ኢትዮ 12 ዜና – የቀድሞው የትግራይ ክልል መሪ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ድምጽ እንደሆነ ተገልጾ ይፋ ሲደረግ በርካታ የውጭ ሚዲያዎች አስቀድመው የጠቀሱት ” ድምጹን ማረጋገጥ አልቻልንም” በሚል ነው። ቢቢሲ፣ሬውተርስ፣ ጀርመን ድምጽ የመሳሰሉት ሚዲያዎች እርግጠኛ ባይሆኑም ድምጸ ወያኔን ጠቅሰው ነው የተጠራጠሩትን ድምጽ ዜናና ዘገባ ያደረጉት።

የህግ ማስከበሩ ከተጀመረ በሁዋላ ሚዛናዊ ዘገባ እንደማይዘገቡ ከሚጠቀሱት ሚዲያዎች መካከል አንዱ የሆነው ሬውተርስ ” ትክክለኛ እንደሆነ አላረጋገጥኩም” ሲል የገለጸውን መረጃ ይዞ ነበር ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ጥያቄ ያቀረበው። በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም “ለወንጀለኛው ቡድን የፌስቡክ ገጽ የተወዛገቡ ሐሳቦች መልስ አልሰጥም” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።

ቢልለኔ እግረመንገዳቸውን ህወሓት እና የውጪ ደጋፊዎቻቸው ከጥቅምት ወር ጀምሮ የራሳቸውን አስከፊ ወንጀሎች ለመሸፋፈን “የዘር ማጥፋት እየተፈጸመ ነው የሚል ያልተጨበጠ ወሬ እየነዙ ነው፤ አጋልጧቸው” ሲሉ ጠይቀዋል። 

የመከላከያ ሰራዊት መቀለን ከተቆጣጠረ በሁዋላ ለመጨረሻ ጊዜ ከተደበቁበት ቦታ ሆነው በድምጸ ወያኔ ቲቪ ሰማያዊ የእጅ ጓንቶች አጥለው እምባ እያቀረሩ ለፌደራል ሃይሎች ” ድረሱልን” ሲሉ ጥሪ አቅርበው የነበሩት ዶክተር ደብረጽዮን ጦርነቱን “ህዝቡ ራሱን በራሱን የማስተዳደር መብቱን በተግባር ለማረጋገጥ በፅናት ስለታገለ የተቃጣበት ጦርነት” ነው ቢሉም ባስተላለፉት ያልተረጋገጠ ድምጽ ለፌደራል ሃይሎች እንደቀድሞው ጥሪ ስለማቅረባቸው አልተሰማም። ይልቁንም አራት መንግስታትና የክልል ልዩ ሃይሎች ተሳትፈው ስለነበር የሃይል አለመጣጣም መከሰቱን በመጥቀስ የፌደራል ሃይሎችም እንደወጓቸው ነው ያመለከቱት።

አሁንም ” ትምክህተኛ” ሲሉ የአማራውን ሕዝብ በሚኮንን መልኩ ሃሳባቸውን ያሰራጩት የትህነግ መሪ፣ “የህወሃት መስራች አባላት ከሚባሉት ላለፉት 45 ዓመታት ከያዙት ህዝባዊ መስመር ፈቀቅ ሳይሉ የታገሉና የመሩ፣ ያታገሉና ብዙ ድል ያስመዘገቡ አዛውንት ነባር ታጋዮች በዚህ የወረራ ጦርነት፣ በጠላት እጅ ተጎድተውብናል። ከባድ መስዋዕትነት ከፍለዋል። አሁንም እየከፈሉ ይገኛሉ። የነዚህ ጀግኖቻችን መስዋዕትነት የበለጠ ቁጭትና እልህ ያስንቀናል እንጂ ፈፅሞ ከትግላችን የሚያቆመን አይሆንም።” ማለታቸውን የጀርመን ድምጽ ትርጉም ያስረዳል።

ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን የመከላከያ ሃይል ” የጠላት ሃይል ” በማለት የገለጹት የትሀንግ ሊቀመንበር ለሁለት አስርት ዓመታት ትግራይንና ህዝቧን ከጠላት ሲጠብቅ የኖረን ሰራዊት ” አቶ ሴኮ ቱሬ በአርባ አምስት ደቂቃ ደምስሰነው፣ ከጥቅም ውጭ አድርገነዋል” ሲሉ እንደ ባዕድ ሃይል ያጣጣሉትን የአገር ሰራዊት ” ጠላት መባሉ ድርጊቱ ከተፈጸመ ጀምሮ ዛሬ ድረስ ሕዝብን እንዳስቆጣ፣ ጦርነቱ በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ እንደሚደገፍና መንግስትን በሚችለው ሁሉ እንደሚረዳ ዛሬ ድረስ እንዳልተረዱ የሚያሳየው መልዕክት ተማጽኖ ታሰማው ለውጭ አገር ሚዲያዎችና አገሮች ነው።

