ኦነግ ሸኔ “እንነጋገር ” ሲል ለኦሮሚያ ክልል ገዢ ፓርቲ አማላጅ ላከ

ከኤርትራ ወደ አዲስ አበባ ከገባ በሁዋላ በውል ባልተቀመጠ ጭብጥ ወታደራዊ ክንፉን የሚመሩት የኦነግ አመራሮች “ሸኔ” የሚለውን ስም ይዘው የትጥቅ ትግል መምረጣቸው በራሳቸው መገለጹ ያታወሳል።

ይህ ከአቶ ዳውድ ኦነግ ውጣ የሚባለው ክፍል ራሱን ” የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሰራዊት” ሲል ቢጠራም መንግስት ቀደም ሲል በያዘው “ሸኔ” የሚል መጠሪያ ይጠራዋል።

ይህ ታጣቂ ቡድን በተለይም በወለጋ ዘርን መሰረት ባደረገ ተደጋጋሚ ግድያ የሚከሰስ ቢሆንም፣ የሰለባዎች ቤተሰቦችና በስራው የሚኖሩ ምስክሮች “ኦነግ ሸኔ” በሚል እየጠሩ የሚወንጅሉት ቡድን በተደጋጋሚ በቪኦኤ የማስተባበያ መድረክ እየተዘጋጀለት ” ከደሙ ንጹህ ነኝ” ሲል ማስታወቁ ይታወሳል።

ከትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ጋር በይፋ ግንባር መፍጠሩን ያወጀው ሸኔ፣ ለኦሮሚያ ገዢ ፓርቲ “እንነጋገር” ሲል አማላጅ እንደላከ የኢትዮ12 መረጃ አቀባዮች አስታውቀዋል።

ሸኔ ይህን ጥያቄ በይፋ ከማቅረቡ በፊት በተለያዩ የክልሉ አንጋፎችና ሽማግሌዎች ወደ ንግግር እንዲመጣ ጥረት ሲደረግ ነበር። መረጃውን የሰጡት አካላት አሁን ላይ ለመነጋገር ጥያቄ ሽማግሌ የላከው የሸኔ ቡድን በጃል መሮ የሚመራውና ስሩ ኡጋንዳ ያለው ቡድን ነው።

የክልሉ ገዢ ፓርቲ በግልጽ የሰጠው ምላሽ ባይታወቅም፣ ትህነግ የጦር አቅሙ ከፈረሰና የተረፈውም ወደ ሰላማዊ መንገድ ከተመለሰ ሸኔ አቅም አልባ ስለሚሆን አባላቱ ትጥቅ ፈተው እጅ መስጠታቸው ግድ እንደሚሆንባቸው እምነት አለ።

በቤኒሻንጉል ብረት አንስቶ ጫካ የመሸገው ሃይል ሰላም አውርዶ ብረቱን ከጣለ በሁዋላ ፣ የትህነግና መንግስት ንግግር ቀጠሮ በተቃረበበት ወቅት ሸኔ ሽምግልና መጠየቁ ከስጋት ቢሆንም የአገሪቱን ሰላም አስተማማኝ ከማድረግ አንጻር ጥያቄውን አስተናግዶ ፍትህ የሚሰፍንበት ንግግር ማድረግ ጉዳይ የለውም ብለው እንደሚያምኑ መረጃውን ያጋሩን ክፍሎች ተናግረዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መሪዎች እንደሆኑ የሚገልጹትና በውጭ አገር ያሉት ክንፎች በዚህ ጉዳይ ይኑሩበት አይኑሩበት የመረጃው ባለቤቶች አላስታወቁም። እነ ፕሮፌሰር ሕዝቄልም ቢሆኑ ዘወትር በሚቀርቡበት የትህነግ ሚዲያዎች ቀርበው ያሉት ነገር የለም። እንደ ዜናው ሰዎች ግን ወታደራዊ ክንፉ የያዘው አቋም ይፋ መሆኑን ተከትሎ ልዩነታቸው ይፋ እንደሚሆን ነው።

See also  ሦስተኛው የቱርክ እና አፍሪቃ ግንኙነት ጉባኤ « ለጋራ እድገት እና ብልጽግና የጎለበተ ወዳጅነት»

የሸኔ ትጥቅ አንስቶ ውጊያ መጀመር የአቶ ዳውድን ኦነግ ቁጥር አምስት ለሁለት እንደከፈለው ይታወሳል። የእነ አቶ ቀጀላ መርዳሳ ቡድን “በሰላማዊ ትግል እየማሉ ጦርነት ማራመድ ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ የያዝነው አቋም አይደለም። ሰላማዊ ትግል ብቻ ነው የምንፈልገው” በሚል የአነ አቶ ዳውድ ቡድን በሁለት ኳስ እንደሚጫወት ጠቅሰው መሰንጠቃቸው ይታወሳል። አቶ ዳውድ በበኩላቸው ወቀሳውን አጣጥለው በዲሲፒሊን ግድፈት መባረራቸውን ማመልከታቸው አይዘነጋም።

ሸኔ የንግግር ጥያቄ ስለማቅረቡ ለማጣራት የአዲስ አበባው ተባባሪያችን ያደረገው ጥረት አልተሳካም። ይሁን እንጂ ሙከራው አዲስ እንዳልሆነና ሲሰራበት የቆየ መሆኑንን የሚያውቁ በዜናው አለመገረማቸውን፣ ይልቁኑም መዘግየቱን አመልክተዋል። አባገዳዎች በክልሉ ዕርቅ እንዲወርድ ጫካ ድረስ እየዘለቁ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ሲገለጽ ነበር።

Leave a Reply