“የሱዳን ተፋላሚ ሀይሎች ምንም የድርድር ፍላጎት አላሳዩም” – ተመድ

የሱዳን ጦርና የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ምንም አይነት የድርድር ፍላጎት አለማሳየታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለጸ።

በአሜሪካ እና ሳኡዲ አረቢያ አደራዳሪነት የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት በተወሰነ መልኩ እየተተገበረ ቢሆንም ተፋላሚዎቹ በንግግር ጦርነቱን ለማቆም ፍላጎት የላቸውም ብለዋል በድርጅቱ የሱዳን ልዩ መልዕክተኛ ቮልከር ፐርትስ።
ልዩ መልዕክተኛው በጸጥታው ምክርቤት ስብሰባ ላይ ከፖርት ሱዳን በቪዲዮ ተሳትፈዋል።
የሱዳን ተፋላሚ ጀነራሎች በየፊናቸው ድል እንደሚቀናቸው ጽኑ አቋም መያዛቸው ለድርድር ቦታ እንዳይሰጡ እንዳደረጋቸው ነው ፐርትስ የተናገሩት።
ይህም “የተሳሳተ ስሌት ነው” ያሉት ልዩ መልዕክተኛው፥ ከትናንት ጀምሮ ለ72 ስአት የተደረሰው የተኩስ ማቆም ስምምነትም በአንዳንድ አካባቢዎች እየተጣሰ እንደሚገኝ መረጃዎች ደርሰውናል ብለዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የሱዳንን ግጭት “ልብ ሰባሪ” ነው ያሉ ሲሆን፥ የስልጣን ሽሚያ ትግሉ ካርቱምን ለአመታት ስቃይ ውስጥ የሚከታት ስለመሆኑ አብራርተዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት በጦርነቱ ምክንያት በካርቱም የሚገኙ ሰራተኞቹን እና ቤተሰቦቻቸውን ወደ ፖርት ሱዳን አዛውሯል።
በፖርት ሱዳንም ጊዜያዊ ቢሮ በመክፈት ስራውን ለመቀጠል ማሰቡ ተገልጿል።
በሱዳን በፈረንጆቹ ሚያዚያ 15 2023 ከተቀሰቀሰው ጦርነት በፊት 16 ሚሊየን ሰዎች የሰብአዊ ድጋፍን የሚፈልጉ መሆናቸውን የድርጅቱ መረጃ ያሳያል።
ከ12 ቀናት በፊት በሱዳን ጦርና በአርኤስኤፍ መካከል የተጀመረው ጦርነትም ሚሊየኖችን የከፋ ችግር ውስጥ ሊጥል እንደሚችል የገለጸው የመንግስታቱ ድርጅት፥ ተፋላሚዎቹ ጀነራሎች ሰላማዊ ትግልን ምርጫቸው እንዲያደርጉ አሳስቧል።(አልዓይን አማርኛ)

See also  ዶላር መተካት የሚችል ገንዘብ ነው? ለምን የዓለም ጠንካራ መገበያያና የክምችት ገንዘብ ሆነ?

Leave a Reply