ምርጫው ወደ ጥምር መንግስት?

ኢትዮ 12 ዜና – ኢትዮጵያን ለማፍረስና ለማዳን በተደረገው፣ እየተደረገ ባለውና ወደፊትም ሊደረግ በሚገባው አግባብ ሲታይ “ያገባኛልና ያገባናል” የሚለው እሳቤ የእያንዳንዱ ዜጋ መመሪያ ሊሆን እንደሚገባ ይታመናል። ለማፍረስ የሚተጉ ጥቂቶች ክንዳቸው የሚበረታው ለበጎ ተግባር መንቀሳቀስ የሚችሉ አብዛኞች ዝም በማለታቸው የተነሳ በመሆኑ የአገር ጉዳይ ለማንም የሚተው ጉድያ እንዳልሆነ በርካቶች ይሳማማሉ።

ሰኞ የሚደረገው ምርጫም ልዩ የሚሆነው ተዳፍኖና ተሰባብሮ የነበረው “ያገባኛልና ያገባናል” የሚለው መርህ ከወትሮው በተለየ ከዳር እሰከዳር ዳግም ተጠግኖ በመቀጣጠሉ የተነሳ ነው። በዚህ ስሜት ተሰፍሮና ተለክቶ የሚካሄደው ምርጫ አሸናፊና ተሸናፊ ቢኖረውም በወል የአገር ድል ተደርጎ ሊታይ እንደሚገባው ስምምነት አለ። ይህ ስምምነት ነው ከየአቅጣጫው ሲረጭ የቆየውን የተቀነባበረ የክፋት መርዝ አወርዝቶ የከሰለው።

በርካታ ጣጣ፣ ሰንክሳር፣ ጫናና ሁከት ታጅቦ እዚህ የደረሰው ምርጫ አጀንዳው በሰላም ተዘግቶ ዜጎች ወደ መደበኛ ህይወታቸው መመለስ እንደሚፈልጉ በቅድመ ምርጫ ዳሰሳ የተሳተፉና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ለኢትዮ12 ከሁለት ሳምንት በፊት ሃሳባቸውን አካፍለዋል። እንደ እሳቸው አባባል በተዛወሩባቸው አካባቢዎች አብዛኛው ህዝብ መደበኛ ሕይወት ናፍቆታል። በተለይ አዲስ አበባ ከኑሮ ውድነቱ ግብግብ በተጨማሪ የአገሪቱ ድባብ የሚያስጨንቃቸው የምርቻው አጀንዳ እንዲዘጋ ፍላጎታቸው ገሃድ ነው።

ኢትዮ 12 ካናገረቻቸው ጋዜጠኞች መካከል ስሙን ያልገለጸው አዲስ አበባ ሲባል በተለምዶ አራት ኪሎ፣ ስድስት ኪሎ፣ ፒያሳ ወይም መርካቶ እንዳልሆነ አስታውሶ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉትን አዳዲስ ክፍለከተሞችና የነዋሪዎችን ብዛት አብዛኞች ዘንግተውታል ይላል። የአዲስ አበባ ዳር ዳርዋ መካከሉን በልጧልና የአራት ኪሎ ወይም ቤላ ስሜት ድፍን አድሲ አበባን እንደማይወክል ይናገራል። በዚሁ መነሻ ምርጫው ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ማስላት፣ ከሁሉም በላይ በየምርጫው ክልልና ታቢያ ለውድድር የቀረቡትን ወገኖች ብቃት ማየትም አግባብ እንደሆነ ያመልክታል። ቅድመ ትንበያው ግን ወደ ብልጽግና ያጋድላል።

የባንክ ባለሙያው አቶ በላይ ባይሳ ምርጫው “ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ያሸጋግራል” ባይ ናቸው። ጋዜጠኛ ፍቱን ታደሰ በበኩሉ ምርጫው ” ሃገራችንን ለመበታተን የተዘጋጀውን ህገ መንግስት ለመቀየር የሚያስችለንን constitutional dialogue ለማካሄድ እድል ይፈጥርልናል” ሲል የምርጫው ፋይዳ ግዙፍ መሆኑንን ያመለክታል። ሳምሶን ሚኻሎቪች ደግሞ ” ብልጽግናና ኢዜማ የጥምር መንግስት የሚመሰርቱ ይመስለኛል” ሲል አዲስ ነገር ይተብቃል። ጋዜጠኛ ቃል ኪዳን አምባቸው ” የአሁኑ ምርጫ፣ ምርጫ ብቻ ሳይሆን አገርን የማሸጋገር እና የቀውስ ጊዜ ፖለቲካን የማለፍም ጉዳይ ነው ” ሲል የምርጫውን ዋጋ በአገር ለክቶ ያገዝፈዋል።

May be an image of Kalkidan Ambachew, hair, standing, suit and outerwear
ቃል ኪዳን አምባቸው

