ታዋቂው ግብጻዊ ፓለቲከኛ ኢትዮጵያን ስለማተራመስ

– ኢትዮጵያ ውስጥ ኤምባሲ አያስፈልገንም

– ፍትሃዊ የውሃ ድርድር የሚለው አያዋጣንም

– ይልቁንም በውስጥ ጉዳያቸው በመግባት ሀገሪቷን ማተራመስ አለብን

በግብጽ በጣም ታዋቂ ፓለቲከኛ ነው። በአገሪቷ የ2005ቱ ምርጫ የቀድሞውን ፕሬዘዳንት ሆስኒ ሙባረክን የተገዳደረ ብቸኛው ሰው ሲሆን የግብጽ ፓርላማ አባልም ነበር።

የኤል ጋህድ ፓርቲ መስራችና ለሊቀመንበር ሲሆን በግብጽ ካሉ ከባድ ሚዛን ፓለቲከኞች አንዱ ነው፤ አይማን አብድልአዚዝ ኑር።

ይህ ግብጻዊ ፓለቲከኛ በይፋ በሚናገርበት አንድ ቪዲዮ ያስተላለፈው መልዕክት አሁን በኢትዮጵያ ላይ ከሚታዩት የጽንፈኞችና አሸባሪዎች ድርጊት ጀርባ ግብጻዊያን የደህንነት ሰዎች እጃቸው እንዳለበት አመላካች ነው።

ግለሰቡ በዚሁ ስብሰባ ላይ “ይህንን ጉዳይ በግል መናገር ይኑርብኝ አይኑርብኝ አላውቅም፤ ነገር ግን ከእኔ በፊት እንደተናገሩት ጓደኞቼ ሁሉ እኔም የምለው በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን የሚታዩ ለውጦችን መጠቀም አለብን” ሲል ይናገራል።

በአትዮጵያ ውስጥ በርካታ የፖለቲካ ተፎካከሪዎች አሉ በማለት እነዚህን ሃይሎች መጠቀም እንደሚገባ የሚጠቅሰው አይማን አብድልአዚዝ፤ “ኢትዮጵያ ውስጥ ኤምባሲ አያስፈልገንም ይልቁንም የሚያስፈልገን በፖለቲካ እና በደህንነት ጉዳዮች ላይ የሚሰራ ግብረ ሃይል ነው” ሲል እቅዳቸውን በግልጽ አስቀምጧል።

በኢትዮጵያ ሁሉም ጉዳዮች ላይ የራሳችንን ሚና መጫዎት አለብን፤ እኔ እንደማስበው ስጋታችንን ለመቀልበስ በጣም አዋጭና በትንሽ ዋጋ የምንጠቀምበት አማራጭ ይህ ነው፤ በኢትዮጵያዊያን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ሀገሪቱን ማተራመስ አለብን ” ሲልም ነው አይማን አብድልአዚዝ ኢትዮጵያን ስለማተራመስ መልዕክቱን በግልጽ ያስተላለፈው።

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጸሙ የንጹሀን ግድያዎች በአሸባሪዎቹ ሸኔ እና ህወሓት የሚፈጸሙ ቢሆንም በዋናነት ከእነዘህ ግድያዎች ጀርባ መንግስት እና የተለያዮ የፓለቲካ ተንታኞች በተደጋጋሚ የውጭ አገራት እጅ እንዳለበት እያስታወቁ ይገኛሉ።

በተመሳሳይም ሱዳን የፈጸመችው የድንበር ወረራና ትንኮሳ የሶስተኛ አገር አጀንዳን ለማስፈጸም እንደሆነ ሲነገር ሰምተናል።

በቅርቡ አስተያየት የሰጡ ረ/ፕሮፌሰር ጌትነት አልማው እንደሚሉት የኢትዮጵያ እድልና ፈተና ከሶት ነገሮች ጋር የተያያዘ ነው። ቀይ ባህር፣ አባይ እና አድዋ ናቸው።

እነዚህ ሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ስለኢትዮጵያ እድልም ተስፋም ናቸው የሚሉት ረ/ፕሮፌሰሩ አሁን ላይ የሚያጋጥሙን ፈተናዎች ከነዚህ ጉዳዮች ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው እና ግብጽን ጨምሮ በቀጠናው የበላይነት ለመያዝ የሚጥሩ ሃይሎች የፈተናዎቻችን ምንጮች እንደሆኑ ያብራራሉ።

ይህንን የረ/ፕሮፌሰሩን ሃሳብ የሚያጠናክረው ደግሞ “በኢትዮጵያ ኤምባሲ ከፍተን የምናደርገው ድርድር በአባይ ላይ ያለንን ጥቅም አያስጠብቅልንም፤ ይልቁንም ኤምባሲያችንን ዘግተን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የደህንነት ስራችንን በማጠናከር ሀገሪቱን ማተራመስ አለብን” የሚለው የግብጻዊያን ፓለቲከኞች ምክክር ነው።

ይህንና መሰል መረጃዎችን ኢፕድ ከዚህ ቀደምም ወደናንተ ማድረሱ የሚታወስ ነው።

Via – http://www.press.et

Leave a Reply