አፋር – መንገድ ላይ የወለዱ እናቶች፣ ነፍሰ ጡሮች፣ አቅመ ደካሞች በጥቃቱ ወላጅ አልባ የሆኑ ህጻናትን …

በትግራይ ክልል አዋሳኝ የሚገኙ የአፋር ክልል ነዋሪዎች ዳግም ወረራ እየተደረገባቸው መሆኑን ተናገሩ

… የተከፈተባቸው አዲስ ጥቃት በከባድ መሳሪያ የታገዘ በመሆኑ የክልሉ ህዝብ ብቻውን ሊቋቋመው እንደማይችል ለቋሚ ኮሚቴው አባላት አስረድተዋል

በአሸባሪው ህወሓት ዳግም ወረራ እየተፈጸመባቸው መሆኑን የአፋር ክልል ነዋሪዎች ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገልጸዋል።

በዶክተር ዲማ ነገዎ የተመራው የቋሚ ኮሚቴው ቡድን ሰሞኑን በአፋር ክልል የመስክ ምልከታ አድርጓል።

ቡድኑ ለትግራይ ክልል አዋሳኝ ከሆኑት 14 ቀበሌዎች ተፈናቅለው በአፍዴራ የመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተጎጂዎችንና የአከባቢው አመራሮችን አነጋግሯል።

ተፈናቃዮቹ አሸባሪው የህወሃት ሀይል ባደረሰባቸው የከባድ መሳሪያ ድብደባ መኖሪያቸውን ለቀው የተሰደዱ ሲሆን፤ መድረሻቸው ያልታወቀ በርካታ ዜጎች ስለመኖራቸውም ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ተናግረዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመነጋገር ለችግሩ እልባት ለመስጠት ይሰራል

የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽንን ጨምሮ ከተለያዩ ለጋሾች ሲደርስ የነበረው ሰብኣዊ ድጋፍም በአሸባሪው ቡድን ቁጥጥር ስር መዋሉን ከአብሃላ ወደ አፍዴራ የተፈናቀሉ ዜጎች ጠቁመዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በሁለት የመጠለያ ጣቢያዎች ተዘዋውረው በአሸባሪው ቡድን ከቀያቸው ተፈናቅለው መንገድ ላይ የወለዱ እናቶች፣ ነፍሰ ጡሮች፣ አቅመ ደካሞች እንዲሁም በጥቃቱ ወላጅ አልባ የሆኑ ህጻናትን ተመልክተዋል።

የአፋርን ልዩ ሀይልና ሚሊሻ በጦርነት መግጠም የማይደፍረው የህወሃት ሀይል ሰላማዊ ዜጎች ላይ የከባድ መሳሪያ ድብደባ መፈጸሙን የአከባቢው አመራሮች ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በዱብቲ አጠቃላይ ሆስፒታል ባደረጉት ምልከታ ሴቶችና ህጻናትን ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች በአሸባሪው ቡድን የከባድ መሳሪያ ጥቃት ደርሶባቸው የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ያሉ ቁስለኞችን ጎብኝተዋል።

አባላቱ ከሀይማኖት መሪዎችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።

መንግስትና የተለያዩ ለጋሾች ለአፋር ክልል እያደረሱ ላለው ሰብዓዊ ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት የክልሉ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች፤ የተከፈተባቸው አዲስ ጥቃት በከባድ መሳሪያ የታገዘ በመሆኑ የክልሉ ህዝብ ብቻውን ሊቋቋመው እንደማይችል ለቋሚ ኮሚቴው አባላት አስረድተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) በክልሉ እየተፈናቀለ እና አየሞተ ለሚገኘው ህዝብ አፋጣኝ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ ገልፀው፤ ቋሚ ኮሚቴው ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመነጋገር ለችግሩ እልባት ለመስጠት ይሰራል ማለታቸውን ምክር ቤቱ ዘግቧል።

(ኢ ፕ ድ)

You may also like...

Leave a Reply