ዐቃቤ ሕግ አነስተኛ የቴምብር ቀረጥ ለመክፈል በማሰብ ንብረት ከሸጠችበት ትክክለኛ ዋጋ አሳንሳ ገልጻለች ባላት ግለሰብ ላይ ክስ መስርቷል፡፡

ዐቃቤ ህግ ሲፈን አበራ ገመቹ የተባለችው የ27 ዓመት ወጣት የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 123(1) (ለ) ስር የተደነገገውን በመተላለፍ የቴምብር ቀረጥ ላለመክፈል ወይም አነስተኛ የቴምብር ቀረጥ ለመክፈል በማሰብ የመኖሪያ ቤት ሽያጭ ከፈጸመችበት ትክክለኛ ዋጋ አሳንሳ በመግለጽ በመንግስት ጥቅም ላይ ጉዳት አድርሳለች ባላት ግለሰብ ላይ ነው ክስ የመሰረተው፡፡

የዐቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው ከሆነ ተከሳሽ መኖሪያ ቤቷን በተጨባጭ የሸጠችው በብር 7‚700.000 (ሰባት ሚሊዮን ሰባት መቶ ሺ) ሆኖ እያለ በሰነዶች ማረጋገጫ ፊት ቀርባ ስትዋዋል ባቀረበችው ሰነድ ግን በብር 1‚000‚000.00 (አንድ ሚሊዮን ብር) እንደሸጠች የገለጸች በመሆኑ እንዲሁም በሌላ የመኖሪያ ቤት ሽያጭ ቤቱን በተጨባጭ የሸጠችው በብር 17‚000.000 (አስራ ሰባት ሚሊዮን) ሆኖ እያለ በሰነዶች ማረጋገጫ ፊት ቀርባ ስትዋዋል ባቀረበችው ሰነድ በብር 1‚000‚000.00 (አንድ ሚሊዮን ብር) እንደሸጠች በመግለጽ የሰነዶቹን ትከክለኛ ባህሪ የደበቀች በመሆኑ ክስ ቀርቦባታል፡፡

በቀረበው ክስ ላይ ክርክር በመደረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን ይህን ወንጀል ጨምሮ ተከሳሿ ከሌሎች ተከሳሾች ጋር በጋራ በአንድ መዝገብ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ክርክሩ በግልጽ ችሎት እተከናወነ ይገኛል፡፡

Leave a Reply