የጥምር ቡድኑ በስደተኞች ላይ ሠብዓዊ ክብርን የናደ ጥቃት መፈፀሙን አጋልጧል

የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሠብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ የጋራ ሪፖርት አሸባሪው ህወሓት በስደተኞች ላይ አሰቃቂ እና ሠብዓዊ ክብርን የናደ ጥቃት መፈፀሙን ያረጋገጠ መሆኑን የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ገለፀ።

አለም አቀፍ ለጋሽ አካላት ስለሁኔታው የነበራቸውን የተሳሳተ ምልከታ በማረም ኢትዮጵያ ለስደተኞች ምላሽ ለመስጠት የምታደርገውን ጥረት እንዲደግፉም ጥሪ ቀርቧል።

የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በጥምር ቡድኑ የወጣው ሪፖርት አሸባሪው ህወሓት በስደተኞች ላይ ሲፈፅም የነበረውን በደል ያጋለጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በስደተኛ አያያዝ ምስጉን ስም ካላቸው አገራት ቀዳሚ መሆኗን እና በስደተኛ አያያዝ ለዘመናት የዘለቀ መልካም ታሪክ ያላት እንደሆነች ተናግረዋል።

ለስደተኞች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስና የስራ ዕድል እንዲሁም ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ የሚያደርግ፣ ከዜግነት በቀር ከዜጎች ጋር እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መብት የሰጠች አገር መሆኗንም አብራርተዋል።

ለስደተኞች የሚሰጠው ምላሽ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የጋራ ምላሽ ኃላፊነት ተደርጎ ቢታሰብም ኢትዮጵያ ኃላፊነትና ሸክምን በመጋራት መርህ ለስደተኞቸ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደምታደርግ አስገንዝበዋል።

“በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከ900 ሺህ በላይ ስደተኞችን ተቀብላ በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ 25 የስደተኛ መቀበያ ጣቢያዎች እያስተናገደች ነው” ብለዋል።

ከእነዚህ መካከል 178 ሺህ የሚሆኑት ኤርትራዊያን መሆናቸውን ጠቅሰው፤ 92 ሺህ የሚሆኑት በትግራይ ክልል የነበሩ፣ 60 ሺህ ያህሉ በአፋር ክልል እና ቀሪዎቹ በአዲስ አበባ እንደሚገኙ ዘርዝረዋል።

አቶ ተስፋሁን በኢትዮጵያ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች በአሸባሪው ህወሓት አማካኝነት ግጭት ከመነሳቱ በፊት እንደ ስደተኛ ሳይሆን እንደ ሁለተኛ አገራቸው ይኖሩ እንደነበረም አስታውሰዋል።

አሸባሪው ህወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በጀመረው ጦርነት ሳቢያ በትግራይ ክልል ከሚገኙ አራት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በህጻጽ እና ሽመልባ ጣቢያዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቁመዋል።

ጉዳዩን ካለመረዳትም ይሁን ሆን ተብሎ ከመፈረጅ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ በርካታ የስም ማጥፋት ዘመቻ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሲካሄድ መቆየቱን አውስተዋል።

ይህን በተመለከተ እውነታውን ለማስረዳት ተደጋጋሚ ጥረቶች ቢደረጉም የያዙትን እምነት መቀየር ያልፈለጉ አካላት ሚዲያዎችን ተቆጣጥረው የሀሰት ወሬ ሲያስተጋቡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ይሁንና የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሠብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ የጋራ ሪፖርት አሸባሪው ህወሓት በስደተኞች ላይ ሲፈፅም የነበረውን በደል አጋልጧል ብለዋል።

የውጭ መገናኛ ብዙሃን ሪፖርቱ አሸባሪው ህወሓት በስደተኞች ላይ አሰቃቂ እና ሠብዓዊ ክብርን የናደ ጥቃት መፈፀሙን ያረጋገጠ በመሆኑ ይህንኑ በሚመጥን መልኩ ለእውነት በመቆም ዘገባዎቻቸውን ማስተካከል ይገባቸዋል ብለዋል።

አለም አቀፍ ለጋሽ አካላትም ስለሁኔታው የነበራቸውን የተሳሳተ ምልከታ በማረም ኢትዮጵያ ለስደተኞች ምላሽ ለመስጠት የምታደርገውን ጥረት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ጥቅምት 26 ቀን 2014 (ኢዜአ)

Leave a Reply