መንግስት የኑሮ ወድነትን ለማሻሻልና የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት ተከታታይነት ያለው እርምጃ አንደሚወስድ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡
መንግስት በሰጠው አቅጣጫና የሀገሪቱ ብሄራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ቡድን በወሰነው መሰረት የኑሮ ውድነትን ለማሻሻልና ገበያውን ለማረጋጋ በሚቀጥሉት ሶስት ወራት 150 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ከውጭ እንዲገባ መወሰኑ ይታወሳል።
በአሁኑ ጊዜም 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ነው። ከዚህ ውስጥ 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ ለህብረተሰቡ እየተከፋፋለ ሲሆን 7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ደግሞ በሚቀጥሉት ሶስት ሳምንታት ውስጥ ወደ ሀገር ውስጥ ተጠቃሎ እንደሚገባ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
ድፍድፍ ዘይት ከውጭ አስመጥተው በሀገር ውስጥ ለሚያመርቱ ሶስት ፋብሪካዎችም ምርቶቻቸውን ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ የውጭ ምንዛሬ የተመቻቻላቸው ሲሆን የምግብ ዘይት እጥረትን ለዘላቂነት ለመፍታትም ለሌሎች አቅራቢዎችም ዘይት ከውጭ አስመጥተው ለመንግስት እንዲሸጡ ፈቃድ የተሰጣቸው መሆኑንም አቶ አህመድ ገልጸዋል፡፡
መንግስት የኑሮ ወድነትን ለመቅረፍ የተለያዩ ጥረት ሲያደርግ እንደነበር የገለጹት ሚኒስትሩ ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታት የምግብ ዘይት ከቀረጥ ነጻ እንዲገባ በማድረጉ 23 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ያጣ ሲሆን ለነዳጅ የ100 ቢሊዮን ብር ድጎማ ማድረጉን መናገራቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
(ኢ ፕ ድ)