የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ አጀንዳ ቀርጸው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ተገለፀ

በህዳሴ ግድብና ሌሎች ሃገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የኢትዮጵያን ሚና ለማጉላት የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አጀንዳ ቀርጸው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡

ከባለሙያዎቹ መካከል በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት አርታኢው ሄኖክ አበራ ለኢዜአ እንደገለፀው፤ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን የየዕለት አጀንዳ ሊሆን ይገባል።

የግብጽ መገናኛ ብዙሃን አባይ የህልውናቸው መሰረትና መነሻውም ግብጽ እንደሆነ የየዕለቱ አጀንዳቸው በማድረግ ደጋግመው በመስበክ ትውልዱን በመቅረጻቸው ከኢትዮጵያዊያን በተሻለ የአባይ ውሃ የኔ ነው የሚል መረዳት እንዲይዙ ማድረጋቸውን ጠቅሷል፡፡

“ከእነሱ ጋር ሲወዳደር እኛ አልሰራንም፤ የመንግስትን አቅጣጫ ከመጠበቅ ውጭ አጀንዳ ቀርጸን አልተንቀሳቀስንም፤ ከዚህ በመውጣት የየዕለት አጀንዳችን አድርገን መስራት አለብን” ብሏል፡፡

“ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ግድብ የምትገነባው የኢኮኖሚ አቅሟን ለመገንባት ሳይሆን ግብጽና ሱዳንን ለመጉዳት እንደሆነ አድርገው የሚረዱ ግብጻዊያን በሚለየን ተከፍሏቸው የሚያሳምኑ ሰዎችን ሳይቀር በመገናኛ ብዙሃን ቀርበው እንዲናገሩ ያደርጋሉ” ብሏል፡፡

ጋዜጠኛው የግድቡ ጉዳይ ከህልውና ጋር የተያያዘ መሆኑን ተረድቶ የየእለት ተግባሩ ማድረግ እንዳለበት ጠቁሟል።

በግድቡ ዙሪያ የሚከናወኑና ትላልቅ ሃገራዊ ጉዳዮችን የአለም ሃገራት እንዲረዱ አሁን የተጀመረውን በተለያዩ ቋንቋዎች የመስራት ልምድ ማጠናከር፣ ግብጽ ለምታነሳው አጀንዳ ከመስጠት ይልቅ የሁልጊዜ አጀንዳ መቅረጽ ከችግሩ መውጫ መንገድ እንደሆነም ገልጿል።

በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የሻሸመኔ ቅርንጫፍ ጋዜጠኛ ጥላሁን ይልማ በበኩሉ፤ የአልጀዚራና ግብጽ መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ የራሷን ግድብ የምትገነባ የማይመስል ጽንፍ የያዘ ዘገባ እንደሚያቀርቡ ተናግሯል።

የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እነሱ የሚሰጡንን አጀንዳ ተከትለን የምንከውን እንጂ ራሳችን ቀርጸን የምንሰራው አይደለም ብሏል።

በሃገር ውስጥ የሚሰሩ ዘገባዎችም ተመሳሳይነት ያላቸው፣ የግንባታው ሂደት የደረሰበትን፣ ሙሌቱንና የቦንድ ሽያጭ ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ጠቁሟል።

አለም አቀፉ ማህበረሰብ እውነታውን እንዲረዳ መገናኛ ብዙሃን አጀንዳ ቀርጸን የግድቡ ግንባታ ለተፋሰሱ ሃገራትና ለአፍሪካ ቀንድ ኢኮኖሚ መነቃቃት የሚኖረውን ፋይዳ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ማስረዳት እንደሚገባ ተናግሯል።

ኢትዮጵያ በአባይ ግድብ ያላትን የባለቤትነት መብት ለአለም አይደለም ለኢትዮጵያውያን እንኳን በተገቢው አላስተዋወቅንም ያለው ደግሞ በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን የዜናና ወቅታዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና አዘጋጅ ጸጋአብ ዮሐንስ ነው፡፡

በማህበራዊ ትስስር ገፆች በየጊዜው አጀንዳ እየቀረጹ የሚጽፉ ሰዎች መኖራቸው መልካም መሆኑን የጠቀሰው ጋዜጠኛ ጸጋአብ “አሁን እንደሃገር ከገባንበት ችግር ለመውጣት በተለይ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚሰሩ ዘገባዎች ታሪካዊ ሂደቱን የሚያሳዩ፣ የተፋሰስ ሃገራቱን ተጠቃሚነት የሚያጎሉና እውነታውን በተገቢው የሚገልጹ ሊሆኑ ይገባል” ብሏል።

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት መምህር ዶክተር መልሰው ደጀኔ በበኩላቸው፤ በትልልቅ ሃገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መገናኛ ብዙሃን አጀንዳ ቀርጸው መስራት ከሃላፊነት ባሻገር ሙያዊ ግዴታቸውም ጭምር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የግብጽ መገናኛ ብዙሃን ለሚያነሱት ዘገባ ምላሽ ከመስጠት የዘለለ የሀገር ውስጡ የራሳቸውን አጀንዳ እየሰጡ አለመሆኑን ጠቅሰው ችግሩ የጋዜጠኛች ብቻ ሳይሆን የዘርፉ ተቋማት ስርዓት ቀርጸው አለመስራታቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

ግብጾች በተለያዩ ቋንቋዎች የሚሰሩት ዘመናቸውን ሙሉ ነው ያሉት አቶ መልሰው በኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ የተጀመረ ቢሆንም መጠናከር ያለበትና መገናኛ ብዙሃኑን ከዲፕሎማቶች ጋር በቅርበት እንዲሰሩ ማድረግም ችግሩን ለማቃለል እንደሚረዳ ተናግረዋል።

ዶክተር መልሰው እንዳሉት፤ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከአጀንዳ አልፎ የሁልጊዜ ጉዳይ መሆን አለበት፣ ከጎረቤት ሃገራት ጋር የሚሰራው ስራ ዘመን ተሻጋሪ በመሆኑ ተከታታይነት ያለው ዘገባ ያስፈልጋል፡፡

ሰኔ 5/2013 (ኢዜአ)

Leave a Reply