በኤርትራ በሚኖሩ የአፋር ተወላጆች ላይ የሚፈጸመው እስር፣ ግድያ፣ ስደት፣ ጭቆናና ግፍ ከልክ በላይ መሆኑን፣ ጥቃቱ ብሄርን መሰረት ያደረገና ዕለት ዕለት መጠኑ እየጨመረ በመምጣቱ ሻዕቢያን በሃይል የማስወገድ አማራጭ እንደሚከተሉና ለዚህም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ። የትጥቅ ትግሉ መስመር የሚይዝበት አግባብ እይተሰራበት እንደሆነም ተመልክቷል።
ሻዕቢያን በትጥቅ ለመፋለም ዝግጅት መጀመሩ ከወራት በፊት ቢሰማም የትና በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እስካሁን በይፋ የተነገረ ነገር የለም። ትግራይን መሰረት አድርጎ ከተጀመረው የወታቶች እንቅስቃሴ በተጨማሪ የቀይ ባህር አፋሮች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት የሚያስተባብረው ህብረት በወራት ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ምክክር አድርጓል።
የቀይ ባህር አፋር ዲያስፖራ ወጣቶችና ሌሎች ተወካዮች፣ በኦሃዩ ክፍለ ግዛት ኮሎምበስ ከተማ ሰሞኑን ህዝባዊ ስብሰባ አካሄደዋል። ከስብሰባው አስተባባሪዎች መኻከል ዶይቸ ቨለ ያነጋገራቸው ፣በሰሜን አሜሪካ የቀይ ባሕር አፋር ዲሞክራሲያዊ ድርጅትና ወጣቶች ተወካይ አቶ አብዱ አሚን፣ጉባዔው የተካሄደበትን አላማ አስረድተዋል።
«ዋናው ዓላማ፣ አምባገነኑ የሻዕቢያ መንግሥት በቀይ ባህር አፋር ህዝብ ላይ የሚፈጽመው ግፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተፋፋመ ስለሆነ የቀይ ባሕር አፋር ህዝብ በስደት እና የቀሩትም በእስር እየተንገላቱ ስለሆነ፣ ይህንን አፈናና ዲሞክራሲያዊ ያልሆነ ሰብዓዊ ረገጣ የሚፈጽመውን ስርዓት ለመደምሰስ ወጣቶቹ በአንድ ላይ ተነስተው የቀይ ባሕር አፋር ወጣቶች ስብሰባውን አካሄደዋል።
የጉባዔው የአቋም መግለጫ
ተሰብሳቢዎቹ ባካሄዱት ህዝባዊ ስብሰባ ማጠቃለያ ላይ ባወጡት የአቋም መግለጫ፣ የቀይ ባሕር(የዳንካሊያ) አፋር ሕዝብ ላለፉት ዓመታት አምባገነን ባሉት የኤርትራ መንግሥት ለከፍተኛ ግፍና ጭቆና መዳረጉን አስታውቀዋል። በቀይ ባሕር አፋር ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ግፍና እና ጭቆና እየተባባሰ ሄዶ፣ ወደ ብሔር ተኮር ጭቆና እና አፈና ተሸጋግሮ ይገኛልም ብለዋል።
ከዚህ ነባራዊ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት፣ የቀይ ባሕር ዓፋር ህዝብ ከዚህ አስከፊ ጭቆና እና ብሔር ተኮር አፈና ነጻ ወጥቶ፣ ሰላምና ደህንነቱን እንዲያረጋገጥ የሚያደርገው ትግልና እንቅስቃሴ በተጠናከረ ሁኔታ ማስቀጠልና ትግሉን ከዳር ለማድረስ ከምንጊዜውም በላይ ቆርጠው መነሳታቸውን ጠቁመዋል።
ሁሉም የኤርትራ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአሁኑ ወቅት ካለበት አስከፊ ስርዓት ነጻ እስከሚወጣ በሚያደርገው ሁሉን አቀፍ የህልውና ትግል በጋራ ለመታገልም በአቋም መግለጫቸው ጥሪ አቀርበዋል።
የኤርትራ ተቃዋሚ ኀይሎች
ተስብሳቢዎቹ በዚሁ መግለጫቸው፣ የኤርትራ ተቃዋሚ ሃይሎች በጋራ ለመታገል የደረሱበትን ስምምነት በጋራ እንተገብራለን ብለዋል። በዚህ ስብሰባ ላይ ከተሳተፉት መኻከል፣ የኤርትራ ተቃዋሚ ሃይሎች እንደሚገኙበት አቶ አብዱ ጠቁመዋል። «በዚህ ስብሰባ ላይ ከፍተኛ የሆኑ የቀይ ባሕር አፋር ወጣቶች ተገኝተዋል። የኤርትራ ተቃዋሚ ሃይሎችም ተገኝተዋል። ከቀይ ባሕር አፋር ሕዝብ ጎን መሆኑን ለእኛም አረጋግጠውልናል።»
በኢትዮጵያ እና በጅቡቲ የስደተኞች ካምፖች የሚገኙ የቀይ ባሕር አፋር ስደተኞችን አስመልክተው፣ ተሰብሳቢዎቹ በመግለጫቸው ወደ ሦስተኛ ሀገር የመዘዋወር ዕድል እንዲያገኙ ለሚመለከተው ሁሉ ጥሪ አቀርበዋል።
አቶ ያሲን አህመድ አብደላ፣ የቀይ ባሕር አፋር ዴሞክራሲያዊ ድርጅትን ወክለው ጉባዔው ላይ ለመሣተፍ ከስዊድን ተጋብዘው መምጣታቸውን ገልጸውልናል። ጉባኤው ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዳለውም ይናገራሉ።
ወጣቱ ለስደት ተዳርጓል
እንደ አቶ ያሲን፣ በአሁኑ ወቅት ኤርትራ ውስጥ ብዙ ግፍ እየደረሰበት እና እየተሰደደ ያለው ወጣቱ ክፍል ነው። «በአብዛኛው ወጣቱ ተሰዳጅ ነው። አሁን ብዙ ግፍ እየደረሰበት ያለው ሕዝብ ዋናው ተጠቂው አብዛኛው የቀይ ባሕር አፋር ወይም የኤርትራ ሕዝብ ወጣቱ ነው አብዛኛው። ይህ ክፍል ደግሞ ዛሬ በስደት ላይ ይገኛል።»
የተነሱ ጉዳዮችን በተመለከተ ዋሽንግተን ዲሲ ወደሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ ደውለን በሰጡን ምላሽ፣ ስለተባለው ሁሉ የሚያውቁት ነገር ስለሌለ፣ አስተያየት ለመስጠት እንደማይችሉ መግለጻቸውን የዘገበው የጀርመን ድምጽ ነው። የድምጽ ዜናውን እዚህ ላይ ያድምጡ።
እስከ ኢትዮጵያን ጅቡቲ የሚዘረጋው የአፋር ህዝብ በይፋ የአሰብ ወደብ የባለቤትነት መብት እንዳለው፣ ይህንንም ጥያቄ የኢትዮጵይ አፋሮች እንደሚደግፉ፣ አቋሙ የኢትዮጵያ መንግስትም እንደሆነ የሚታወቅ ነው።