አዲስ አበባ መልስ ሰጠች! ይህን ሕዝብ መውረር ይቻላል?

በክልልና የከልል የተለያዩ ከተሞች የተደረገውን ” የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባርና ሸኔን አንፈልግም” ሰልፍ ለጊዘው አቆይተነው የዛሬ የአዲስ አበባን ሕዝብ ምላሽ ስንምለከት ” ይህን ሕዝብ መውረር ይቻላል? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ እንገደዳለን። ይህን ሕዝብ በውጭና አገር ውስጥ በተተከሉ ሚዲያዎች የሽብር ዜናዎች መናድ ይቻላል? የሚል መከራከሪያ ማቅረብ እንጂ ምላሹን መጠበቅ አያስፈግልም።

አዲስ አበባ የተተከለው የቢቢሲ ሪፖርተር በ”እናት አገሩ” ኢትዮጵያ ቋንቋ ለኢትዮጵያዊያን “በአስር ሺህ የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች” ሲል የዛሬውን የተቃውሞ ሰልፍና “ትህነግ ወግድ አንፈልግህም” መልዕት አሳንሶ ነግሯል። ይህንኑ ዜናውን በረጨበት የፌስቡክ ገጹ የቀርበለትን ግብረ ምላሽ ይመልከቱ። የሕዝብን ቁጣና ሚዲያው ላይ የተሰነዘረውን ምላሽ እዚ መድገም አልፈልግም።

አንዴ ወደ ኦሮሚያ እናምራ አዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ከተሞች ዱከም፣ ሱሉልታ፣ሰበታ፣ ለገጣፎ፣ ራቅ ሲል ከቢሾፍቱ እስከ አዳማ፣ ከሰንዳፋ በታች፣ ከተጂ እስከ ወሊሶ፣ አይነኬው አምቦ፣ ከሙከጡሪ እስከ ሰላሌ ብቻ ያለውን ተቃውሞና ” የሚዘረፍ ሃብት የለም” ቅኔ መፈክር ላደመጠ፣ ይህን ሁሉ ህዝብ በመጨረስ ነው አዲስ አበባ የሚገባው ብሎ የቀላል አመክንዮ ጥያቄ ቢቀርብ መልስ የሚኖር አይመስለኝም። አልፎ አልፎ እንክርዳድ ቢኖርም።

ወደ አዲስ አበባ ልመለስ። ቢቢሲ አማርኛ፣ የአሜሪካ ሬዲዮና የጀርመን ድምጽ ባሳደገቻቸው ኢትዮጵያና ቤተሰቦቻቸው ላይ ስለሚከፈላቸው ብቻ በቋንቋችን የከፈቱት ዓመት የሞላው የሽብር ዜና፣ እንዲሁም የዋናዎቹ አጋፋሪዎች የሚዲያ ፊት አውራሪዎቹ እንደሚነዙት “አለቀላችሁ” ዜና ቢሆን ኖሮ ዛሬ የአዲስ አበባ ሕዝብ ከቤቱ ባልወጣ ነበር።ከሌቦቹ ስብስብ የተሻለ መንግስት ባይኖረው ኖሮ አብሮ ለመገፍተር ሲተባበር ባየነው ነበር። ይልቁኑ ” ችግርም ቢሆን እችለዋለሁ” ብሎ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ “ትህነግን አልፈልግም። ዋ!” ሲል በገሃድ እያዩ ስልት እንኳን ለመቀየር አለመሞከራቸው ያስገርማል። በማን ላይ ሂሳብ ለማወራረድ እንደሚክለፍለፉም ግልጽ አይደለም። ልክ እንደ ኮምቦልቻ፣ ቆቦ፣ ደሴ፣ ዋግ፣ አፋር ጋሊሶማ፣ ታስቦ ከሆነ “እኔ አላማረኝም” የሚለውን ዜማ ከማዜም ውጭ የምለው ነገር የለም።

