በሀሰተኛ ሰነድ ህጋዊ ባለቤቱ ሳያውቅ ቤት በሸጠውና በተባበረው ላይ ከባድ የሙስና ክስ ተመሰረተ

በሀሰተኛ ሰነድ ህጋዊ ባለቤቱ በማያውቅበት ሁኔታ የራሱ ያልሆነን ቤት በሸጠው እና በተባበረው ግለሰብ ላይ ከባድ የሙስና ወንጀልና በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ክስ ተመሰረተ

በኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ ሀሰተኛ ስምና ሰነዶችን በመጠቀም ህጋዊ ባለቤቱ በማያውቅበት ሁኔታ 72 ካ.ሜ ላይ ያረፈ ጅምር ቤት ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ በመሸጥ ለግል ጥቅሙ ባዋለ ግለሰብና ተባባሪው ላይ ከባድ የሙስና ወንጀልና በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ክስ መሰረተባቸው፡፡

የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው 1ኛ ተፈራ አበራ፣ 2ኛ ደስታ ኑታ የተባሉ ተከሳሾች የእያንዳንዳቸው የተሳትፎ ደረጃ ተጠቅሶ በዐቃቤ ሕግ አራት ክሶች ተመስርቶባቸዋል፡፡

1ኛ ክስ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ ሲሆን ተከሳሹ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ትክክለኛ ስሙ ተፈራ አበራ ተከስተ ሆኖ ሳለ ቀድሞ ሊሰራው ላሰበው ህገ-ወጥ ተግባር እንዲረዳው ተሾመ ገዝሙ ለቺ በሚል ሀሰተኛ ስም በመጠቀም በቤተል የጋራ የመኖሪያ ቤት ህ/ስ/ማህበር አባል በሆነ ተሾመ ገዝሙ ለቺ በተባለ ግለሰብ ስም በን/ስ/ላ/ክ/ከተማ በቀድሞ ወረዳ 01 የሚገኘውን ስፋቱ 72 ካ.ሜ ላይ ያረፈ ጅምር ቤት በህገ-ወጥ መንገድ በመሸጥ ለግል ጥቅሙ ለማዋል በማሰብ፣ በተሾመ ገዝሙ ለቺ ስም በሴሪ ቁጥርና ካርታ ቁጥር የተዘጋጀ የራሱ ፎቶ ያለበት ሃሰተኛ የባለይዞታነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት በመጠቀም ቤቱን ለግል ተበዳይ መስከረም 20/2015 ዓ.ም በተጻፈ የመንደር ሽያጭ ውል በ5 ሚሊየን 50 ሺ ብር ለመሸጥ በመስማማት በዚያኑ ቀንም በፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ጽ/ቤት ቅርንጫፍ በአካል በመቅረብ የቤት ሽያጭ ውል ስምምነት በመፈጸም በሀሰተኛ ማንነት እና የይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ በመጠቀም የራሱ ያልሆነን ንብረት በመሸጥ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም በማግኘቱ በፈፀመው በሃሰተኛ መንግስታዊ ሰነዶች መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ የቀረበበት ሲሆን

በተያያዘም በ2ኛ ክስ ሃሰተኛ ሰነድ በመገልገል በፈጸመው ህገ-ወጥ የቤት ሽያጭ ውል ያገኘውን ገንዘብ ህገ-ወጥ ምንጭ ለመደበቅ እና ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ በማሰብ የሽያጩን ገንዘብ በ2ኛ ተከሳሽ ስም በተከፈተ የተለያየ የባንክ ሂሳብ ቁጥር በመጠቀም 4 ሚሊየን 900 ሺ ብር፣ እንዲሁም በሌላ ግለሰብ ስም በተከፈተ ባንክ ሂሰብ ቁጥር 150 ሺ ብር፣ በአጠቃላይ 5 ሚሊየን 50 ሺ ብር እንድታስገባለት ያደረገ በመሆኑ እና 2ኛ ተከሳሽም በአካውንቱ ከገባለት ከዚሁ ገንዘብ ውስጥ 500 ሺ ብር ያስተላለፈለት በመሆኑ በፈጸመው በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ተከሷል፡፡

3ኛ ክስ በ2ኛ ተከሳሽ ላይ ሲሆን ተከሳሽ ገንዘቡ የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቀ የባንክ ሂሳባቸውን ለ1ኛ ተከሳሽ አሳልፎ በመስጠት ህገ-ወጥ የቤት ሽያጭ ውል የተገኘውን ገንዘብ የተረከበ እና ለሌሎች ግለሰቦችም ዝውውር የፈጸመ ሲሆን ይህም በስሙ በተከፈተው ከተለያየ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ከግል ተበዳይ ከተላለፈለት 4 ሚሊየን 900 ሺ ብር ውስጥ ለ1ኛ ተከሳሽ 500 ሺ ብር እና ለሌሎች ግለሰቦችም የተለያ መጠን ያለው ገንዘብ ያስተላለፈ በመሆኑ፣ በአጠቃላይ 4 ሚሊዮን 900 ሺ ብር በይዞታው በማድረግ የተጠቀመ በመሆኑ በፈፀመው በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ክስ ተከሷል፡፡

እንዲሁም 4ኛ ክስ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ ሲሆን ተከሳሽ ያንኑ ቤት በ ህዳር 23/015 ዓ.ም በፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ጽ/ቤት ቅርንጫፍ አስር በአካል በመቅረብ ከመጀመሪያዋ ግል ተበዳይ ጋር ፈጽሞት የነበረውን የቤት ሽያጭ ውል በማፍረስ እና ከ2ኛው የግል ተበዳይ ጋር የቤት ሽያጭ ውል በመፈጸም የራሱ ያልሆነን ንብረት በድጋሚ የሸጠ ሲሆን የ2ኛው የግል ተበዳይም የሽያጩኝ ገንዘብ በውክልና ከሚያስተዳደረው ግለሰብ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ላይ ለ1ኛዋ ተበዳይ 7 ሚሊዮን ብር እንዲያስተላልፍ ምክንያት በመሆኑ እንዲሁም ከ1ኛዋ ተበዳይ በባንከ ሂሳብ ቁጥር 400 ሺ ብር ገቢ እንዲሆንለት በማድረግ ያልተገባ ጥቅም ያገኘ በመሆኑ በፈጸመው በሃሰተኛ መንግስታዊ ሰነዶች መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተከሷል፡፡

ክስ እና ማስረጃው የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ችሎትም የክስ እና ማስረጃው ዝርዝር በችሎት ለተከሳሽ ደርሶት 1ኛ ተከሳሽ በክሱ ላይ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ፣ 2ኛ ተከሳሽን ፖሊስ መጥሪያ እንዲያደርስ ለጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ፍትሕ ሚኒስቴር

Leave a Reply