የሬዲዮ ግንኙነቱ ተቋርጧል።የስልክ መስመሮች ድምፅ አልባ ሆነዋል።የከተማው መብራት ጠፍቷል።የወታደራዊ ሬዲዮ ግንኙነት አባላት ግን ጥበብ በተሞላበት መልኩ ከበላይ አመራርጋ የሚያገናኛቸውን ግንኙነት ፈጠሩ።
የሀገሪቷ የጦሩ የሰላ ጫፍ ለይ ያሉ ጄነራል በከበባ ውስጥ ያሉትን አዛዥ ለማነጋገር መስመር ለይ ናቸው።አዛዡ ቀርበው የሬዲዮውን እጀታ ወደ ጆሯቸው አስጠጉ።እጅግ አስገምጋሚ ድምፅ በሞገድ ውስጥ መጣ!
“አዝናለው እንዳለን ወዳጅነት እንደመሪ እና ተመሪ ግንኙነታችን ልባዊ እና ጥልቅ ሰላምታ ለመለዋወጥ የሚሆን ጊዜ የለንም!እስክንደርስለህ ድረስ ባለህ ነገር ሁሉ ተፋለም።ታንኮችህ ቀጥታ ተኩስ እየተኮሱ እንዲሁም የጠላትን ሀይል እየደፈጠጡ አንተ ወዳለህበት ማዘዣ ጣቢያ እንዲመጡ አድርግ።ከዛ ሀይልህን ይዘህ ጎረቤት ሀገር ግባ።”
አዛዡ “እሱን አልችልም!ብረት ለበሶቹም ሆኑ ታንኮቹ የሞሉት ነዳጅ እኔ ወዳለሁበት ማዘዣ ጣቢያ አያደርሳቸውም!!ቀድመን የተዘጋጀነው ከፊት እንጂ ከጀርባችን እንወጋለን ብለን አይደለም!!”
“ባሉበት ሆነው ወዳንተ እየተኮሱ ድጋፍ እንዲሰጡህ ማድረግስ አትችልም!?”
ብ/ጄነራል “ክቡር ጄነራል!እርሶም እንደሚያውቁት ዳንሻ ያለንበት ካንፕ በህዝብ መሀል ይገኛል። የመጀመሪያው ጥይት ሲተኮስ ያረፈበትን አይቶ ለማረም ያስቸግራል።ከረዘመም ካጠረም ህዝባችን ለይ ይወድቃል! ያ ከሚሆን ደሞ እኛ ብናልቅ ይሻላል።”
“ካንተ የቅርብ ርቀት ለይ ያሉት ሀይሎች የተሻለ ከፍታማ ቦታ ለይ ስላሉ እራሳቸውን ለመከላከል በቂ ናቸው።ስለዚህ የተወሰነ ሀይል ቀንሰው ወዳንተ እንዲልኩልህ አድርግ❗”
“ጠላት ቀድሞ ተዘጋጅቶበት ስለሆነ ዲሽቃ እና መትረየስ የታጠቀ የተወሰነ ሀይል እንዳንገናኝ እና በተኩስ እንዳንተጋገዝ መሀል ለይ አስቀምጧል። ቢሆንም ግን በትንሽ መሰዋዕትነት የጠላትን ሀይል ሰብረው ወደ እኛ ለመምጣት አሁን ውጊያ ለይ ናቸው። ተሳክቶላቸው ይመጣሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን።ከዛ እናንተ እስክደርሱ እራሳችንን እንከላከላለን❗”
ባለ ብዙ ኮኮቡ ጄነራል ቀጠሉ። ” ባንተ የፀና እምነት አለኝ።አሁን ቀጥዬ የምነግርህ መመሪያ ነው።ካንተ ስር ያሉት አባላቶችህ ተስፋ ቆርጠው መዋጋታቸውን እንዳያቆሙ።ጠላት የድል መንፈስ እንዳይላበስ። ለዚህም ሲባል ለአንተ መሞትም ሆነ መማረክ በፍፁም አልፈቅድልህም። መልካም እድል!”
ግንኙነቱ ተዘጋ።
ድጋፍ ለመስጠት የተወሰነ ሀይል ይዘው ይመጡ ከነበሩት ሁለቱ ኮረኔሎች አንዳቸው ቆስለው አንድ ሰው ሰውተው ከግቢው ደረሱ።
አዛዡ የነፍስ ወከፍ ኤኬም ከዘጠና ጥይት ጋር የታጠቁ የእስታፍ አባላትን ይዘው በልበ ሙሉነት ገጠሙ። እንደ ጄነራል አዋጉ❗እንደተራ ወታደር ተዋጉ‼የግል አጃቢዎቻቸው እና ሹፌራቸው የታጠቁትን ቦንብ ወደ ተጠጋቸው የጠላት ሀይል ለይ ወረወሩ።ከፊታቸው ከተደቀነው ጠላት ብቻ ሳይሆን ከውስጥ ከሚወጋቸው ጋ እልህ አስጨራሽ ውጊያ በዛች ጠባብ ግቢ ውስጥ እውን ሳይሆን ፊልም በሚመስል መልኩ አደረጉ። ጥቂት ጓዶች በውጊያው መሀል ቆሰሉ ተሰው። ሀረር እና አለሙን የመሰሉ ጀግኖች እየተፋለሙ በእራሳቸው ጓዶች ከጀርባቸው ተመተው ወደቁ።ሀረር ተመልሶ አልነቃም❗
ጀግናው የአማራ ልዩ ሀይል ሶረቃ ለይ የነበረውን ጠላት ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀር ደምስሶ ከፊቱ ያገኘውን እየመነጠረ አዛዡ የተከበቡበት ግቢ በአጥር እየዘለለ ገባ።የሞት ሽረት ትግል ለይ የነበሩት አባላት አይናቸውን ማመን አቃታቸው። የአማራ ክልል ልዩ ሀይሎች ከምድር ይፍለቁ ከሰማይ ይዝነቡ እስካሁንም መልስ ያላገኙለት ጉዳይ ነው።
ክብር እና ምስጋና የጦር ሜዳ ውሎ እና ገድላቸው በሽለላ እና በዘፈን ደምቆ ላልተነገረላቸው የአፋር ክልል ልዩ ሀይሎች‼
Via – Zerihun Nuri Abote