የአንድ ሀገር የስነልቡና ፅናት ከወቅቱ መንግስት፣ ከዕዳውና ከውጭ ንግዱ በላይ ስለሆነ በሐሰት ትርክት፣ በመሰረተቢስ መጣጥፍ፣ በማህበራዊ ድረ ገጾች በዘፈቀደ በሚሰነዘሩ ስድቦች እና እንቶፈንቶዎች የኢትዮጵያና ሕዝቧ አይበገሬነት ሊሟሽሽ ወይም ሊሞት እንደማይችል አውቀን በአንድነት እንጓዝ።

 ነጻ አስተያየት – ሰማነህ ታ.ጀመረ

“የአውሮፓ ሕብረት ከዚ ቀደም የያዘውን አቋም በማጤን ምርጫውን የሚታዘቡ ኤክስፐርቶችን የመላክ ፍላጎት እንዳለው አሳውቆናል። ሩሲያም ምርጫ 2013 እታዘባለው ብላለች።” ሲሉ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል። ይህን በተመለከተ ታዛቢና ባለሙያ መካከል ያለው ልዩነቱ ምንድነው የሚል ጥያቄ ላቀረቡልኝ ጓደኞቸ ‘አጭሩ መልስ ምንም ልዩነት የለውም ነው።

በረዥሙ ሲታይ ምዕራቡ ዓለም አስራ አንደኛው ግንፍል ማህበረሰብ መሆኑን ተረድተንበታል። በማናለብኝነትና በችኩልነት የሚወስን ማህበረሰብ እንደሆነም ተገንዝበንበታል በዬ አምናለሁ። በተጨማሪ በሩስያ ውሳኔ ቀንተው የወሰኑትም ሊሆን ይችላል። ለማንኛውም የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው ለሚለው የዘልማድ ንግግር ግን ጥሩ ማሳያ ነው።

ሲጀመር የውሳኔአቸው ዓላማ ኢትዮጵያን በማስፈራራት ተንበርክካ እንድትለምናቸው ለማድርግ ታልሞ የተደረገ ነበር። ግን ኢትዮጵያ ዘዎር በሉ በራሴ ሰርግ ተጋባዡን የምጠራው እኔ እንጂ ተጋባዡ አይወስንልኝም በማለቷ ምክንያት የተጨነቁ መሆኑን ተገንዝበንበታል። በራሳቸው አባባል when the going gets tough, the tough gets going  ማለት ነው።

ስለሆነም በችኩል ውሳኔአቸው ተፀፅተዋል። ዝግይቶ የመጣ ፀፀት። በነርሱ ንግግር ጨርሶ ከሚቀር ዘግይቶ መደረጉ (better late than never) አይከፋም ነው ። ማጣፊያው አጠረና የመጀመሪያ ውሳኔአቸውን ቀለበሱት። ለዚህም መውጫ መንገድ (የጎበዝ መውጫ አላልሁም) ፈለጉ። ካፈርሁ አይመልሰኝ ሆኖባቸውና እሽ ታዛቢ ሳይሆን ባለሙያ እንልካለን የሚል ጨዋታ አመጡ። ድሮስ ታዛቢ የሚልኩት ባለሙያ እንጂ ከመንገድ የተለቀሙ መደዴች ሊሆኑ ኖሯል።

ለነገሩ እነሱ ምርጫ ሲያካሂዱ ታዛቢ ላኩ ብለው ጠይቀውን ያውቃሉ፤ እኛስ ታዛቢ እንላክ ብለን ጠይቀናቸው እናውቃለን? ሳይጠሩት አቤት የሚልና እንዲሁ ጥልቅ ብሎ የሚገባ ዝምብ እንጂ ሰው አይደለም። በዚህም አለበዚያ ታዝቢም ሆነ ባለሙያ ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጡ ነው ነገሩ። ሁለቱም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው። ምንም ልዩነት የላቸውም። ከመጡ እሰየው ከቀሩም እንደፍጥርጥራቸው። ባቄላ ቀረ ምን ቀለለ አለ ያገሬ ሰው።

ይሁን እና ሁሉም ሊአስታውሰው የሚገባ ጉዳይ ቢኖር ትዕግስትን እንደ ፍርሃት አንዲቆጥሩ ግን መፍቀድ የለብንም። ይህ የሆነ ጊዜ ነው እንደልባቸው የሚፈነጩብን። ገንዘባቸውንና ሃይላቸውን መከታ አድርገው ድሃ አገርና ሕዝብን ማስፈራራት የተካኑበት ሙያ ነው። እነርሱ በጠበቃ ኩባንያ (lobby firm) በገንዘብ ተገዝተው ወራዳ ተግባራቸውን ስለሚፈጽሙ ኢትዮጵያም ለገንዘብ ስትል ህልውናዋን የምትሸጥ መስሎ የታያቸው ናቸው።

በኃይልና በሃብት የሚመካ መንግስት፤ ቡድንና ግለሰብ የፈሪዎች ሁሉ ፈሪ፤ የትንሾች ሁሉ ትንሽ ነው። በራሱ የተማመነ፤ የራሱ ስብእና ብሎም ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው ሕዝብና ሃገር ምንም ያህል ምዕራቡ ዓለም ቢጠላውና ሊአዋርደው ቢሞክር ከቶውኑ አይወድቅም። ከመሬት ተነስቶ የአውሮፓ ህብረት የባለሙያ ቡድን እንደሚልክ ሲአስታውቅ እኛ እንደነሱ በደስታ ገንፍልን ጮቤ ሳንረግጥ ድሮስ ማን ከለከላችሁ ልንላቸው ይገባል።

በቅርቡ ጄፍ ፒርስ (Jeff pearce) የተባለው ጸሐፊና የኢትዮጵያ ጠበቃ ‘ኢትዮጵያ አታፍርም(Ethiopia without Shame[2]) የተሰኘውን መጣጥፍ እኔ ወደ አማርኛ ተርጉሜ ባስነበብኋችሁ ጽሑፉ ላይ የሰጠውን ምክር በጥሞና እንመልከት። ይሄውም የአንድ ሀገር የስነልቡና ፅናት ከወቅቱ መንግስት፣ ከዕዳውና ከውጭ ንግዱ በላይ ስለሆነ በሐሰት ትርክት፣ በመሰረተቢስ መጣጥፍ፣ በማህበራዊ ድረ ገጾች በዘፈቀደ በሚሰነዘሩ ስድቦች እና እንቶፈንቶዎች የኢትዮጵያና ሕዝቧ አይበገሬነት ሊሟሽሽ ወይም ሊሞት እንደማይችል አውቀን በአንድነት እንጓዝ። የአባቶቻችንና የእናቶቻችን ልጆች መሆናችንን ደግመን ደጋግመን ማሳየት አለብን። ስለሆነም አይዞሽ ኢትዮጵያ ከዚህ የበለጠ ድህነትና መከራ አይደርስብሽም። ኢትዮጵያን ሁሌም በእናት ስለምንመስላት እንኳን ለእናቶች ቀን ግንቦት 1, 2013 (May 9, 2021) አደረሰሽ እንበላት። አበቃሁ።

ሰማነህ ታ. ጀመረ (የቀድሞ ተመድ ሰራተኛ) – ኦታዋ ካናዳ፤ ሚያዝያ 30, 2013


    Leave a Reply