የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ መግለጫ
የአማራ ክልል የትግራይን መሬት በካርታው ላይ በማስፈርና በስርዓተ ትምህርቱ ላይ በማካተት እያስተማረበት እንደሚገኝ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ተረድቷል።
ክልሉ ይሄንን የትግራይ መሬት በስርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ማካተቱ ሃላፊነት የጎደለው ተግባር ብቻም ሳይሆን የትግራይን ህዝብ ቆራርሶ የማጥፋቱ ዘመቻ እንዳይቆም በከፋ መልኩ እየተሰራበት እንደሚገኝ የሚያረጋግጥ ተግባር መሆኑንም ተገንዝበናል።
የአማራ ክልል መንግስት በህዝባችን ላይ ሲፈፅም የነበረውን ግፍና አሁን በሃይል ተቆጣጥሮ በያዛቸው የትግራይ መሬቶች ውስጥ እየፈፀመ ያለውን ግፍና መከራ ሳያቆምና ለፈፀማችው በደሎች ሳይፀፀት እንዲህ በመሰለ ታሪካዊ ስህተተ ውስጥ መግባቱ በቀጣይ ዋጋ እንደሚያስከፍለው አውቆ ከወዲሁ በአስቸኳይ ከስራው ሊታቀብ ይገባል።
የፌዴራል መንግስትም ቢሆን ከዚህ በፊት በፌዴራል ተቋማት አማካኝነት አሁን ደግሞ በክልሎች አማካኝነት እየተዘጋጁ ያሉ ሃላፊነት የጎደላቸውን ካርታዎች ሊያስተካክልና በአጥፊዎቹም ላይ እርምጃ መውሰድ ሲገባው አይቶ እንዳላየ ማለፉ ራሱ መንግስት የዚህ ጥፋት አንደኛው አካልና ተዋናይ መሆኑን የሚያመላክት ነው።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርና ህዝብ የፕሪቶሪያው ስምምነት ተግባራዊ ሆኖ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እየተጋ ባለበት ባሁኑ ወቅት የአማራ ክልል መንግስት እየፈፀመ ያለው አሉታዊና ተንኳሽ ስራ የሰላም ሂደቱን ለማወክ ሆነ ብሎ ያደረገው መሆኑን ሊሰመርበት ይገባል።
የአማራ ህዝብና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የአማራ ክልል መንግስት በትግራይ ህዝብ ላይ እየፈፀመ የቆየውንና አሁንም በመፈፀም ላይ ያለውን ግፍና በደል እንዲቆም ጥሪ በማስተላለፍ ከትግራይ ህዝብና ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጎን እንዲቆም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ።
ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን ቀጥሎ ለሚመጣው ነገር ሁሉ ሃላፊነቱን የሚወስደው እራሱ የአማራ ክልል መሆኑን ማሳወቅ እንወዳለን።
- የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ
- መጋቢት 16/ 2016 ዓ.ም መቀሌ