ባልደራስ “መንግስት ሕዝብን ንቋል” አለ፤ “ራስህ ትህነግን ግጠም “

ለትህነግ ወግኖ በሚሰራው የ360 የተቃውሞ ድምጽ ባለቤት ምክትል ሊቀመንበርነት የሚመራው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ፤ ማዕከላዊ መንግስት ህወሓትን “ትግራይ ድረስ ሂዶ ማጥፋት አለበት” ሲል አስታወቀ። ፓርቲው የኢትዮጵያ መንግሥት የመከላከያ ሰራዊቱን ባለበት ጸንቶ እንዲቆይ ያስተላለፈውን ውሳኔንም ነቅፏል። ይህ መግለጫ በተሰራጨባቸው የማህበራዊ ሚዲያዎች ተቃውሞምም ድጋፍም ተሰንዝሮበታል። የባልደራስን አቋም የተቃወሙ አስተያየት ሰጪዎች እንዳሉት ባልደራስ “ውጊያ ከፈለገ ራሱ ሄዶ ትህነግን ይግጠም” ብለዋል።

ፓርቲው “መንግሥት ‘ምዕራፍ አንድ’ ያለውን ዘመቻ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሳያረጋግጥ ማቆሙ፤ ትልቅ አደጋ ያዘለ ነው” ሲል ስጋቱን ገልጿል። ህወሓት አሁንም የሀገሪቱን አንድነት ሊፈታተን በሚችል ወታደራዊ ቁመና ላይ ይገኛል” ያለው ባልደራስ፤ መንግሥት “ዘመቻውን ያቆመበትን ምክንያት በተመለከተ በቂ ምላሽ አልሰጠም” ሲል ተችቷል። የፌደራል መንግሥቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ “ንቀት እያሳየ ነው” ሲልም ነቅፏል፡፡

ፓርቲው በመግለጫው እንዳስታወቀው አሸባሪው ህወሓት በጀመረው ጦርነት ምክንያት ሀገራችን ኢትዮጵያ የህልውና ትንቅንቅ ላይ እንደምትገኝ ጠቁሟል፡፡ በዚህም አገርን ለማስቀጠል በተደረገው መስዕዋትነት ፓርቲው ግንባር ድረስ በመሄድ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱንም አስታውቋል፡፡

የሰሜኑ ጦርነት መነሻ አሸባሪው ህወሓት በጀመረው የቅድመ-ማጥቃት እርምጃ መሆኑን እንረዳለን ያለው መግለጫው፣ የፌደራል መንግስት ጥቃቱን ለመከላከል ያደረገው ሀገር አቀፍ ዘመቻ ትክክለኛና ፍትሃዊ እንደነበርም ጠቁሟል፡፡ አሸባሪው ህወሓት አሁንም የአገሪቱን አንድነት ሊፈታተን በሚችል ወታደራዊ ቁመና ላይ ይገኛል ያለው መግለጫው፣ የዘመቻው ፍፃሜ የኢትዮጵያን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥለውን የህወሓት ወታደራዊ አቅም በመስበር መቋጫት ይገባል ብሏል፡፡

ከምክክር ኮሚሽኑ ጋር በተያያዘ መንግስት እያካሄደ ያለው እንቅስቃሴ የአገራችንን ፖለቲካዊ ጥያቄዎች በውይይትና በምክክር ለመፍታት ትልቅ እድል እንደሚፈጥር የጠቆመው መግለጫው፣ የምክክር ሂደቱ አትዮጵያን አሸናፊ በሚያደርግ መልኩ እንዲጠናቀቅ እና ግልፀኝነት የተሞላበት ምክክር እንዲሆን ፓርቲው የበኩሉን አስታዋፅኦ እንደሚያደርግ አስታወቋል፡፡

የባልደራስን መግለጫ ተከትሎ መግለጫውን በመደገፍ የተናገሩ ሲሆን ሌሎች ግን ራሳቸው ሄደው የማይዋጉትን ጦርነት መከላከያው ይሂድ ብለው መወሰን አግባብ አይደለም በሚል ነቅፈዋል። በአማራና አፋር የመንደር ሚሊሻዎች ሳይቀሩ ትህነግን ሲዋጉ እንደነበር ባልደራስም እንዲሁ የራሱን ሚሊሻ አስተባብሮ ትህነግን መግጠም ይችላል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ጦርነት አገሪቱን ወደ ገደል እየነዳት በመሆኑ፣ አገሪቱን እየፈተናት ያለው ትህነ ሳይሆን በረካታ እጆች መሆናቸው፣ አገሪቱን ለማተራመስ ሰፊ ሃብት እየተረጨ መሆኑ፣ ከሁሉም በላይ የደረሰው ውድመትና ጥፋት፣ የሚገታበት ሁኔታ ሊፈጥርና፣ ደፋር ውሳኔ ሊወሰን እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎች ሲናገሩ እየተሰማ ነው።

Leave a Reply