በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ያቤሎ ወረዳ ሃርወዩ በምትባል ቀበሌ ሁለት ወጣቶች ላይ ኢሰብአዊ ርምጃ የወሰዱ የተባሉ ባለስልጣናት መታሰራቸው ተሰምቷል።
በአከባቢው ሰሞኑን ሁለት ወጣቶች እጅ እግራቸውን የፊጢኝ ወደኋላ ታስረው ሲደበደቡና ሲሰቃዩ የሚያሳይ ምስል በማኅበራዊ መገናኛ ተለቅቆ መነጋገሪያ ሆኗል። ጃሮ ዳሌ እና ጋርቦሌ ዋቆ በተባሉ ሁለት ወጣቶች ላይ የተፈፀመው የደቦ ፍርድ በሚል በሰብአዊ መብት ጥሰት ተተችቷል ።
የያቤሎ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጎቡ ጫና እንደተናገሩት፤ በዚህ ሰብአዊ መብትን በጣሰው ድርጊት የተሳተፉት ከቀበሌ አስተዳዳሪ እስከ የአከባቢውን ሰላም እንዲያስጠብቁ የታጠቁ ሚሊሻዎች ያሉት ናቸው ብለዋል ።
በመሆኑም ወጣቶቹን ይዘው ያለ ፍርድ አስረው በማሰቃየት ድርጊት የተጠረጠሩ እስከ ዛሬ የቀበሌ አስተዳዳሪ እና ታጣቂ ሚሊሻዎችን ጨምሮ ዐሥር ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ለፍረድ እየቀረቡ ነው ሲሉ ገልፀዋል ።
አንደ ኃላፊው ገለጻ ለችግሩ መነሻ የሆነው በቀበሌው 6 ኩንታል የርዳታ እህል ጠፍቶ በገበያ መሸጡና በዚህም ስርቆት ሁለቱ ወጣቶች መጠርጠራቸው ነው ። ሁለቱ ለድብደባ እና ስቃዩ የተዳረጉት ወጣቶች አንዱ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ እረኛ ነው ተብሏል ።
የወረዳው አስተዳዳሪ ድብደባው የተፈፀመባቸው ሁለቱ ወጣቶች አሁን በደህና ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙና እነሱን የሚያስከስስ መረጃ አለመኖሩንም አንስተዋል ። ስለጉዳዩ የተጠየቀው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በጉዳዩ ላይ መረጃ እያሰባሰብኩ ነው ብሏል፡፡
(ዶይቸ ቬለ)