እንደ ማርቲን ፕላውት የመሳሰሉት የትሀንግ አፍቃሪ የሚዲያ ሰዎች ይህንኑ የድምጽ መልዕክት የንግሊዝኛ ትርጉም በስፋት አደራውን በመቀበል እያሰራጩ ነው። ከትርጉሙ ስርጭት ጎን ለጎን የተናበበ በሚመስል መልኩ የተለያዩ ተቋማት ሪፖርቶች አብረው እየቀረቡ ነው።

ደብረጽዮን በሃሳባቸው የሴቶች መደፈር፣ የሰብአዊ መብት መጣስ፣ ህዝቡ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መውደቁን ገልጸዋል። ህዝቡ ላይ እየተፈፀመ ነው ያሉትን ወንጀል በግልፅ እንዲቃወምና እንዲያወግዝ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጥሪ አቅርበዋል። ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ ተፈፀመ ያሉት ወንጀል በገለልተኛ አካል እንዲጣራና ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀው ለዚህ ተጠያቂ ናቸው ብለው የጠሯቸውን የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎች ወደ አለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት መቅረብ እንደሚገባቸው አስታውቀዋል።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለዓለም ዓቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የጠየቁት ደብረጽዮን በማይክድራ ስለተጨፈጨፉት ወገኖች ያሉት ነገር የለም። አስቀድሞ ሳንጃና አበል በመስጠት፣ ነዋሪዎቹ ከቤት እንዳይወጡ በማድረግ በማይክድራ የጠጨፈጨፉ ወገኖች ጉዳይ ያላነሱት የትግራይ ክልል የድሮው ሊቀመንበር፣ በምሽት በተኛበት ስለተጨፈጨፈው፣ ስለታረደው፣ አስከሬኑ ላይ ስለተጨፈረበት፣ እንደ ባዕድ ወረራ ተካሂዶበት ለስለተሰደው፣ እጅና እግሩ ታስሮ ገደል ስለተጨመረው የአገር መከላከያ ሰራዊት ጉዳይም ገልለተኞች እንዲያጣሩት የሚል ሃሳብ አላነሱም።

“እኛ ከመሬታችን እና ከቀያችን ለቀን የምንሄድበት ሌላ ቦታ የለንምና የተሟላ ድል እስክንቀዳጅ ህዝባዊ ጦርነት ከማፋፋም ወደ ኋላ እንደማንል ወዳጅም ጠላትም ሊያውቀው ይገባል።” ሲሉ ትግሉ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። እሳቸው ይህንን ባሉ ቀን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከሰባት መቶ በላይ የቀድሞ ፖሊሶችን የተሃድሶ ትምህርት ሰጥትቶ ወደ ስራ መመለሱን አመክቷል።

ክሁለት ቀን በፊት ለኢቲቪ መግለጫ የሰጡት ኤታማዦር ሹም በሃኑ ጁላ ” ህወሃት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተደምስሷል” ካሉ በሁዋላ ” አልፎ አልፎ ተበትኖ የሚወራጭ ሃይል አለ። እሱም የድመሰሳል። በዚህ ዘመን ጎሬላ እሆናለሁ ብሎ ካሰበ ያስገርመል። ሁውላ ቀርነት ነው” ማለታቸው ይታወሳል። እዛም እዚህም ችግር ሊፈጥር ቢሞክርም መጨረሻ ላይ እንደሚደመሰስ ገልጸዋል።

በሕግ ማስከበሩ የተሳተፉት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ባህር ሃይል ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ ከመከላከያ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ” ማሰብ ያምይችሉ፣ የትግራይን ህዝብ የማይመጥኑ፣ የሚያውቁ የሚመስላቸው ነገር ግን ምንም የማያውቁ ” ሲሉ የገለጿቸው የትህነግ ሰዎች ” የትግራይ ሕዝብ ጦርነት ባህላዊ ጨዋታው ነው ሲሉ ሰድበውታል” ብለዋል።

የትግራይ ሕዝብ ጦርነት የሰለቸው፣ ጦርነትን የሚጸየፍ እንጂ ጦርነት ናፋቂ እንዳልሆነ ያመለከቱት ጄነራሉ ” ውጊያ ምክንያት ይፈልጋል፤ እኛ ወገን አለን ብለን በተኛንበት መረሸናችን ፍትህ እንድንጠይቅ አድርጎናል፤ ያ ስሜትና እልህ ከተነደፈው ልዩ ስትራቴጂ ጋር ተዳምሮ ለድል አብቅቶናል፤ እነሱ ሊወጉን የተነሱበት ምክንያት ስለሌላቸው ተሸንፈዋል። የትግራይ ሕዝብም ከፍተኛ ድጋ አድርጓል” በማለት በመከላከያ ቲቪ የጦርነቱን ትንታኔ በሰጡበት ወቅት መናገራቸው አይዘነጋም።

ፎቶ የኢትዮጵያ መከላከያ በምዕራብ በኩል የአገሪቱን ድንበር ለመከላከል ከትግራይ ውስን ሃይል ሲያንቀሳቅስ በታገተበት ወቅት


Leave a Reply