“ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ ለምን?”

ወዳጆቼ፤ ለመሆኑ ታላቋ አገራችን ኢትዮጵያ እንደ አሁኑ ከየአቅጣጫው በፈተና የተወጠረችበት ጊዜ ኖሮ ያውቃል? (ቢኖርም ባይኖርም ለወደፊትም ፈጽሞ አይግጠማት!) ያለ ኃጢያቷ መከራዋን በላች እኮ! ከውስጥም ከውጭም እኮ ነው እየተናጠች ያለች በአንድ በኩል እነ ግብፅና ሱዳን የጎን ውጋት ሆነውባታል- በፈረደበት የህዳሴው ግድብ ጉዳይ! በሌላ በኩል ዓለማቀፍ ማህበረሰብ ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ ዕለት ተዕለት ይነዘንዟታል፡፡ በእርግጥ  በዚህ ሁሉ ተግዳሮቶች መሃል ሁለት ትላልቅ ስጋቶችን በአንድዬ እርዳታ ወደ ተስፋ ለውጠናቸዋል። ብዙዎች የቀውስና የግጭት ምንጭ ይሆናል ብለው ያሟረቱበትን 6ኛ አገራዊ ምርጫ፣ ወደ ተስፋና በረከት ለውጠነዋል፡፡ ያውም በኢትዮጵያዊ ጨዋነት! (ጠ/ሚኒስተራችን   ዓለም በምርጫው ይበጣበጣሉ ብሎ ሲጠብቀን እኛ “ምርጫችን በሰላም አጠናቀን ለዓለም ትምህርት እንሰጣለን” ነበር ያሉት ልበል?) ተሳክቶቷልና!
የህዳሴው ግድብ ሁለተኛው የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ ሌላው ስኬታችን ነው።  ያውም በአስደማሚ ዲፕሎማሲያዊ ድል የታጀበ!  
እና…. ምን ለማለት ነው? ችግሮችና ውጣ ውረዶች ተከበንም ጭምር ትላልቅ ግባችንን አሳክተናል። ትላልቅ ድሎች ተቀዳጅተናል። በሌላ በኩል አሁንም ድረስ  ከዓለማቀፉ ማህበረሰብ  ጫና ተፅዕኖ ነጻ አልወጣንም።  (ዛሬም ስለማዕቀብ እያወሩ ነው!)
የፌደራል መንግስቱ ማንም ባልጠበቀው ሁኔታ የተናጥል ተኩስ አቁም አውጆ፣ መከላከያን ከትግራይ ማስወጣቱ፣ በእጅጉ ጠቅሞታል፡፡ ከምዕራባውያን ጫናና ተፅዕኖ በጥቂቱም ቢሆን እፎይ ብሏል። የትንፋሽ ጊዜም አግኝቷል። በዋነኝነት ግን የህወኃት ቡድንን እውነተኛ ማንነት (አሸባሪነቱን ማለት ነው) ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ ለማጋለጥ መልካም አጋጣሚን ፈጥሮለታል። የህወሃት ቡድኑን ከዋሻ ወጥቶ መቀሌንና ሌላውን የትግራይ አካባቢ በተቆጣጠረ ማግስት፣ “የመንግስት ደጋፊዎች ነበራችሁ” በሚል ዜጎች ላይ የወሰደው የበቀል የግድያ እርምጃም  የቡድኑ እነተኛ ገፅታ ለዓለም ያስመሰከረ ተግባር ነው። በኤርትራ ስደተኞች ላይ የፈጸመው  አስከፊ ጥቃትስ? ይኼ የጁንታውን ማንነትን ፍንትው አድርጎ ለዓለም ያሳየ ኹነት ነው። ከሰሞኑ የእርዳታ እህል ጭነው ወደ ትግራይ የሚጓዙ መኪኖችን መንገድ መዝጋቱስ? ዓለማቀፍ ማህበረሰብ በዚህ የህወሃት እንግዳ ባህርይ በእጅጉ ሳይገረሙ አይቀሩም፡፡ ለገዛ ህዝቡ የሚደረስ የእህል እርዳታ ላይ ቀርቶ አሻጥር የሚሰራ ማንም የለም- ከጁንታው!
