ለኢፌዴሪ አየር ሃይል እንደተጻፈ ተደርጎና በቅንብር ተሰርቶ ማህበራዊ ሚድያ ላይ የተሰራጨ ደብዳቤ ቅጥፈት ነው

“በአስቸኳይ ሽፋን እንድትሰጡን” በሚል ርዕስ ለኢፌዴሪ አየር ሃይል እንደተጻፈ የሚገልጽ ደብዳቤ ባለፉት ሁለት ቀናት በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት ሲሰራጭ ተመልክተናል። በርከት ያሉ ሰዎችም የደብዳቤውን ትክክለኛነት በተመለከተ አስተያየታቸን ሲሰጡ አስተውለናል።

ኢትዮጵያ ቼክ የደብዳቤውን ትክክለኛነት ለማወቅ በደብዳቤው ላይ ምርመራ አድርጓል፣ የፎቶፎረንሲክ ፍተሻ አካሂዷል እንዲሁም የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊትን አነጋግሯል።

በደብዳቤው ላይ ባደረግነው ምርመራም በርከት ያሉ ግድፈቶች መኖራቸውን አስተውለናል።

በደብዳቤው ላይ ሌ/ጄነራል ጌታቸው በቀለ የሰ/ምዕ እዝ አዛዥ መሆናቸው ተገልጿል። ነገር ግን የሰ/ምዕ እዝ አዛዥ ሌ/ጄነራል ብርሃኑ በቀለ እንጂ ሌ/ጄነራል ጌታቸው በቀለ አይደሉም።

በተጨማሪም በደብዳቤው ላይ “የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ” የሚል ማህተም ያረፈ ሲሆን ይህም ደብዳቤውን ጻፈው ከተባለው የሰ/ምዕ እዝ ጋር የሚጣረስ ነው።

ጉዳዩን በተመለከተ ኢትዮጵያ ቼክ ያነጋገራቸው የኢፌድሪ መከላከያ ሠራዊት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ የተሰራጨው ደብዳቤ “ውሸት ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

“ውሸት መሆኑን በአንድ ነገር ብቻ ላረጋግጥ! ጠየቁ የተባሉት ሌ/ጀነራል ብርሃኑ በቀለ ዕዝ አዛዥ ናቸው፡፡ ማህተሙ ግን የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ የሚል ነው፡፡ ኮንስትራክሽን ድሮን አይጠይቅም የግንባታ ዕቃ እንጂ! ደግሞም እንኳን ጥያቄ የሌለውን ቢኖር በወታደራዊ የመገናኛ ሬዲዮ ተመስጥሮ እንጅ በእንደዚህ አይነት ዘፈቀደ ደብዳቤ አይደለም” በማለት ሃላፊው አብራርተዋል።

ይህን ደብዳቤ በተመለከተ ኢትዮጵያ ቼክ ስሙ በማህተሙ ላይ የሚታየው የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝን ምላሽም የጠየቀ ሲሆን ደብዳቤው የድርጅቱ እንዳልሆነ የሚገልጽ ምላሽ አግኝቷል።

በመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ከፍተኛ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ የሆኑት ማርታ ተፈሪ ደብዳቤው “የኛ አይደለም፤ እንደዚህ አይነት ደብዳቤ ከድርጅታችን አልወጣም” ሲሉ ለኢትዮጵያ ቼክ ነግረዋል።

“ደብዳቤው የተደራጀ የደብዳቤ ፎርማት የለውም፤ ፕሮቶኮልም የለውም” ሲሉም ነግረውናል።

ኢትዮጵያ ቼክ ይህንኑ ደብዳቤ በፎቶፎረንሲክ መገልገያ የመረመረ ሲሆን የተነካካ ወይም በቅንብር የተሰራ መሆኑን መመልከት ችሏል።

#EthiopiaCheck Fact Check

See also  ኢመደበኛነት ባንዳነት - ምሳሌ ለክህደትና ለመሸጥ የተወለደው ትህነግ

Leave a Reply