በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሲንቀሳቀሱ በነበሩ የአሸባሪው ሸኔ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ። በዞኑ በሚገኙ በአቦቴ እና በወረጃርሶ ወረዳዎች በስፋት በመንቀሳቀስ ህበረተሰቡን ሲዘርፉ እና ሲያሰቃዩ በነበሩት የሸኔ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ በመወሠዱ በአሁኑ ወቅት በአካባቢዎቹ አስተማማኝ ሰላም መስፈኑ ተገልጿል።
በዞኑ ቀጣይነት ያለው ሰላም ለማስፈን በአካባቢው የተሰማሩት የጥምር ፀጥታ አካላት በሽብር ቡድኑ ላይ የማያዳግም እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን የገለፁት የጥምር ፀጥታ አካላት አስተባበሪ እና በኮማንዶ ክፍለ ጦር የሬጅመንት ዋና አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ታሄል ሬድ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በተደረገው ሁሉን አቀፍ ዘመቻ በርካታ አመርቂ ድሎች እየተመዘገቡ ይገኛሉ ብለዋል።
እንደ ዋና አዛዡ ገለፃ እስከ አሁን በተደረጉ ዘመቻዎች እርምጃ የተወሰደባቸው 44፣ የተማረኩ 05፣ ሲሆን 18 የተለያዩ መሳሪያዎች ተማርከዋል፣ የሽብር ቡድኑ ሲጠቀምበት የነበረም 19 ኩንታል እህል በቁጥጥር ስር ውሏል።
በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን የሰጡት ደግሞ 233 መሆናቸውን የጥምር ፀጥታ አካላት አስተባበሪ እና በኮማንዶ ክፍለ ጦር የሬጅመንት ዋና አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ታሄል ሬድ ገልፀዋል።
ከአከባቢው ህብረተሰብ፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ከአባገዳዎች ጋር በመሆን በተሰራው የተቀናጀ ትብብር የተገኘው ድል አበረታች ነው ያሉት ደግሞ የወረጃርሶ ወረዳ ዋና አስተዳደሪ አቶ አየለ መንግስቱ ናቸው።
ከህብረተሰቡ የተወከሉ የአከባቢው ሽማግሌዎች እና አባገዳዎችን ወደ ጫካ በመላክ ከታጣቂዎቹ ጋር በተደረገው ድርድር እና ውይይቶች በርካታ የአሸባሪው ሸኔ ታጣቂዎች በየቀኑ በሰለማዊ መንገድ እጃቸውን በአከባቢው ለተሰማራው ለፀጥታ አካላት እየሰጡ እንደሚገኙ የገለፁት ዋና አስተዳደሪው በአሁኑ ወቅት በአከባቢው አንፃራዊ ሰላም መስፈን ችሏል ብለዋል።
ታሪኩ ሻሜቦ መከላከያ ማህበራዊ ገጽ