«…የሽብር ቡድኑ ወደደም ጠላም ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጣ ለማድረግ አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ ይወስዳል» መንግስት

የትግራይ ህዝብ ችግሮችን ለመፍታት ሰላማዊ አማራጭ ዛሬም፤ ነገም ብቸኛዉ መፍትሄ ነዉ!

መንግስት ተገዶ የገባበትን የሰሜኑን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት ያስችላሉ ያላቸውን እርምጃዎች ሲወስድ መቆየቱ ይታወቃል። የሽብር ቡድኑ ህወሃት ከወረራቸው የአማራና የአፋር አብዛኞቹ አካባቢዎች ተገፍቶ እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ መንግስት፤
• ሙሉ የሰራዊትና ሎጂስቲክስ አቅም እያለው ወደ ትግራይ ክልል ከመግባት መቆጠቡ
• የተሳለጠና ያልተቋረጠ የሰብአዊ ድጋፍ ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ የተናጠል ተኩስ አቁም ማድረጉና ምቹ ሁኔታን መፍጠሩ
• ለሰላም በር ይከፍታል በሚል እስረኞችን መፍታቱ
• የሰላም አማራጭንም አሟጦ ለመጠቀም እንዲቻል የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴን በይፋ ወደ ስራ አስገብቶ ግልጽ አቅጣጫንም ማስቀመጡ
• አስፈላጊ የሆኑ መሰረታዊ ቁሳቁሶች ወደ ትግራይ እንዲጓጓዝ ማድረጉ
• በአሸባሪዉ ቡድን የወደሙ አገልግሎት መስጫዎችን በመጠገን በሶስተኛ ወገን በኩል ስራ ለማስጀመር እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

ሆኖም አሸባሪው ቡድን ከውጪ ደጋፊዎቹ ጋር በመሆን ጦርነቱን የመቀጠል ከፍተኛ ፍላጎትን ሲያንጸባርቅ ቆይቷል፡፡ ከበባውን እንሰብራለን፣ መተማመኛችን ክንዳችን ነው፣ የትግራይ መሬቶች ተወረዋል፣ እናስለቅቃለን፣ ወዘተ በሚል ፉከራ ታጅበው ባለፉት ስድስት ወራት የተለያዩ ትንኮሳዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። በምዕራብ በኩል በተደጋጋሚ ሞክረው ሽንፈትን እየተከናነቡ ተመልሰዋል። በደቡብ ትግራይ በኩልም ተደጋገሚ ሙከራ ቢያደርጉም መንግስት ሙከራቸውን እያከሸፈ ዋናው መፍትሔ የሰላም መንገዱ ነው በሚል ጉዳዩ እንዳይባባስ አድርጓል።

ሆኖም ከመንግስት በኩል የቀረቡለትን በርካታ የሰላም አማራጮች ሁሉ ወደጎን በመተው የሽብር ቡድኑ ህወሃት ታጣቂ ቡድን ሰሞኑን ሲፈጽም የሰነበተዉን ትንኮሳ ገፍቶበት ዛሬ ንጋት ላይ በምስራቅ ግንባር በቢሶበር፣ በዞብል እና በተኩለሽ አቅጣጫዎች ከለሊቱ 11 ሰአት ጀምሮ ጥቃት ፈጽሟል። በወሰደዉ እርምጃም ተኩስ ማቆሙን በይፋ አፍርሷል፡፡ የፈጸመው ጥቃትም ሆነ እሱን ተከትሎ ያወጣው መግለጫ አሰቀድሞ ለትንኮሳው ሲዘጋጅ እንደነበር ግልጽ ማሳያ ነው።

ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችንና መላው የጸጥታ ሃይላችን ከሽብር ቡድኑ የተሰነዘረውን ጥቃት በተቀናጀ መልኩ በድል እየመከቱት ይገኛሉ። የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከአሸባሪው ቡድን ለመጠበቅም በወትሮ ዝግጁነት ሁሉም የጸጥታ ሃይላችን በተጠንቀቅ ቆሟል።
ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል እንደሚባለው ቀድሞም በተካኑበት የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ስራ ራሳቸዉ ተንኩሰዉ ራሳቸዉ እየጮሁ ይገኛሉ፡፡

See also  ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል

ለሰላም እጁን የዘረጋዉን መንግስት በሃሰት በመወንጀል “ድርድሩ አስቀድሞ ከሽፏል” በሚል ለተለያዩ ወገኖች ጦርነቱ እንደማይቀር ሲያደርጉ የነበረዉን ቅስቀሳ በማጠናከር የትግራይን ወጣት ዳግም ሊማግዱት በይፋ አዉጀው ወደ ጦርነት እየተንደረደሩ ነዉ፡፡

ሰሞኑን አለም አቀፍ አጫፋሪዎቻቸው ካሸለቡበት ብቅ ብቅ ማለታቸውም የጦርነት ዝግጅቱን በፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የማጀብ አካል መሆኑ ግልፅ ሆኗል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የትግራይን ወጣት ለማስጨረስ ሕወሓት የሚያደርገውን የጦርነት ጉሰማ እንዲያቆም ጠንካራ ግፊት ማድረግ ይኖርበታል፡፡

በሃገር ውስጥም ሆነ በመላው አለም የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ከዚህ የጥፋት ሃይል የሚሰነዘረውን ጥቃት ለመመከትና ኢትዮጵያን የመበተን ግልጽ አላማ የያዘውን ይህንን የሽብር ቡድን የጥፋት ሙከራ ለማምከን በጋራ እንድንቆም መንግስት ጥሪውን ያቀርባል።

የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥያቄ መፍትሄ ማግኘት የሚችለው በሰላማዊ መንገድ ብቻ መሆኑን በመገንዘብ ዛሬም ነገም የሰላም አማራጭ የመጀመሪያ መፍትሔ እንደሆነ መንግሥት ፅኑ እምነት አለዉ፡፡

ሆኖም አሸባሪዉ የሕወሓት ቡድን በትንኮሳው ከገፋበት፤ መንግስት ሀገር የማዳን ሕጋዊ፣ ታሪካዊና ሞራላዊ ግዴታ ስላለበት እንዲሁም የሽብር ቡድኑ ወደደም ጠላም ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጣ ለማድረግ አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ ይወስዳል፡፡

ይህንን ለማስፈፀም ደግሞ መንግስትና መላው የፀጥታ ሃይላችን ከነሙሉ ብቃትና ቁመናቸዉ በተጠንቀቅ ላይ ናቸው።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

Leave a Reply