከ ነው። ደብረ ጽዮን ከአንዴም ሁለቴ እርቅ እየለመነ ደብዳቤ በሚጽፈበት ወቅት ነፋስ መውጪያ፣ ደባርቅ፣ ደብረታቦርና ወልደያ በቁጥጥራቸው ስር እንደሆነ እየለፈፉ ነው። ይህ ነው እንግዲህ ” ምን ይዤ ልመለስ” የሚለውን የቲዲን ዘፈን ያስታወሰው። በውጭ አገር ተሰቃይታ አልሆን ያላት/ ያለው ” ምን ይዤ ለመለስ” በሚል እንደወጣ መቅረቱን የሚያሳየው ልብ የሚነካ ዘፈን በትህነግ መንደርም አሁናዊ ዜማ ሆኗል።

የትግራይ ሕዝብ የታሰበለት ምን እንደሆነ ለምን አይጠይቅም? እስከ መቼስ ይሞታል?

አሸባሪው ትህነግ ካሁን በሁዋላ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሊመራ አይችልም። ይህ አሁን ያለው መንግስት ኖረም አልኖረውም ሃቅ ነው። የትግራይ ሕዝብም ይህን እውነት ጠንቅቆ ያውቃል። በተላይም ፊደል የቆጠሩት ይህን ይረዳሉ። ይህ ፖለቲካዊ ሃቅ ነው። ሸኔን ተሸክሞ ለመንከላወስ መሞከሩ ውጤት አልባ መሆኑንን እንቁው ወንድማችን ሃጫሉ በግፍ እንዲገደል ከተደረገ በሁዋላ የሆነው ሁሉ በቂ ምስክር ነው። ዝርዝር ውስጥ አልገባም።

እውነታው ይህ ከሆነ የትግራይ እናት ልጅ አልባ የምትሆንበት ምክንያት ምንድን ነው? ትህነግ አማራ ክልልን ወረረ፣ አፋርን ወረረ ከዛ የትግራይ እናት ወይም ሕዝብ ምን ያገኛል? ወረራው ተቀልብሶ፣ ይህ ሁሉ የተነቃነቀና የተቆጣ ሕዝብ በደረሰበት በደል ልክ ልበቀል ካለ የትህነግ መጨረሻ ምን ሊሆን እንደሚችል ማስላትስ እንዴት ይከብዳል? ይህ ሁሉ እየደረሰ እንዴት ነው ለምን? ለማን? ከዛስ? የሚል ትውልድ ትግራይ ውስጥ የማይነሳው? እስከመቼስ ነው የትግራይ ህዝብ እንደ ጠላት እየታየ እንዲኖር የሚፈረድበት? እስከ መቼ ነው በዚህ የሚቀጥለው? መንግስት በነበረበት ጊዜ ሁሉ የነበሩ ችግሮችን አሰባስቦ በንግግፍር መፍትሄ እንዳይገኝ በር ተዘግቶ የትግርያ ህዝብ ለቸነፈር የሚዳረገው ለምንድን ነው? መመለስ ያቃተኝ ጥያቄ ነው።

ሰለበዛና ጉዳቱ የከፋ በመሆኑ የትህነግን ብቻ አጎላሁት እንጂ ከዚህም ወገን ሰው አልቋል። ንብረት ወድሟል። ሃብት ባክኗል። እስከመቼ በዚህ ይቀጥላል? የሚለውን ጥያቄ አንስቼ ነበር። የሰላም መንገድ የሚጀመረው በትህነግ መቃብር ላይ እንደሆነ ሰማሁ። ትህነግ ብዛቱ ስንት ነው? የትህነግ መቃብርስ ስንት ነው? እነማን ሲያልቁ ነው ትህነግ ጠፋ የሚባለው?

በጥቅሉ የደረሰብን ውድመት እንደ አገር ወደፊት ሲገለጽ ትርፉ ህመም እንደሚሆን እሙን ነው። በመቶ ሺህ ሰው አልቋል። የዓለማችን የጦርነት ውሎዎች መጨረሻቸው ጠረጴዛ ነው። ዓለም ላይ የተካሄዱ አውዳሚ ጦርነቶች ያበቁት በመጨባበጥ ነው። መቶ ሺህ ሕዝብ ያለቅበት ባድመ፣ አልጀርስ ላይ በመጨባበጥ ነው ያለቀው። ከዛ በሁዋላ እርቅ የፈጸሙት ወደ ውስኪያቸው ሲዞሩ ልጇን ያጣች እናት በር በሩን እያየች ሃዘን እየጠበሳት ታልፋለች። ትናንት “አዲስ አበባን በሁለት ሳምንት እይዛለሁ ብያለሁና ካፈርኩ አይመልሰኝ” ግጥም ድርደራ ዋጋ የለውም። አሁንም እጅግ ሳይረፍድ ሞት የሚያበቃበት፣ የንጹሃን ስቃይ የሚቆምበት መንገድ ይፈለግ። በተለይ ትህነግ አስብበት!!

በላይ ይሁን ካሳዬ – ደብረብርሃን

Leave a Reply