 ቡድኑ መቀሌ በገባ ማግስት (እረፍት እንኳ ሳያደርግ) አዲስ የጦርነት ትንኮሳ ወደ ከአማራ አፋርና ኤርትራ ማድረጉም ፈረንጆቹን ግራ ማጋባቱ አይቀሬ ነው።  ከእልቂትና ጥፋት፣ ወደ ሌላ ዙር እልቂትና ጥፋት! ህፃናትን በጦርነት ላይ ማሰለፉም ሌላው አስደንጋጭ የቡድኑ ማንነት መገለጫ ነው። ለማያውቁትም ብቻ ሳይሆን ለሚያውቁት ጭምር!
ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ሌላ ዓላማ ከሌለው በስተቀር በዚህ አጋጣሚ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በትግራይ ክልል፣ በትክክል ምን  እየተካሄደ እንደሆነ የሚገነዘብበት ዕድል ተፈጥሮላቸዋል- ፌደራል መንግስቱ አስልቶና አጥንቶ ከትግራይ በመውጣቱ!! አሁን የሚቀረው የትግራይን ህዝብ ከአሸባሪው ቡድን  እንደምንም አላቅቆ ነፃነቱንና ሰላሙን ማረጋገጥ ነው። ከጦርነት ድባብ አስወጥቶ ወደ ሰላምና ልማት ድባብ ማስገባት ያስፈልጋል – የትግራይን ህዝብ!!
ያኔ እነ አሜሪካም – ዓለማቀፍ ማህበረሰብም እንኳን ኢትዮጵያ ላይ ጫና መፍጠር አይደለም   ትክ ብለውም አያይዋትም።
 የትግራይ ጦርነት (ከጁንታው ጋር የተገባው እሰጥ አገባ!) ግን በፍጥነት መቋጨት  አለበት!
 በነገራችን ላይ ታጣቂው ቡድን መቀሌን በተቆጣጠረ ማግስት፣ የተኩስ ማቆም ለማድረግ ከመንግስት ጋር ለመደራደር ሰባት የማያመስሉ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጦ ነበር።  “የማይመስል ነገር  ለሚስትህ አትንገር እንዲሉ”
አሁን ደግሞ በእዚያ የድርድር ቅድመ ሁኔታዎች ላይ መጠነኛ ማሻሻያ አድርጎ ማቅረቡ እየተሰማ ነው። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ አንዳንዶች እንደሚሉት፤ ከልቡ መደራደር ፈልጎ ሳይሆን እንደምንም ብሎ የክልሉን ባጀት በእጁ ለማስገባት ነው። (No money no funny! ያለው?! ያለ  ማነው? ገንዘብ ሆነ ህዝብን ማስተዳደር (ከዳያስፖራ በሚሰባሰብ ድጋፍ!)  ለነገሩ ዳያስፖራውም ቢሆን ገንዘብ የሚያዋጣው ለጦርነት እንጂ ትግራዋይ ዲያስፖራ ለጁንታው ጦርነት ካሰባሰበው ስንት ሚሊዮን ዶላር ውስጥ በጦርነቱ ተጎጂ ለሆኑ የትግራይ ወገኖች እንዲለግስ ሲጠየቅ መች በጄ አለ?! ይልቁንም በትግራይ ያለውን የሰብአዊ ቀውስ እንቃወማለን የሚሉ ሞልቃቃ የትግራዋይ ዳያስፖራዎች ውድ አውቶሞቢላቸውን አደባባይ አውጥተው  በዱላ ሊሰባብሩ አይተናቸዋል- በማህበራዊ ሚዲያ! ለተራቡ የትግራይ እናቶችና ህፃናት ውድ አውቶሞቢል ሰባብሮ ከጥቅም ውጭ ማድረግ… ምን ይጠቅማቸዋል?! መቼም የትግራዋይ እናቶችና አባቶች ይሄን ቢሰሙ….ንስሀ ይገቡላቸዋል።
የጁንታውን የድርድር ቅድመ ሁኔታ ሳነሳ፣ አንድ ስሙን የማላውቀው ኮሜዲያን፤ በዚሁ ጉዳይ ላይ ያቀረባት ቀልድ ተመችታኛለች። ራሱን አንዱ የጁንታው አባል አድርጎ ነው የሚተውነው- ኮሜዲያኑ። እናም “ዐቢይ ሰላም ፈላጊ ነው የምትሉት ውሸት ነው፤ እሱ ሰላም አይፈልግም” ሲል  ይጀምራል። ከዚያም ከዐቢይ ዘንድየእንደራደር ጥያቄ ቀርቦለት፣ ለዚሁ ዓላማ ያቀረበውን ቅድመ ሁኔታ ይነግረናል (እንደ ድርድር ቅድመ ሁኔታ ቁጠሩት!) ይገልፃል።