በተለይም አዲስ አበባ ላይ የጎላውን እይታ አስመልክቶ ቃል ኪዳን አምባቸው የሚከተለውን ብሏል። ቃል ኪዳን ከመጽሃፍት ጋር የጸና ቁርኝት ያለው፣ ከመጽሃፍት ጋር ያለው ቁርኝት በደንብ የሞረደው የአድሲ አበባ ነዋሪ ነው። ብልጽግና አዲስ አበባ ላይ ኮርቶ እንደሚያሸንፍ ይናገራል። ይህን ሲል ምክንያቶች አሉት።

የአሁኑ ምርጫ ምርጫ ብቻ ሳይሆን አገርን የማሸጋገር እና የቀውስ ጊዜ ፖለቲካን የመለፍም ነው፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብ የዚህ የተወሳሰበና ውጥንቅጡ የወጣ ፖለቲካ ሰለባ ነው።ብልጽግና አገሪቱ ለሰላሳ ዓመታት የተጫነባትን የፖለቲካ ዳፋ እያቀናነሰ፣ የረጋ መንግስትነት በማቋቋም ሰላም የሰፈነባት ሃገር ይገነባል የሚል ዕምነት በአብዛኛው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ዘነድ አለው። በአንጻሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይህንን የአገሪቱን ነባራዊ ዕውነታ ያልተረዱ፣ በስሜት የሚነዱ እና የጦዘውን የብሄር ፖለቲካ ያላገናዘቡ፣ የሃይማኖት ውጥረቱ አደጋ ያልታያቸው እንደሆኑ አድርጎ አብዛኛው ማህበረሰብ ይስላቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባና በዙርያዋ ካሉ የኦሮሚያ ከተሞች ጋር የሚፈጠረው ውጥረት አዲስ አበቤን ያሳስበዋል።

አሁን ያለው የአዲስ አበባ ሁናቴ በኮረናና በፖለቲካ አለመረጋጋት ከፍተኛ የኑሮ ውድነት የተስተዋለበት በመሆኑ አብዣኛው ማህበረሰብ ተጨማሪ ጫና መሸከም አይፈልግም። ሁሉም ሆኖ ትልቁና ዋነኛው የብልጽግና አቅም ጠቅላይ ሚንስትሩ መሆናቸው ግን አይካድም። የአዲስ አበባ ነዋሪ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ከፍ ያለ አክብሮት እና ለላቀ ስብዕናቸው የገዘፈ እውቅና ያለው መሆኑ ነዋሪው ብልጽግናን ተስፋ እንዲያደርግና እንዲያምን ያደርገዋል የሚል ዕምነት አለኝ።

ሌላው ቴክኒካዊ ዕይታ ነው። አዲስ አበባ ላይ የተፎካካሪዎች ድምፅ በከፋ ደረጃ የተከፋፈለ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፡፡ ይኸ ደግሞ ከፍተኛ የካድሬ ቁጥር ላለው ብልጽግና በደጋፊዎቹ ታጅቦ የከተማውን ምክርቤት በርካታ ወንበር በማሸነፍ የአዲስ አበባን መስተዳድር ለማሸነፍ አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥሩለት ቃል ኪዳን አስተያየቱን ይቋጫል።

ሳምሶም ሚሃሎቪች በፌስ ቡክ ሚዛናዊ አስተያየት በመስጠት የሚታወቁና የሚወዱትን ፖለቲካና እምነት ለማወደስ የሰለጠነ ዘዴ ከሚጠቀሙት መካከል የሚመደቡ በሳል ፖለቲከኛና ብዕረኛ ናቸው። ለኢትዮ 12 አስተየት እንዲሰጡ ተጠይቀው “እገሌ ያሸንፋል ለማለት ያስቸግራል” ሲል የአዲስ አበባን ምርጫ አስመልክቶ ሃሳባቸውን ይሰታሉ። አስከትለውም “በግሌ ብልጽግናና ኢዜማ ተቀራራቢ ድምጽ ይኖራቸዋል” ካሉ በሁዋላ ጋዜጠኛ ቃል ኪዳን እንዳለው ሁሉ የተቃዋሚዎች መከፋፈል ለብልጽግና ትልቅ እድል እንዳጎናጸፈው መካድ እንደማይቻል ይገልጻሉ። ያም ሆኖ ግን ” ሸገር ላይ ብልጽግናና ኢዜማ የጥምር መንግስት የሚመሰርቱ ይመስለኛል” ሲሉ ምርጫው አዲስ ነገር ይዞ እንደሚመጣ ይገምታሉ።

