ኢትዮጵያ ከተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ጋር ያላት ሁለንተናዊ ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል – ጠ/ሚ ዐቢይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ ከተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ጋር ያላት ሁሉን አቀፍ ትብብር በበርካታ ዘርፎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ እና የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፎች የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ያለመ ስትራቴጂያዊ አጋርነት መመስረታቸውንም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን ማፍሰስ ለሚፈልጉ አልሚዎች ገና ያልተነኩ ሐብቶች እና የተፈጥሮ ፀጋዎች እንዳሏትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አንስተዋል፡፡

የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ጠንካራ እና ተጠያቂነት የሠፈነባቸውን ዓለም አቀፋዊ ተቋማት በመገንባት ረገድ ያስመዘገበችው ስኬት ለኢትዮጵያ መነሳሳትን እንደፈጠረም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ስትራቴጂያዊ ኢንቨስትመንት ክንድ የሆነው “የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ” በተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ውስጥ ከሚገኙ በርካታ አልሚ ተቋማት ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከተቋማቱ ጋር በታዳሽ ኃይል፣ በመኖሪያ ቤት ግንባታ እንዲሁም በግብርናው ዘርፍ በትብብር እየተሠራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ÷የኢትዮጵያ እና የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች የሁለትዮሽ ጥምረት ታዳጊ እና ያደጉ ሀገራት ለጋራ ተጠቃሚነት የሚኖራቸው ግንኙነት ምን መምሰል እንዳለበት የሚያሳይ ሞዴል ነው ብለዋል፡፡

“በሀገራቱ መካከል የሰፈነው የመተማመን፣ የመከባበር እና በጋራ የማደግ ፍላጎት ብዙ ፍሬዎችን እያፈራ ነው ፤ይህ አጋርነት እንደሚቀጥልና እንደሚሰፋም አልጠራጠርም” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸውን መልካም ምኞት ገልጸዋል።

See also  “በአሸባሪው ህወሓት” ሲደርስባቸው የነበሩ ግፎችንና የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚያወግዝ ሠልፍ በሑመራ እየተካሄደ ነው

Leave a Reply