ይህንን ጽሁፍ ስጽፍ እርቅና መግባባት አስፈላጊ አይደለም የሚል አቋም የለኝም። ግን ትህነግ ከአሁን በሁዋላ እንዴት ነው ከአማራ ህዝብ ጋር ሊታረቅ የሚችለው? እንዴት ነው ከአፋር ሕዝብ ጋር ዘመድ ሊሆን የሚችለው? እንዴት ነው ከሶማሌ ሕዝብ ጋር ህብረት ሊፈጥር የሚችለው? እንዴት ነው ዛሬ ላይ እያስፈራራው ካለው የሲዳማና የአርባ ምንጭ ሕዝብ ጋር ጎን ለጎን ሊቆም የሚችለው? እንዴት ነው የደራራ ከፈኒ ደም ላይ ቆሞ ከአምቦ ኦሮሞ ጋር የሚሳሳመው? ለመሆኑ የነዲ ገመዳ ደም ዋጋው ስንት ነው? ኦሮሞ በወጉ የትም ተጥለው በወጉ ባልተቀበሩ፣ የት እንደገቡ በማይታወቁት ልጆቹ ደም ላይ ቆሞ ከትግራይ ነጻ አውጪ ሃይሎች ጋር በምን ሂሳብ ነው እርቅ የሚያወርደው? የኢትዮጵያ እስር ቤት ቋንቋ ኦሮምኛ ሆኖ ሲቀጠቀጥ፣ ሲሰደድ፣ ሲቆረጥና ሲኮላሽ የነበረ ኦሮሞ እንዴት ነው ይህ ታሪክ ረስቶ ዳግም የትህነግ አጋር ሊሆን የሚችለው? እዚህ ላይ የተለየ አሳብ ያልችሁ? ከሽመልስ አብዲሳ፣ ከታዬ ደንደአ፣ ከአብይ አሕመድ፣ ከሌንጮ ባቲ፣ ከመርዳሳ ሌሊሳ… ይልቅ “እነሱን ገድዬና አስገድዬ፣ በኦሮሞ ልጆች ደም ላይ ቆሜ ከደብረ ጽዮን፣ ከጌታቸው፣ ከጻድቃን፣ ከትህነግ ሰራዊት ጋር በአንድ ጮጮ እጠጣለሁ፣ በአንድ ገበታ እቆርሳለሁ” የምትል ኦሮሞ ወዲህ በለኝ። ከተሳካ ማለቴ ነው። ሕዝብ በስለፍ አስታውቋል። ማሰብ ግድ ይላል ባይ ነኝ።

See also  ቻይናዊው የፀሃይ ሪል ስቴት ዋና ስራ አስኪያጅ ከ9 ግብረ አበሮቻቸው ጋር የውጭ አገር ብሮች በማተምና በጥቁር ገበያ ወንጀል ታስረው ፍ/ቤት ቀረቡ

እንደ ሕዝብ እርቅ ሊወርድ ይችላል። በግል የሚያሳስበኝ ጉዳይ ግን ከላይ ያነሳሁትን የሕዝብ ፍላጎት እንዳላዩ በመሆን ” ግፋ በለው ፕሮፓጋንዳ” ሌላ መዘዝ እንዳያመጣና ሁላችንም ልንረሳው ከማንችለው ሃዘን ውስጥ እንዳንቀመጥ ነው። ዛሬ በየወረዳው ክተት እየተባለ ነው። በትግራይም ክተት አለ። የዚህ ከተት መጨረሻ የሚታወቅ ነው። ስጋቱም እሱ ነው። አሁን ላይ ጦርነቱ የጦርነት ህግን ሽሮ ወደ ማዕበል መተላለቅ እየተቀየረ ነው። አንዱ ሌላውን መታገስ የማይችልበት ደረጃ ተድርሷል። የውጭ ሚዲያዎች የልዩ ፍላጎታቸውን ግብ እያዩ ከዛም ከዚህም ግፋ በለው እየሉ የሚፈራውን የከፋ እልቂት እየቆሰቆሱት ነው።

