“ታማኝ ናችሁ”- ልዩ መብት የተፈቀደላቸው የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች

ልዩ መብት የተፈቀደላቸው የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች የተሰጣቸውን ዕድል በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል-ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ

ልዩ መብት የተፈቀደላቸው የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች የተሰጣቸውን ዕድል በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ ገለጹ።

የጉምሩክ ኮሚሽን በዛሬው እለት ለ193 ድርጅቶች “የልዩ መብት የተፈቀደላቸው ኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች መርሐግብር” ተጠቃሚ እንዲሆኑ እውቅና ሰጥቷል።

የልዩ መብት የተፈቀደላቸው የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች ጉምሩክን ጨምሮ በማንኛውም አገልግሎት ሰጪ የመንግሥት ተቋም ቅድሚያ የማግኘት ዕድል አላቸው ተብሏል፡፡

ድርጅቶቹ ዕቃዎችን ሲያጓጉዙ በዝቅተኛ የሥጋት ደረጃ የሚስተናገዱ ሲሆን የድኅረ-ክፍያ፣ የቀረጥና ታክስ ዱቤ የሚያገኙ ይሆናል ተብሏል፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ግብር ከፋዮች የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ በርካታ የሪፎርም ሥራዎች ተከናውነዋል።

በዚህም የመንግሥት ገቢ የመሰብሰብ አቅም ከመቼውም ጊዜ በላይ እያደገ እና የአገልግሎት አሰጣጡም እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።

የልዩ መብት የተፈቀደላቸው ኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች በታማኝነት የሚጠበቅባቸውን በመወጣታቸው የተሰጠ ልዩ ጥቅም መሆኑን ገልጸዋል።

መንግሥት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ታማኝ ግብር ከፋዮችን ከማመስገንና እውቅና ከመስጠት ባለፈ የልዩ መብት እንዲፈቅድላቸው እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የልዩ መብት የተፈቀደላቸው 193 የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾችም የዚሁ አካል መሆናቸውን ገልጸው፤ የላቀ አገልግሎት ፈልገው በሚሄዱባቸው ተቋማት ሁሉ የቅድሚያ አገልግሎት ያገኛሉ ብለዋል፡፡

እውቅና የተሰጣቸው ድርጅቶችም የተሰጣቸውን ልዩ መብት ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ በመጠቀም እስካሁን የነበራቸውን ታማኝነት አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ፤ በበጀት ዓመቱ እስካሁን በተወሰደ እርምጃ 52 ቢሊዮን ብር የሚገመት ቁሳቁስ በኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ ንግድ ሲንቀሳቀስ በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ገልጸዋል፡፡

የልዩ መብት የተፈቀደላቸው የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች ተቋማዊ አቅምን በማጎልበት፣ ለሕግ ተገዥነትን በማክበር እና ኢኮኖሚውን በማንቀሳቀስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

የልዩ መብት የተፈቀደላቸው ኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች በበኩላቸው፤ መንግሥት “ታማኝ ናችሁ” ብሎ እውቅና ስለሰጠን እናመሰግናለን ብለዋል፡፡

የተሰጣቸውን ዕድል በታማኝነት መጠቀም ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ (ኢዜአ)

See also  አራዊት ጤንነቱ ታውኳል፤ ወደ አገር ቤት ለመመለስ አብነት ገብረመስቀል ምላሹ እየተጠበቀ ነው

Leave a Reply