«ትግራይን ነፃ እናወጣለን ነው የሚሉት። ትግራይ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ማን ኢትዮጵያዊ ሊሆን ነው? አሁንም ምን እንደሚያደርጉ ግራ ስለገባቸው ነው እንጂ ትግራይ አሁንም ያለችው በእነርሱ እጅ ነው። በአንድ በኩል ትግራይን ነፃ እናወጣለን ይላሉ በሌላ በኩል አገልግሎት ስጡን ይላሉ። አሁን ደግሞ ኤርትራን ሰብረን ወጥተን አሸንፈን ታላቋን ትግራይ እንመሠርታለን እያሉ ነው። ይህ የማይሆን ነገር ነው። ድሮስ ጎረቤት ላይኖራቸው ነበር? ይህ የመወራጨት ዓይነት ተግባር ነው።» ፕሮፈሰር ሀረገወይን

አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ጥላቻን የማያቆም፣ ሕፃናትንና አረጋውያንን ጭምር መሣሪያ አሸክሞ የሚያስጨርስ ጦርነትን እንደ አምልኮ የሚቆጥር ቡድን ነው ሲሉ ፕሮፌሰር ሀረገወይን አሰፋ ተናገሩ፡፡

ፕሮፌሰር ሀረገወይን አሰፋ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ አሸባሪው ሕወሓት ከ40ዓመታት በፊት የጀመረውን በጥላቻ የተሞላ የጦርነት ታሪክ ዛሬም እየቀጠለ ይገኛል፡፡ የሽብር ቡድኑ ይህን መጥፎ ታሪኩን እንደ እምነትና አምልኮ በመቁጠር ከበፊት የቀጠለ የጥላቻ ትርክት በማስቀጠል ሕፃናትን በ13ዓመት መሣሪያ አሸክሞ ወደ ጦር ግንባር በመላክ ጦርነት እየቀሰቀሰ ነው፡፡

ፕሮፌሰር ሀረገወይን እንደሚሉት፤ የሽብር ቡድኑ ምን እያደረገ እንዳለ አያውቅም፡፡ በፊትም ቢሆን ጦርነቱ መጀመር አልነበረበትም፡፡ የአገር መከላከያ ሠራዊት ከገበሬው ጋር ሲያጭድ ገንዘብ በማዋጣት ዓመት በዓልን ከአረጋውያን ጋር ሲያሳልፍ ነበር፡፡ በዚህ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙ ተገቢ አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያት በተጀመረው ያላባራ ጦርነት ውስጥ በርከታ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ሕወሓት አሁን እያደረገ ያለውና ከዛሬ 40ዓመት በፊት ሲያደረግ የነበረው የጦርነት ታሪክ አንድ ዓይነት ነው፡፡ ይህ የሽብር ቡድኑን በጦርነት የማምለክ ባህልን የሚያሳይ ነው፡፡

ጦርነት ሲደረግ የሚጨፈርበት ቦታ ትግራይን ብቻ ነው የማውቀው ያሉት ፕሮፌሰሯ፤ ክልሉ በእናቶች ስም ጦርነት የሚሰየምበት፤ አንድ እናት ጀግና ለመባል አምስት ልጆቿን ገፍታ እንድትልክ የምትገደድበት እንደሆነም ገልጸዋል። በክልሉ ውስጥ ቡድኑ እንዳሻው የሚያደርግበት በመሆኑ ሴቶች መጠቀሚያ እንጂ እናትነታቸው እንኳን በተግባር የተገለጠበት አይደለም ይላሉ። 

በተለይ ክልሉ ከድሮም ጀምሮ በጦርነት ውስጥ ያለፈ በመሆኑ ጦርነትን እንደ ትልቅ ነገር ከዚያም ባለፈ እንደ አምልኮ የመቁጠር ሁኔታ እንዳለ ጠቅሰዋል። ለልጅ ጥላቻን ማስተማር ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ከመሆኑም በላይ ሕፃናት ላይ ጥላቻን መዝራት በሂደት የትግራይን ሕዝብ የሚጎዳ በመሆኑ ከጦርነት ታሪክና ከጥላቻ ይልቅ ፍቅር ማስተማር ከሕዝቡ እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።

 ፕሮፈሰር ሀረገወይን፤ ጦርነት ምንም ነገር እንደማይፈታ ከትግራይ በላይ የሚያውቅ የለም በማለት፤ ሕወሓት ጥላቻን በሕዝቡ ላይ በመርጨት ከ13ዓመት ጀምሮ በማስታጠቅ ትግራይን ወደ ኋላ እያስቀራት እንደሚገኝ፤ ለሦስተኛ ጊዜ አደርገዋለሁ የሚለውም ጦርነት ሕዝብ ለማስጨረስ እንጂ የትም እንደማያደርሰው ተናግረዋል።

«ትግራይን ነፃ እናወጣለን ነው የሚሉት። ትግራይ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ማን ኢትዮጵያዊ ሊሆን ነው? አሁንም ምን እንደሚያደርጉ ግራ ስለገባቸው ነው እንጂ ትግራይ አሁንም ያለችው በእነርሱ እጅ ነው። በአንድ በኩል ትግራይን ነፃ እናወጣለን ይላሉ በሌላ በኩል አገልግሎት ስጡን ይላሉ። አሁን ደግሞ ኤርትራን ሰብረን ወጥተን አሸንፈን ታላቋን ትግራይ እንመሠርታለን እያሉ ነው። ይህ የማይሆን ነገር ነው። ድሮስ ጎረቤት ላይኖራቸው ነበር? ይህ የመወራጨት ዓይነት ተግባር ነው።» ሲሉም ነው ፕሮፈሰር ሀረገወይን የተናገሩት።

ፕሮፌሰር ሀረገወይን አሰፋ የታዋቂዋ ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ እናት ሲሆኑ የሕወሓትን ሴራና ድርጊት በማጋለጥ እናትና ልጅ ግንባር ቀደም ተሳትፎ የሚያደርጉ ናቸው።

አዲሱ ገረመው አዲስ ዘመን ግንቦት 11 ቀን 2014 ዓ.ም

Leave a Reply