ምን ተማርን? ምንስ አጣን? (በላይ ባይሳ)


This image has an empty alt attribute; its file name is img_4307.jpg

የዛሬ አመት (ትላንት) ይሄን ጊዜ ጋሽ ኮረና በሃገራችን በመታየቱ ምክንያት የነበረው ድንጋጤ፣ ግርግር፣ ወከባ እና ጥንቃቄ እጅግ ከፍተኛ ነበር።

ምስጋና ለፈጣሪ ይብዛለትና ምህረቱ እጅግ በዝቶልን እንደኛ መዘናጋትና ቸልተኝነት ሳይሆን በፈጣሪ ምህረትና እርዳታ የወረድሽኙ አቅም ወደኛ ሃገር ሲመጣ ከተፈራውና ከተጠበቀው በታች ሊሆን ችሏል (ለምን? ለሚለው ጥያቄ ግን የዘርፉን ባለሞያዎች ጥልቀት ያለው ጥናትና ምርምር ይጠይቃል)።

ይሁንና አደጋው ምንም ጉዳትና ማህበራዊ መናጋት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ መስተጓጎል አላስከተለም ማለት ግን አይደለም። ብዙ ጠባሳ ጥሏል።

ልክ በአመቱ ትላንት ክትባቱ በሃገራችን መጀመሩ ደግሞ ሌላኛው ታሪካዊ ግጥምጥሞሽ ነው። ክትባቱ መገኘቱ አንድ ተስፋ ሲሆን ጥንቃቄውን አጠናክሮ መቀጠሉ ደግሞ ሌላኛው የመከላከያ መፍትሄ እና ሃላፊነትም ጭምር ነው።

በነገራችን ላይ በቫይረሱ ጤናቸው የተጎዳ እና ህይወታቸውን ያጡ እንዳሉ ሁሉ ቁጥራቸው ብዙ ባይሆንም ችግሩ መልካም አጋጣሚ ፈጥሮላቸው ከፍተኛ ገቢ በማግኘት ህይወታቸው የተቀየረ መኖራቸውንም ማሰቡ ተገቢ ነው። አንዳንዱ ሲታገል አንዳንዱ ደግሞ ይታደለዋል ይሉሃል ሄው ነው። ለዚህም አይደል ” It is a blessing in disguise” የሚባለው። አጋጣሚው አለም ምን ያህል ፍትሃዊ አለመሆኗን ጭምር ማሳያ ነው። ለአንዱ ጪቶ ለሌላው ሽቶ!

የዛሬ አመት ደግሞ ከአሁኑ የተሻለ ሌላ ተስፋ ይዞ እንደሚመጣ ይጠበቃል (ተስፈኞችም አይደለን?)።

ግን ኮረና ምን አስተማረን?


 • ከርቀት መስራትን
 • በርቀት መሰብሰብን
 • ከቤት ሆኖ መማርን
 • ቴክኖሎጂ መጠቀምን
 • ጥንቃቄ ማድረግን
 • የሰው ልጅ ምንም ዘምኛለሁ ቢልም ደካማ መሆኑን እና ለችግሮች ሁል-ዓቀፍ እውቂያ እንደሌለው ክስተቱ አመላክቷል
 • የሰው ልጅ ችግሩን ሊፈታ የሚቻለውን እና መፍትሄ ናቸው ያለውን ሁሉ ለማድረግ ከሰማይ በታች ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን
 • አለም በአንድ ተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ወጥነት ያለው ስምምነት እንደሌለው አስረግጧል
 • እኔነትንና ግለኝነትን አጠናክሯል
 • ካላስፈላጊ እንቅስቃሴ ራስን መግታትን አስተምሯል
  -ለሌሎች መጠንቀቅን
 • እጅ መታጠብን ወዘተ… አስተምሮ አልፏል።

ምናችንንስ ጎዳው?


 • ማህበራዊ ግንኙነታችንን በእጅጉ አውኳል
 • የለት-ተዕለት ተግባራችንን አስተጓጉሏል
 • የስነ-ልቦና ጥንካሬያችንን ፈትኖናል
 • ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ወገኖቻችንን ነጥቆናል
 • ፍርሃት አንግሷል
 • ለኢኮኖሚያችን በእንቅርት ላይ … ሆኗል ወዘተ…

ሲጠቃለል ወደፊት ትምህርት ቤት መሄድ (በአብዛኛው ወላጆችን ባያስማማም)፣ ለስብሰባ ወደ አዳራሽ መጓዝ፣ ስራ ለመስራት መስሪያ ቤት በአካል መገኘት፣ አንድ ጉዳይ ለመፈፀም በአካል የመንግስትም ሆነ መንግስታዊ መ/ቤት መሄድ፣ ማህበር ለመጠጣት፣ የዕድር ለመክፈል፣ ቅርጫ ለማረድ እና እቁብ ለመጣል … ወዘተ በአካል መገኘት ሊቀር ይችል ይሆን?

አንዘናጋ!

በላይ ባይሳ
መጋቢት 5/2013 ዓ.ም

Leave a Reply