በሳዑዲ አረብያ ኢትዮጵያዊያን ላይ የሚፈጸመው ግፍ እንዴት ማስቆም ይቻላል? የሚል ጭንቀት በርክቷል

መረጃውን በፎቶ አስደግፈው ያሰራጩት ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ በማህበራዊ ገጻቸው ያሰራጩት ዜና ከተለመደው በላይ ያስደነግጣል። ምስሉን እድንብ ለመመልከት አይቻልም። የሰው ልጅ በህግ ጥላ ስራ ሆኖ እንዲህ የሚሰቃየው ለምንድን ነው? ምንስ ስላደረገ ነው? ህጻናትን ሙቀት ማቃጠልና በቁስል ማንፈር ለምን ተፈለገ? … ይህ የወገን ስቃይ እንዴት ይቁም? ማን ያስቁመው? መንግስት ሲሄድ “እሺ” ይላሉ። ወዲያው ከእስር ቤት የሚወጣው መረጃ ታጥቦ ጭቃ ነው። ምን ይደረግ?

ኡሳታዝ አሕመድም የጠየቁት ይህንኑ ነው። ቀደም ባሉት ዓመታት ጡንቻቸውን ተማምነው በህገወጥ መንገድ ዜጎችን ሲያግዙ የነበሩ ማጅራት መቺዎች በልጽገው ዛሬ ወገኖች መከራቸውን ያያሉ። እንደ ባሪያ ንግድ በጅምላ ሃብታቸውን እያሸጡ አግዘዋቸው ለህገወጥነት ዳረጉዋቸው። በህገወጥ ሃብታቸውን እየበሉ ባዕድ እጅ በትነዋቸው ዛሬ በየ እስር ቤት ወገኖቻችን እያለቁ ነው። በምስሉ ላይ እንደሚታየው የሚፈጸመውና የሚሆነው ሁሉ ያማል። ። ምስሉን ለመለጠፍ አቅም ባይኖረንም እየፈራን እየተባን ከውስጥ አንድ ምስል ተጠ3ቅመናል። ኡስታዝ ከዚህ የሚከተለውን ማስታወሻ አቅርበዋል

በሳዑዲ አረብያ እስር ቤት የሚገኙ ወገኖቻችን በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወታቸው ማለፉ እንደቀጠለ ነው:: ከእስር ቤቶቹ የወጡ እጅግ ልብ የሚሰብሩ በኢ ሰብዓዊ አያያዝ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ህፃናት እና ወጣቶች ምስሎችንም እየተመለከትን እንገኛለን::

የኢትዮጵያ መንግስት እያደረገው ካለው ጥረት በተጨማሪ ሰፊ የዲፕሎማሲ እና የነፍስ አድን ስራዎችን እንዲሰሩ ሊያደርግ ይገባል

በዚህ ባለንበት ዘመን በህግ ጥላ ስር የሚገኙ እስረኞችን እንዲህ ኢ ሰብዓዊ በሆነ አያያዝ መያዝ በአለም አቀፍ የሰብኣዊ ድንጋጌዎች ብቻ ሳይሆን በኢስላምም ፈፅሞ የተወገዘ ተቀባይነት የሌለው ነው::

ህግ የተላለፉ በህግ ጥላ ስር የሚገኙ ሰዎችን ይቅርና የጠላት የጦር ምርኮኞችን እንኳን እንዴት በአግባቡ መያዝ እንዳለብን ኢስላም አስተምሮን ሲያበቃ በሳዑዲ ምድር የዚህ አይነቱን ግፍ መመልከት ልብ ያደማል::እንዲህ አይነት ጭካኔ እና ለሰው ልጆች ነፍስ መራራት ከልባቸው ውስጥ እንጥፍጣፊ ሳይቀር መጥፋቱ ከምን ይሆን??

በቅርቡ ወደ ሳዑዲ አረቢያ የተጓዘው ቡድን ከሳኡዲ አረቢያ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች ጋር እስረኞቹ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ በተመለከተ ተወያይተው የውይይቱ ውጤት ን በሳዑዲ እና በኢትዮጵያ መንግስታት ተፈፃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ሁላችንም እየተጠባበቅን ባለንበት ወቅት የዜጎቻችን ስቃይ እየከፋ መምጣቱ እጅግ ያሳስባል::

See also  የአረብ ሊግ የሕዳሴ ግድብ አመልክቶ ያወጣውን መግለጫ " የአንድ አገር ቃል አቀባይ" ስትል ኢትዮጵያ አጣጣለች

እኛም እንደ ሃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ የወገኖቻችንን ስቃይ በማህበራዊ ሚዲያ ማስተጋባት ብቻ ሳይሆን አቅም በፈቀደው መልኩ በመንግስት ደረጃም የዜጎቻችን ጉዳይ ትልቅ ትኩረት እንዲቸረው ግፊት በማድረግ የምንችለውን ነገር ሁሉ ከማድረግ አልተቆጠብንም::

በሳኡዲ እስር ላይ የሚገኙ ወገኖቻችን ጉዳይ በግለሰቦች ጥረት ብቻ የሚፈታ ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ የሚጠይቅ ነው::

ይህ ሳኡዲ በምትባለው የምድር ሲኦል ውስጥ ከሚፈጸመው ግፋ ከብዙዎቹ አንዱ አስጨናቂ ምስል ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት እያደረገው ካለው ጥረት በተጨማሪ ሰፊ የዲፕሎማሲ እና የነፍስ አድን ስራዎችን እንዲሰሩ ሊያደርግ ይገባል:: በእስር ላይ እያሉ በህመም እየተሰቃዩ እና በሞት አፋፍ ላይ የሚገኙ ዜጎቻችን አስቸኳይ ህክምና እንዲያገኙ መንግስት ከፍተኛ ስራ መስራት ይጠበቅበታል::

የሳዑዲ መንግስት ለበርካታ አመታት እስረኞችን የአውሮፕላን ትኬት ወጪያቸውን በመሸፈን ወደ ሃገር ሲመልስ የቆየ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የሃገሪቷን መልካም ስም የሚያጠለሽ በኢስላምም ሆነ በአለም አቀፍ የሰብኣዊ ድንጋጌዎች ያፈነገጠ የእስረኞች አያያዝ ተግባራዊ ማድረጉ ሊያቆም እና አላህን ፈርተው የእስረኞችን አያያዝ ሊያስተካክሉ እንደሚገባ ሰፊ ስራዎችን መስራት ይጠበቅብናል::

ዜጎቻችን ወደ ሃገራቸው እስኪመለሱ በዱዓ እነሱን ከማገዝ ጎን ለጎን መንግስት ከሳኡዲ መንግስት ጋር ያደረገውን ውይይት ባስቸኳይ ተፈፃሚ ይሆን ዘንድ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ማሳሰብ እና ግፊት ማድረግ ይኖርብናል

Via ኡሳታዝ አቡበከር ፌስ ቡክ

Leave a Reply