ትግሬ ቢገድል ወገኑን፣ ሌሎች ቢገድሉ ወገናቸውን መሆኑ እየታወቀ፣ አስከሬን ላይ ቆሞ በኩራት የሚጨፈርበት ዘመን ላይ ተድርሶ፣ ሚዲያዎች በወንድማማች ጦርነት አንዱን ልዩ ሌላውን ተሸናፊ እያደረጉ ዜና ሲረጩ ዓመት ሞላ። ኢትዮጵያዊያንም በየአቅጣጫው ሲያለቅሱ ሶስት ዓመት አለፋቸው። ከዛም ቀደም ሲል አገሪቱ ለውጥ አርግዛ ለሁለት ዓመት ያህል ስትናጥና ልጆቿን ስትቀብር ነበር። ሁሉም ተጠራቅሞ ዛሬ ዜጎች ጥር እያፋጩ ነው። ከዛም ከዚህም አክቲቪስት ነን ባዬች ለሳንቲም ለቀማ “ሰበር” እያሉ የሚረጩት መርዝ ነገሩን አግሞታል። ያለ ምንም መደባበቅ ነገሩ ተበላሽቷል።

ብልሽቱ ግልጽ ሆኖ ሳለ የውጭ ሃይሎችን ግፊትና ቅስቀሳ በማዳመጥ ” ግፋ በለው” እየተባለ ነው። “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” እንዲሉ ሊደርስ ያለው ትልቁ ቀውስ አሳሳቢነቱ አልታየም። የአሜሪካና ምዕራብ ሚዲያዎች ልክ በሊቢያ፣ በየመን፣ በኢራቅና በሲሪያ፣ ቀጥሎም በአፍጋኒስታን እዳደረጉት ኢትዮጵያ ላይ ለያዙት የመጨረሻ ዕቅድ ሕዝባቸውን የማሳመን ስራ እየሰሩ ነው።

ኢትዮጵያ ላይ ሊያደርጉ ያሰቡትን ለማከናወን ህዝባቸው እንዳይቃወማቸው እየነዙ ያለው ቅስቀሳ ሰርቶላቸዋል። ዛሬ አውሮፓውያንና አሜሪካውያን በአብዣኛው ወይም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ኢትዮጵያ እየነደደች፣ ልተነድ እንደደረሰች፣ አንድን ሕዝብ ነጥላ ልታጠፋ እንደተነሳች ተደርጋ ተስላለች። እውነታው ግን ሌላ ነው። ሁሉም ወገን ያውቀዋል። ዛሬ አዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች፣ ትናንትናና ከትናንት ወዲያ በርካታ ከተሞች ድምጻቸውን አሰምተው ቢናገሩም የዓለም ሚዲያያዎችና በዓለም ዓቀፍ ሚዲያ ውስጥ የሚሰሩ ተቀላቢ ወገኖቻችን የተሳሳተ መረጃ ለተጋተው ዓለም ለማዳረስ ፈቃደኛ አልሆኑም። ስጋቴ ትልቅ የሚሆነውም ለዚሁ ነው።

See also  የአሜሪካን ዓለም ዓቀፍ ተራድኦ ድርጅት USAID የሰሞኑን ተናዳፊነቱን ትቶ ለስለስ ያለ መግለጫ ሰጥቷል

በሌለ እውነት፣ መንግስትን የመገልበጥ አቅም ሳይኖር፣ ሕዝብ እንደማይፈልግ እያስታወቀ፣ መፈንቅለ መንግስት እንዲደረግ መሞከር ወይም መሪን አንድ ነገር ለማድረግ መሯሯጥ እዳውን ሌሎች እንዲከፍሉ እንዳያደርጋቸው ስጋቴ ታላቅ ነው። ዛሬ አዲስ አበባ የነገረችኝ ይህንኑ ነው። እንደ እኔ እንደ እኔ ሁሉም ወደ ክልሉ፣ ወደ ቀዬው ቢመልስ ደግ ነው ባይ ነኝ። ሁሉም ወደየክልሉ ተመልሶ ነገር ከተላዘበ በሁዋላ ሌላውን ጉዳይ በመነጋገር መፈወስ ይቻላል። ሌላው መንገድ “በማን ዳፋ ሌላው ተደፋ” እንደሚባለው ምክንያቱ ለማይታወቅ ጉዳይ ማለቅ መተላለቅ፣ በሚያስጨንቅ የግፍና እልቂት ታሪክ እየቆዘሙ መኖር። እስካሁን የተጫረስነው ራሱ ጊዜ ይፋ ሲያድርገው በሃዘን ለመማቀቅ ከበቂ በላይ ነውና ይብቃ!!

Leave a Reply