“ለእኔ ጠ/ሚኒስትር ታደርገኛለህ… ለደብረፅዮን ምክትል ታደርገዋለህ… … ጌታቸው ረዳን ደግሞ ኤታማዦር… ለፃድቃን ምክትል ታደርገዋለህ ከዚያም በቃ የሰላም ሰው ነህ ማለት ነው” አልኩት ይላል- የጁንታው አባል ሆኖ የሚተውነው ኮሜዲያኑ። “ዐቢይ ግን ይሄ የማይሆን ነገር ነው ብሎ ድርድሩን አፈረሰው፤ ዐቢይ ሰላም ፈላጊ ነው ትላላችሁ እንጂ አይደለም” ሲል ይወቅሳል። ዐቢይ በጦርነቱ ወቅት የተጠቀመበት አይነት ድሮን ገዝቶ እንዲሰጠው መጠየቁንም ይናገራል።  በኋላ በንዴት ሃይለቃል ሊናገር ሲዳዳው፣ የአንድ ሪፐብሊካን ጋርድ ፈጣጣ ዓይን ይመለካል። ደንግጦ ከቤተ-መንግስቱ መውጣቱን ይናገራል- ኮሜዲያኑ። ድንቅ ወቅታዊ የፖለቲካ ኮሜዲ ነው። ጁንታውን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ!!
ፖለቲካ ደስ የሚለውን እንዲህ ሲቀለድበትና ሲፌዝበት እንዲህ ሲያፋጅና ሲያስጨርስ አይደለም። ፖለቲካ ከክብ ጠረጴዛ ውጭ የሆነ ለታ ጦርነት ትራጄዲ ነው የሚሆነው። አሳዛኝ እልቂትና ፍጅት!
የሚገርመው ነገር እስካሁን የማወጋችሁ ከዛሬው የፖለቲካ አጀንዳዬ ውጭ ነው፡፡ ድንገት በጀመርኩት ሃሳብ ተወስጄ ይኸው አራት ገፅ ደረስኩ።  እንግዲህ ዋና ርዕስ ጉዳዬን በጥልቀት ባልሄድበትም ላስተዋውቃችሁና ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ።
ምን መሰላችሁ  ማውጋት የፈለኩት?  የዘር ፖለቲካን የተመለከተ ለዚህ ነው ርዕሴን  “ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ፤ ዘረኝነት” ይፍረስ! ያልኩት (ትስማማላችሁ?) ከተስማማችሁ እቀጥልበታለሁ። ባትስማሙም ግን ችግር የለውም። ብቻ በትዕግስት አድምጡኝ። ባትወዱትም ሃሳቤን በነፃነት የመግለፅ መብቴን አክብሩልኝ። በሚቀጥለው ደግሞ እናንተ  በተራችሁ ሃሳባችሁን ትገልጻላችሁ። በዚሁ ጋዜጣ-በዚሁ መድረክ! (የሃሳብ ልዩ ይለምልም!!) ጦርነትማ ለዘመኑ  አይመጥንም። ለ21ኛው ክ/ዘመን!!
እናላችሁ…. በዛሬው የፖለቲካ ወጌ ደፈር ያለ ፕሮፖዛል ነው  ለማቅረብ ያቀድኩት። ኢትዮጵያችን እንዳትፈርስ ልንታደጋት ከፈለግን፣ ዘረኝነትን ወይም አክራሪ ብሔርተኝነት አለያም  ቀድመን ልናፈርስ ይገባል። (ኢትዮጵያን አፍራሽ ጁንታው ብቻ ነው ያለው ማነው) የሚገርመኝ ከሁሉም የጁንታው ቡድን “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል መግባት ካለብን እንገባን” ያሉት ነው።
(ምነው ምነው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ?) ክፋቱ ግን ኢትዮጵያን ሲኦልም ብትገቡ አታገኟትም። (በምን ዕዳዋ!) አድራሻዋ ገነት ነው!!

አዲስ አድማስ – ምንጭ

Leave a Reply