ሳምሶን በፌስ ቡካቸው “መልካም ዕድል ለእስክንድር !” አሉ። ሲቀጥሉም ” ብዙ ሰው እንደሚያውቀው የእስክንድር ነጋም እርሱ የመሰረተው ባልደራስ ፓርቲም ደጋፊ አይደለሁም። በግሌ እስክንድር ከጋዜጠኝነት ወደ ፖለቲከኝነት የሚያደርገውን ሽግግር አጠናቋል ብዬ አላምንም” አሉ ። “ማንም ሰው ከእናቱ ሆድ የበቃ ፖለቲከኛ ሆኖ እንደማይወለደው ሁሉ እስክንድርም በሂደት የተዋጣለት ፖለቲከኛ የማይሆንበት ምክንያት የለም … እስክንድር ለአዲስአበባ ም/ቤት ተመርጦ ከኢዜማው ክቡር ገና እና ከብልጽግና ተመራጮች ጋር በሀሳብ ሲፋለም ማየት ምኞቴ ነው” ሲሉ ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።

የባንክ ባለሙያው አቶ በላይ ባይሳ

አቶ በላይ ባይሳ

የዘንድሮ ምርጫ ከመደበኛ ምርጫ ከፍ ያለ ሃገርን ለማስቀጠል የሚደረግ የህዝብ ይሁንታ የሚረጋገጥበት ነው ማለት ይቻላል።ከፓርቲ ርዕዮት ባሻገር ኢትዮጵያን ካለችበት ውስብስብ ችግር ወደተሻለ ምእራፍ ለማሸጋገር ብሎም ወደ እድገት ጎዳና ሊወስዳት የሚያስችል ድልድይ ስለሆነ የያንዳንዱ ዜጋ ድምፅ ዋጋው ከፍ ያለ እና የሃገሪቱን መፃኢ-ፈንታ የሚወስን ነው።ስለሆነም ሁሉም ዜጋ የፓለቲካ ድርጅትን ብቻ እንደሚመርጥ ሳይሆን ኢትዮጵያንም እንደሚመርጥ ጭምር ታሳቢ በማድረግ የፓለቲካ ድርጅቶቹ ያቀረቡትን አማራጭ ሃሳቦች ግምት ውስጥ በማስገባት አሁን ላይ ሃገሪቱን ወደፊት ሊያራምድ የሚችልብልህ መሪ፣ ልማትን በማፋጠን ሃገርን የሚያሳድግ፣ ፅናትን የተላበሰ፣ ግልፀኝነትን በማስፈን የዜጎችን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ የሚችል ና እንደ ንስር አሻግሮና አርቆ የሚያየይ ብቁ ግለሰብ ወይም ጠንካራ ድርጅትበመምረጥ የዜግነት ሃላፊነቱን መወጣት አለበት።ለተወዳዳሪዎች መልካም እድልን እመኛለሁ! ኢትዮጵያ ትመርጣለች! ታሸንፍማለች! የሚል ሃሳባቸውን በማህበራዊ ገጻቸው አካፍለዋል።

አቶ በላይ መልካም ሃሳብ በማካፈል የሚታወቁ ኢትዮጵያዊ ናቸው

May be an image of 1 person
ፍቱን ታደሰ

የሪፖርተር አንጋፋ ጋዜጠኛ ፍቱን ታደሰ ለፌዴራል መንግስት የሚደረገውን ምርጫ ብልፅግና እንደሚያሸንፍ አይጠራጠርም። ብልፅግና አሸንፎ ዶክተር አቢይ በጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ይቀጥላሉ የሚል እምነቱ የጸና ነው። በማህበራዊ ገጽ በጎ ተግባራትን በማጋራት የሚታወቀ ፍቱን፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም እስካሁን ከነበረው በተሻለ ሁኔታ ፓርላማ ውስጥ በርካታ ወንበሮችን እንደሚያገኙ ይገልሳል።

በተለየ የአዲስ አበባን ምርጫና ውጤት አስመልክቶ ግን ኢዜማ አብላጫ ድምፅ አግኝቶ የሚያሸንፍ ይመስለዋል። ብልፅግና እና ባልደራስም በብዙ ወረዳዎች አሸንፈው ወንበር ማግነታቸውን ይጠቁማል። “በመጪው ዓመት የተሻለ ፓርላማ ሊኖረን ይችላል። እንዲህ መሆኑ ደግሞ ሃገራችንን ለመበታተን የተዘጋጀውን ህገ መንግስት ለመቀየር የሚያስችለንን constitutional dialogue ለማካሄድ እድል ይፈጥርልናል” ሲል አስተያየቱን አጠቃሏል።

ሁሉም ዓይነት አስተያየት በሚሰማበት በአሁኑ ወቅት ምሁራን ስለ ጥምር መንግስት አበክረው መናገራቸውና የአገሪቱን የተከመረ ችግር ለመፍታት መልካም አጋጣሚ አድረገው እያዩትም ስለሆነ የጥምር መንግስት ምስረታ ዜና አየሩን ሞልቶታል። ኢትዮ 12 ዜና

Leave a Reply

%d bloggers like this: